ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተጣለበት አምስተኛ ዓመት በዓል ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ በኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት አማካይነት እየተካሄዱ ካሉ ጥበባዊ መሰናዶዎች አንዱ መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የቀረበው የኪነ ጥበብ ምሽት ነው፡፡
የመዝናኛውና ሙዚቃ ድራማ ዝግጅት እስከ መጋቢት 19 ቀን ሰኞ ድረስ የሚዘልቅ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ስታዲየምም መጋቢት 18 ቀን ከእኩለ ቀን ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር የሚያደርጉትን የእግር ኳስ ጨዋታ ጨምሮ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እንደሚከበር ብሔራዊው ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በተያያዘም ይኸው የሕዳሴ ግድብ ክብረ በዓል፣ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በመዲናይቱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አማካይነት በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ‹‹የዓባይ ዘመን ጥበብ 2008›› በሚል ርእስ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የሥዕል ዐውደ ርዕይ መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ተከፍቷል። በማግስቱም በተመሳሳይ ርዕስ አንጋፋና ወጣት ደራስያን የተሳተፉበት በቪዲዮ ምስልና በሙዚቃ የታጀበ የሥነ ጽሑፍ ምሽት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ሲቀርብ፣ እሑድ መጋቢት 18 ቀን ደግሞ መነሻውና መድረሻው ዳያስፖራ አደባባይ ያደረገ ከ170 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 12 ሺሕ ተማሪዎች የጎዳና ሩጫ እንደሚካሄድ ታውቋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ጉባ በተባለው ስፍራ እየተገነባ ያለውና ሥራው እየተጋመሰ መሆኑን የሚነገርለት የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ ‹‹የሚሌኒየም ግድብ የውኃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ፕሮጀክት›› በሚል መጠርያ የመሠረት ድንጋይ የተጣለው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሲጠነሰስ 5250 ሜጋዋት ለማመንጨት የታሰበው ግድቡ፣ ስሙ ወደ ሕዳሴ ከመቀየሩም በተጨማሪ ሜጋዋቱም 6000 እንዲደርስ መደረጉ ይታወሳል፡፡