Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአፋን ኦሮሞ ከልሳነ ግእዝ ያገኘው በረከት

አፋን ኦሮሞ ከልሳነ ግእዝ ያገኘው በረከት

ቀን:

የራሷ ፊደል ያላት ኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪኳ የሚመዘዘው በተለይ በመጀመሪያው ምታመት በአክሱም አካባቢ ነው፡፡ ከብራና (ቆዳ) እና ከወረቀት በፊት በድንጋይ ላይ በሚጻፍ ጽሑፍ የወቅቱ ገጽታና የነገሥታቱ ዜና መዋዕል በግእዝ፣ በሳባና በግሪክ ቋንቋዎች ይዘገብበት ነበር፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ልዩ ክፍሎች መተርጐም በተጀመረበት ጊዜ ከድንጋይ ወደ ብራና ሽግግር ሲደረግ በርካታ የሃይማኖትና የሥርዓት መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡

በ1500 ዓመታት የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ጎልተው ከሚታወቁት መካከል የስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ ለሥርዓተ አምልኮ የሚያገለግሉ ከኢትዮጵያ አራቱ ወቅቶች ክረምትና በጋ፣ መፀውና ፀደይ ላይ የተመሠረቱ ድርሰቶች ይወሳሉ፡፡

በምሥራቅም ሆነ በምዕራብ በግሪክ፣ በላቲን፣ በሶርያ፣ በግብፅ እንዳሉት የቅዳሴ መጻሕፍት ወደረኛ የሆነው የግእዝ የቅዳሴ መጻሕፍት በየዓረፍተ ዘመኑ ከስድስተኛው እስከ 15ኛው መቶ ዘመን ድረስ፣ ኢትዮጵያውያኑም ሲደርሱና ሲያዘጋጁ ከውጭም ሲተረጉሙ ኖረዋል፡፡

በዘመነ ጐንደር ወደ አማርኛ የመተርጐሙ እንቅስቃሴ ተጀምሮ በ20ኛው ምታመት በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ጥረት የኅትመት ብርሃን ማግኘት ችሏል፡፡

በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ግእዙን ከአማርኛ በማስተባበር ለሥርዓተ አምልኮ ሲጠቀሙበት፣ በአሥመራም (ኤርትራ) ከግእዙ ወደ ትግርኛ በመተርጐምና በማሳተም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡

በግእዝ ቋንቋ ውስጥ የሚገኙት መደበኛዎቹን 14ቱን የአናፎራ (ቅዳሴ) መጻሕፍት በተለያዩ የአውሮጳ ቋንቋዎች ተተርጉመው ምሁራን ለተለያየ ማዕረግ እንደበቁበትም ይጠቀሳል፡፡

መሰንበቻውን በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ተናጋሪ ባለው አፋን ኦሮሞ (ኦሮምኛ) 14ቱ መጻሕፍት ተተርጉመው ከግእዝ ጋር ባንድ ጥራዝ ታትመው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡

በልሳነ ግእዝና በአፋን ኦሮሞ (ግእዚፊ አፋን ኦሮሞቲን- Giiiziifi Afaan Oromootiin) የተዘጋጀው ‹‹መጽሐፈ ቅዳሴ -ክታበ ቅዳሴ- Kitaaba Qiddaasee›› መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢሊሌ ሆቴል ተመርቋል፡፡

የትርጐማና የአርትኦት ሥራው 10 ዓመት የወሰደው ባለ ሦስት ዓምዱ  ክታበ ቅዳሴ፡- የመጀመርያው ረድፍ በግእዝ ቋንቋ፣ ሁለተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በግእዝ  (ሳባ) ፊደል፣ ሦስተኛው ረድፍ በኦሮምኛ ሆኖ በቁቤ ፊደል ተጽፏል፡፡

‹‹የኦሮሞ ብሔረሰብ ምእመናን ልጆቻችን በአሁኑ ወቅት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አምልኮአቸውን መፈጸም እንዲችሉ፣ በቋንቋቸውም እንዲያስቀድሱና  እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ ተተርጕሟል፤›› ያሉት መጽሐፉን የመረቁት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ ‹‹የኦሮሞ ክልል ምእመናን ልጆቻችን እንኳን ደስ አላችሁ እንላለን፤›› ብለዋል፡፡ በሥነሥርዓቱ ላይ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስና የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣኖች ተገኝተዋል፡፡

ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በኦሮሚያ ክልል ለሚገኙ ምዕመናን እንዳደረገችው ሁሉ፣ ለሌሎች ብሔረሰቦች ምዕመናንም በተመሳሳይ የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነድፋ እያስተረጐመችና እያሳተመች ለአገልግሎት ማዋል ቋሚ ዓላማዋና ተቀዳሚ ተልዕኮዋ ስለሆነ በስፋት እንደምትቀጥልበት ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

መጽሐፈ ቅዳሴውን ለመተርጐም በነፍስ ኄር ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዘመን፣ 1998 . ጀምሮ አራት የአፋን ኦሮሞ ተናጋሪ በሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ሔኖክ (ከግምቢ)፣ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ (ከሙገር)፣ ብፁዕ አቡነ ያሬድ (ከኩዩ ጋብራ ጉራቻ) እና ብፁዕ አቡነ ኤዎስጣቴዎስ (ከሙገር) አስተባባሪነት፣ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማዋቀርና ከሊቃውንት ጉባኤ አራት አባላትን በማካተት ሥራው ተከናውኗል፡፡ ትርጉሙን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ለሚገኙ ምሁራንና የብሔሩ ተወላጅ ተማሪዎች እንዲመለከቱት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነገሩትን የቃላት (ዘዬ) አጠቃቀም ለማረምና ሁሉንም ሊያግባባ በሚችል ሁኔታ በጥንቃቄ እንደተሠራና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቋንቋ ባለሙያም በእርማቱ እንደተሳተፉ ተጠቅሷል፡፡

ትርጉም ሥራውን ለመሥራት 1997 .ም. ጀምሮ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን የገለጹት የምዕራብ ወለጋ ቄለምና አሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሔኖክ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቅዶ የትርጉም ሥራውን ለመሥራት 10 ዓመታትን እንደወሰደ ተናግረዋል፡፡ ግእዙና ያሬዳዊ ዝማሬው እንደተጠበቀ መሆኑ፣ በማእከላዊነትም የኢትዮጵያ ብቸኛ ቋንቋ ግእዝ ስለሆነ የሁሉንም ብሔረሰቦች አንድነት የሚጠብቅ ነው€በማለትም ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ሔኖክ አውስተዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሔኖክ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለትርጉም ሥራው መጀመር ምክንያት የሆኑት የንባቡን ክፍል አልፎ አልፎ በመተርጐም ፋና ወጊዎቹ የምዕራብ ወለጋ ካህናት ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ጥንታዊ የትምህርት ሥርዓት ለዘመኑ ትውልድ ለማስተማርም በምዕራብ ወለጋ በ2003 ዓ.ም. የአብነት ትምህርት ቤት መቋቋሙንና የጉሙዝ ብሔረሰብን ጨምሮ ለአካባቢው ወጣቶች ትምህርቱ ለሦስት ዓመታት እንደሚሰጥ፣ የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎችም መመረቃቸውን ሊቀ ጳጳሱ አክለው ገልጸዋል፡፡

 

 

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...