Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ደመና ባይኖርም መዝነቡ አይቀርም?

ሰላም! ሰላም! ‹‹ከቤቴ በላይ ዳይመንድ ሠፍሮ…›› አለኝ አንዱ፡፡ አልወርድም ብሎ አስቸግሮ፣ መሰላል ጠፍቶ ማውረጃ አንጋጦ ማየት አወይ ፍርጃ፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ሰው የቤት ያለህ ይላል ለካ አንዳንዱ ወርቅና አልማዝ የተንጠለጠለበት ጣሪያም አለው። ይኼ ነው እንጂ ዕድገት አልኩ በልቤ። ያው እንደምታውቁት ሁሉም ሰው የራሱ የቤት ጣጣ አለበት። ጣጣ የለኝም ሲሏችሁ አትመኑ። ድሮስ በሕዝብ መንገድ ላይ ቆሞ ማን ጣጣ አለኝ ይላል? እውነቴን እኮ ነው። ለዚያ አይመስላችሁም ጭንቅንቁ የበዛው። ሁሉም የቤቱን ጭንቅ ሊሸሽ ይወጣና መንገድ ይዘጋጋል። የዕድሉን መዘጋጋት የሚያማርር የለም። ለምን? ምክንያቱም መንገዱን ማማት ቀላል ስለሆነ። እንዲያውም አንዴ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የነገረኝ ነገር አለ። ‹‹ሰውን የምታወቀው አራት በአራት በሆነች ዛኒጋባው ውስጥ ብቻውን ሲሆን ነው፤›› ብሎኝ ነበር። ብቻውን ከሆነማ ማን ያውቀዋል እለዋለሁ ራሱ ነበር መልሱ።

አይዟችሁ ይኼን ተረት ብዬ አፌን በዳቦ አብሱ አልልም። እንዴ ዳቦ እኮ ሦስት ብር ገብቷል። ሦስት ብር ዓባይን ይገድባል። እንግዲህ ታዲያ ዘንድሮ በተረት አሳቦ አፌን በዳቦ አብሱ የሚል የህዳሴ ግድባችን ህልውና ላይ የሚዘባበት ብቻ መሆን አለበት ማለት ነው። አሁን ይኼን ከጣራው በላይ ‘ዳይመንድ’ ከሠፈረበት ወዳጄ ትርክት ጋር ምን ያገናኘዋል? ምንም! ብቻ ሰውና ሐሳቡ፣ ሰውና ዕቅዱ፣ ሰውና ሰው አልገናኝ ባሉበት በዚህ ጊዜ ወሬ አልተዛመደም ተብሎ እብደት ቢጀመር አደራ እኔ ሰበብ እንዳልሆን። ይልቅ የሚረባውን ለወዳጄ ምን መከርኩት መሰላችሁ? ‹‹ለምን አታወርደውምና አትገላገልም?›› አልኩት። ‹‹መሰላል ጠፋ፤›› አለኝ። ‹‹ታዲያ መሰላል ካጣህ ‘ዳይመንዱ’ ራሱ እንዲወርድ መላ ፈይዳ፤›› ስለው፣ እሱማ ቤቱ ካልፈረሰ አይሆንም። ቤት ማፍረስ ደግሞ ከ9/11 ወዲህ ሽብርተኝነት ነው፤›› አለኝ። ይኼው ዳይመንድ አለኝ ጣሪያ ላይ ነፀብራቁን አላይ እያለ ይኖራል። በዳቦ አይሁን እንጂ ግድ የለም በሆነ ነገር አፌን አብሱልኝ አደራ!

ሰሞኑን በደርግ ጊዜ ሰላሳ አምስት ሺሕ ብር ወጥቶበት የተሠራ ቤት በኢሕአዴግ 4.5 ሚሊዮን ብር አውጥቶ አሻሻጥኩ። እንግዲህ በሕገ መንግሥቱ ላይ በግልጽ በሠፈረላችሁ የመናገር፣ የመገመት፣ የማጣጣል፣ የማሞካሸት መብታችሁን ተጠቅማችሁ ይህን የዋጋ ልዩነት ሲሻችሁ በኑሮ ውድነት፣ ሲሻችሁ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ውጤት መመዘን ትችላላችሁ። የእኔ ሥራ መደለል ነዋ። በነገራችን ላይ ባሻዬ አንዳንዴ ሲያሾፉብኝ፣ ‹‹በመጨረሻው ዘመን ሰዎች ገንዘብ ወዳድ ይሆናሉ የሚለው ቃል እንዲፈጸም ደላላ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፤›› ይሉኛል። ባሻዬ ናቸውና ስቄ ዝም እላለሁ። የቅርብ ሰው እኮ ቢደፍረንም አናመርበትም። አይደል እንዴ? ወይስ ይኼም ድሮ ቀረ? አዎ! ይኼም ድሮ ቀርቷል በሚለው ቢጠቃለል ይሻላል።

ምክንያቱማ ይኼንን አሻሻጥኩት ያልኳችሁ ቤት እናትና ልጅን ያጣላ ስለሆነ ነው። ልጅ እናት ገና በቁም ሳለች ‘ሞተሽ እስክወርስ መታገስ አልችልምና ቤቱ ይሸጥ’ አለ። እናት ይኼን ሲሰሙ ‘ስትሮክ’ መታቸውና ‘ፓራላይዝድ’ ሆኑ። ዘመድ አዝማድ በእናትና ልጅ መሀል ጣልቃ አንገባም አለ ነው ሲባል የሰማሁት። ስሰማ ኧከከከከ! ድንቄም ጨዋነት እቴ ከማለት የዘለለ የትችት ቃል አዕምሮዬ ማምረት አቃተው። ‹‹ስምንተኛው ሺሕ ግን ይኼን ያህል ‘ነጌቲቭና ፖዘቲቭ’ እስከማንለይ ያምታታናል ይላል ፍካሬ ኢየሱስ?›› ብዬ ባሻዬን ብጠይቃቸው፣ ‹‹ኔጌቲቭና ፖዘቲቭ ምንድነው?›› ብለው በምፀት መልሱን ሰጡኝ። ቤቱም ተሸጠ። በሰማሁት ነገር እየተረበሽኩ በማሻሻጥ ተግባር ተሳትፌ ከጨረስኩ በኋላ በስውር ትንቢት ማስፈጸሜ ተገለጸልኝ። ሰማይና ምድር እንኳንም ደላላ ባለበት አልተፈጠሩ ስትሉ ሰማሁ ልበል?!

ካለፈ በኋላ እየጮኸ የሚረብሸኝን ህሊናዬን ለመሸሽ ቤት መዋል ጀመርኩ። ማንጠግቦሽ ሁኔታዬ ሁሉ ደስ አላላትም። ከፕሮፌሽኖች ሁሉ የሚሰቀል ነገር የሌለው ደላላ ያደረገኝ መጨረሻህ ምን ይሁን ብሎ ነው እያልኩ ስቃዥ ለካ ሰምታኛለች። ኳስ ተጫዋች ጫማ ይሰቅላል። ቦክሰኛ ጓንቱን ይሰቅላል። ደላላ ምን ይሰቅላል ብዬ ጠላት ይሁን ወዳጄ በቅጡ የማለየውን አንድ ባልደረባዬን ብጠይቀው፣ ‹‹ራሱን ይሰቅላል፤›› ብሎ ወደ ሥራዬ እንድመለስ እልህ እስካሲያዘኝ ቀን ድረስ ተኝቼ እየዋልኩ ተኝቼ እያደርኩ ሰነበትኩ። ‘ምቀኛ አታሳጣኝ’ የሚባለው ለካ የመኖር ጉጉታችን ነዳጅ ማቀጣጠያ ስለሚሆነን ነው ብዬ ራስህን አጥፋ ብሎ ለመከረኝ ባልደረባዬ ሳጫውተው፣ ና አንድ ነገር ላሳይህ…›› ብሎ ይጎትተኝ ጀመር።

መውጣትና መግባት በተውኩባቸው በእነዚያ ጥቂት ቀናት የምሥራች አለኝ ባይ የመንገድ ሰባኪ ለካ ሠፈራችን ተቆጣጥሮት ኖሯል። ሕዝብ ተሰብስቦ ያደምጠዋል። ‹‹ይዘንባል! ይዘንባል! በቅርቡ ይዘንባል!›› ይላል። የተማረረው ወገኔ ‹‹እልል…›› ይላል። ይኼኔ አንዱ፣ ሦስት ቀን ሙሉ ሰማንህ። ይዘንባል ትላለህ። ምንድነው የሚዘንበው?›› ቢለው ሰውየው፣ እሳት!›› ብሎ ቁጭ። በመልካም አስተዳደር ዕጦትና በወበቅ የተማረረው ወገኔ ይኼን ሲሰማ አሁንስ ምንድነው እየዘነበብን ያለው? እያለ ተበታተነ። ወደ ባሻዬ ልጅና ወደ እኔ እያየ፣ ‹‹በአጭሩ ምን ልልህ ፈልጌ መሰለህ? በአየቅጣጫው  የጥፋት ወሬ ስለነገሠ ሰምተህ እንዳልሰማህ ኑር ብዬ ነው፤›› አለኝ። ለሰባኪው ጀርባችንን ሰጥተን ስንጓዝ ‹‹የምር አትጣሉ፣ የምር አትኑሩ፣ የምር አትጥገቡ፤›› ሲል እሰማለሁ። አጥብቀው ከያዙት ለካስ ፍቅርም ሞት ነው ሲባል ሰምተን የላላነው አንሶ ይኼ ሲጨመርብን ደግሞ አስቡት። አይዟችሁ የምር አታስቡ አላለም ሰባኪው!

ታዲያላችሁ ዓለምና ታሪኳን እያሰብኩ መንገዱን የሞላው ተራማጅ ለዕለት ጉርሱ ፍጅት ገጥሞ ሲራኮት በማየት ፈላስፋ መሆን ሲያምረኝ ስልኬ ጠራ። ‘አንድ አሮጌ ፔጆ መኪናዬን ወዲያ አሽጠህ ገላግለኝ’ የሚለኝ ደንበኛዬ ነው። መኪናዋን ታክሲ አድርጎ ስለሚሠራባት ታክሲ መሥራት የሚፈልግ በቅርቡ በግብርና ለተመረቀ ለሠፈሬ ልጅ ትሆናለች ብዬ ካለሁበት ና አልኩት። መጣ። ልክ እንዳየኝ፣ ‹‹አንበርብር እንደምንም ብለህ በዚህ ሁለት ቀን ውስጥ ገላግለኝና ወደ ቀድሞ የሰላም ሕይወቴ ልመለስ፤›› ብሎ ጉልበቴ ሥር ወደቀ። የቀድሞ ሥራውን ስጠይቀው ባሬስታ እንደነበር አጫወተኝ። ‹‹ታዲያ ተቀጥሮ ከመሥራት የራስ አይሻልም?›› ስለው ደግሞ፣ ‹‹እኔም መስሎኝ ነበር። ግን በሁሉም በኩል ጨረሰችኝ…›› ብሎ ኤክስፓየርድ ያደረገችውን መኪናውን ጠቆመኝ። ‹‹እሠራለሁ ለእሷ ነው። እሠራለሁ ጋራዥ ነው። ከሰው ጋር ከመዳረቅ ብዬ የራሴን ሥራ ብጀምር ከብረት ጋር መታገል ሆነ ሕይወቴ…›› እያለ ብዙ ተማረረብኝ።

ከመኪናዋ ታሪክ የእሱ የሕይወት አተያይ መስጦኝ ዝም ብዬ ሳዳምጠው፣ ‹‹በዚህ ዓለም ላይ ስትኖር የሚሳካልህ ስለተቀጠርክ ወይም ቀጣሪ ስለሆንክ አይደለም። ስላላገጥክ ብቻ ነው፤›› ብሎኝ አረፈው። ‹‹ማለት?›› ስለው፣ በቃ ስታመር አይሳካልህም። ስታሾፍና ቀለል አድርገህ ሕይወትን ስትመራ በነፈሰው ስትነፍስ አንድ መላ አይጠፋም። መስሎን ከስንት ነገር ታቀብን። አልሆነም ግን። ዛሬ የበለጡን ዛሬ ዕድሜያቸው የረዘመው ቀለል ፈታ ብለው ነገን ሳያስቡ የኖሩት እንጂ እኛ አይደለንም፤›› ሲለኝ፣ ‹‹በል በል ወንድሜ የተገናኘነው እኮ አንተ መኪናህን ልትሸጥ፣ እኔ ደግሞ ላሻሽጥልህ እንጂ ገልቱዎችን ልናበረታታ ታታሪዎችን ልናዳክም አይደለም፤›› ብዬ ፋይሌን ዘጋሁ። ታዲያ በምን አፌ ነገ ጉቦኛና ፀረ ሕዝብን ልገስጽ ነው? ሰው በገዛ እጁ እጁን ማሳሸጉ ሳያንሰው አፉን ያሳሽጋል? ከዚያ ዴሞክራሲን ለማማት? ወቼው ጉድ!

በሉ እንሰነባበት። እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ ተጉዘን አንድ አንድ እያልን ነው። አንድ ወጣት ልጅ ሰማይ ቢወድቅ ክንዱ እንደ ባላ መሀል ገብቶ መሸከም የሚችል፣ ‹‹በፈጠራችሁ ቸግሮኝ ነው፤›› አለን። ልመና መሆኑ ነው። ‹‹አንተን የመሰለ ልጅ ሲለምን አያሳዝንም? ለምን አትሠራም?›› ሲለው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሥራ እኮ ያደክማል…›› ብሎ መለሰለት። ጣጣ አለው እንዴ? የሕዝብ መንገድ ላይ ቆሞ ድሮስ ማን ጣጣ ይኖረዋል አልተባባልንም? ታዲያስ! ‹‹እንዲያው የምናየውና የምንሰማው ቀልድ ብቻ ሆነ?›› ስለው የባሻዬን ልጅ፣ ‹‹ምን ታደርገዋለህ? ያው የሕዝብ መድረክ ላይ…›› ይለኛል። እንዲያ ሲለኝ በግጥም አንድ ያላቅሙ ልተንትን ብሎ ለግጥም የኳስ ምሳሌ ሲሰጥ መስማቴ ትዝ አለኝ። ወዲያው ለባሻዬ ልጅ ስነግረው፣ ‹‹ሚዲያውን፣ መንገዱንና ንግዱን ቀልደኛ ነግሦበት ለጠላት ታልፋ የተሰጠች ከተማ መስላለች አገራችን፤›› አለኝ። ልብ ብዬ ባስተውል እውነቱን ይመስላል።

ግን ለምንድነው የሕዝብ የሆነ ነገር ላይ ማንም እየወጣ ሲቀልድ ዝምታ የበዛው? በእውቀትና በክህሎት ያልበቃ ሰው አስቀድሞስ እንዴት ኃላፊነትን በማጉደል ይጠየቃል? እዚህ የገነባነውን እዚያ እየናደ ዓይናችን እያየ ጣት ከመቀሳሰር የምንታቀበውስ መቼ ነው? መቼ ነው ሲበዛብኝ ወደ ባሻዬ ልጅ ዞርኩና፣ ‹‹መቼ ነው ዛሬ ነው፣ ነገ ነው አገሬን የማየው?›› እያልኩ አንጎራጎርኩ። ‹‹አገርህ መስለኸኝ አሁን…›› ሲለኝ፣ ‹‹የለም ያቺ ኩሩዋ ኢትዮጵያ፣ የይድረስ የይድረስ የማታውቀው፣ እውቀትና አዋቂነትን የምታከብረው፣ ያለበደል የሚያተርፍ ነጋዴ የምታፈራው ያቺ ኢትዮጵያን ነው የምልህ…›› ስለው፣ ኦ! ኦርጋኒክ ኢትዮጵያን ማለትህ ነው?›› አለኝ፡፡ በእርግጥም መልሱን አግኝቶታል፡፡ እኔ ግን ጉልበተኛ፣ ጨካኝ፣ ዘራፊ፣ አስመሳይና አድርባይ የሌሉባት የትጉኃን አገር ትናፍቀኛለች፡፡ ለዚህ ደግሞ ከመወነጃጀል ይቅል ይቅር ባይነት ይቅደም ብንልስ? ለጊዜው ደመና ባይኖርም መዝነቡ አይቀርም፡፡ መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት