Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጾሙ ማዕድ

የጾሙ ማዕድ

ቀን:

ዓቢይ ጾም ከተጀመረ ሁለት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በአጽዋማት ወቅት ደንበኞች ከሚበዙበት ቦታዎች አንዱ በሆነው አትክልት ተራ የተገኘነው ማልደን ነበር፡፡ ለወትሮውም በሸማቾች ተጨናንቆ መተላለፊያ እንኳን ለማግኘት የሚያስቸግረው የአትክልት ተራ ጐዳና በልዩ ልዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች ተሞልቷል፡፡ በመጋዘኖቻቸው ምርቶቹን ያቀረቡ፣ በችርቻሮ መንገድ ላይ የሚሸጡትም ገዢዎችን ይሻማሉ፡፡ ከአዲስ አበባ የአትክልትና ፍራፍሬ ተቀዳሚ ገበያዎች አንዱ በሆነው አትክልት ተራ የሸማቾች ቁጥር በጾም ወቅት ይጨምራል፡፡ ለቤት ውስጥ ፍጆታም ይሁን ለሽያጭ የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች በተለይም እንዳሁኑ በዓቢይ ጾምና በፍልሰታ ጾም በስፋት ይሸጣሉ፡፡

አቶ ሲሳይ አርጋው የአትክልት ምርቶች ማከፋፈያ መጋዘን ኃላፊ ነው፡፡ ያገኘነው ከሌሊት ጀምሮ የነበረውን የመጋዘኑን ወጪና ገቢ ሲያሰላ ነበር፡፡ ‹‹አትክልት ተራ ሁሌም ብዙ ገዢ ቢኖርም በጾም ወቅት ይጨምራል፤ ፍላጐቱ ሲጨምር እኛ የምናመጣው ምርትም በዛው ልክ ያድጋል፤›› በማለት ሰሞነኛውን ገበያቸውን ይገልጻል፡፡

ኃላፊው እንደሚለው፣ በጾም ወቅት የሚበሉ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ፈላጊያቸው ሲበዛ ዋጋቸው የሚጨምርበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡ በእርግጥ ዋጋ የሚጨምርባቸው ሌሎችም ምክንያቶች አሉ፡፡ ምርት በብዛት የሚገኝበት ወይም የሚጠፋበት ወቅት ላይ ዋጋ ይጨምራል፡፡ ‹‹በጾም አብዛኛው ኅብረተሰብ የሚያተኩረው በጾም ምግቦች ላይ በመሆኑ ምርቶቹን የሚያቀርቡልን ሰዎች የፍላጐቱን መጨመር ተከትለው መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ ያደርጋሉ፡፡ ጾም ተፈቶ የሰው አመጋገብ ሲለወጥ ደግሞ ዋጋው ይቀንሳል፤›› ይላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ሲሳይ እንደሚለው፣ በጾም ወቅቶች የጾም ሕግጋት ያሏቸው ሃይማኖቶችን የሚከተሉ ብቻ ሳይሆኑ የማይከተሉም ወደ ጾም ምግቦች ሲያዘነብሉ ይስተዋላል፡፡ ይህንን ተከትሎም ሻጮች የተለያዩ የጾም ምግቦች ያዘጋጃሉ፡፡ ከአትክልት ቤቶች በተጨማሪ በፍስክ ምግቦች የሚታወቁ ቤቶችም ወደ ጾም ምግቦች ፊታቸውን ያዞራሉ፡፡

‹‹ልዩ የጾም ብፌ ጀምረናል››፣ ‹‹የጾም ምግቦች እዚህ ያገኛሉ›› የሚሉና ሌሎችም ተመሳሳይ መልዕክቶች ያዘሉ ማስታወቂያዎች ማንበብ የተለመደ ነው፡፡ ለጾም በሚዘጋጁ ምግቦች ዕውቅናን ያተረፉ ቤቶችም በየጊዜው አዳዲስ የጾም ምግቦች እያሰናዱ በምግብ ዝርዝራቸው ያካትታሉ፡፡ የጾም ምግቦችን በየቤታቸው እያዘጋጁ የሚመገቡም ብዙዎች ናቸው፡፡

የጾም ወቅት በጾም ብቻ የጾም ምግቦችን ከሚመገቡ ሰዎች ባሻገር ሙሉ በሙሉ አትክልት የሚመገቡ (ቬጂቴሪያን) የሆኑ ግለሰቦች ልዩ ልዩ የጾም ምግቦችን እንዲያገኙም ያስችላቸዋል፡፡ ለወትሮው በብዛት ከሚዘጋጁት ታዋቂ የጾም ምግቦች በየዓይነቱና ሽሮ በተጨማሪ እንደ ሱፍ ፍትፍት፣ ተልባ፣ ቲማቲም ቁርጥ፣ ስልጆና ህልበት ሌሎችም ምግቦች ይገኛሉ፡፡

አቶ ሲሳይ፣ አትክልት የሚመገቡ የሆኑ እንዲሁም አትክልት ነክና ሥጋ ነክ ምግቦችን አመጣጥነው የሚመገቡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣ ለገበያ የሚያቀርቧቸውን ምርቶች እንዲጨምሩ እንዳደረጋቸው ይናገራል፡፡ አትክልት ነክ ምርቶችን የሚያቀርቡ ቤቶች መበራከትም ከፍላጐቱ መጨመር ጋር የተያያዘ እንደሆነ ያምናል፡፡ እነዚህ ቤቶች ከአዘቦት ቀን በበለጠ ጾም ላይ ሥራ ሲበዛባቸውም ይስተዋላል፡፡

እሱም በተለይ በጾም ወቅት የጾም ምግቦች የሚያቀርቡ ቤቶች ተጠቃሚ ነው፡፡ ከአትክልት ተመጋቢዎች በተጨማሪ የሌሎች ሰዎችም አመጋገብ በጾም ወቅት መለወጡ ከጤና አንፃር ጠቀሜታ እንዳለው ያምናል፡፡ ምግቦቹ ከጾም ወቅት ባለፈ በሌሎች ወቅቶችም በስፋት ቢቀርቡና ተጠቃሚዎችም ከሥጋ ነክ ምግቦች ጋር እያመጣጠኑ ቢመገቡ መልካም ነው ይላል፡፡ ‹‹በአትክልት ተራና በምግብ ቤቶች የሚበራከተው የጾም ምግቦች ሸማች በሌላ ወቅትም ቢኖር ተጠቃሚ ይሆናል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

ወ/ት ትርሀስ ካህሳይ የሀሌታ ባርና ሬስቶራንት ባለቤት ናት፡፡ በጾም ወቅት ልዩ ልዩ የጾም ምግቦችን የሚያቀርበው ሀሌታ፣ ቦሌና 22 አካባቢም ይገኛል፡፡ በዓቢይና ፍልሰታ ጾም ወቅት የፍስክ ምግቦችን አያዘጋጁም፡፡ የጾም ምግቦች ዝግጅት ከፍስክ ምግቦች ስለሚከብድ የሠራተኛ ቁጥር ይጨምራሉ፡፡

ባለቤቷ እንደምትናገረው፣ ላለፉት አራት ዓመታት የቤቱ የጾም ምግቦች በተጠቃሚዎች ስለታወቁ የጾም ወቅት ደንበኞቿ ብዙ ናቸው፡፡ እሷም በየዕለቱ የተለያዩ የጾም ምግቦች በማዘጋጀት ታስተናግዳለች፡፡ በቅርቡ ሀሌታ በተገኘንበት የምሳ ሰዓት ብዙ ተጠቃሚዎች በየዓይነቱና ቲማቲም ቁርጥ ሲመገቡ ተልባና ሱፍ ብጥብጥ ሲጠጡም አስተውለናል፡፡ አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች በአካባቢው ባሉ መሥሪያ ቤቶች የሚሠሩና ረጅም ጊዜ የምታውቃቸው ደንበኞቿ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡

ደቀቆ፣ ህልበት፣ ተልባ፣ ድርቆሽ ፍርፍርና ጐመን ክትፎ በጾም ወቅት ብዙ ተጠቃሚ እንዳላቸው ትገልጻለች፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚዘወተሩ ምግቦችን (ለምሳሌ ደቀቆ መቐለ) ስታቀርብ ደንበኞቿ እንዲቀምሱ ታደርጋለች፡፡ ስለምግቦቹ ምንነትና አዘገጃጀት የሚጠይቋትም አሉ፡፡ ‹‹በጾም ወቅት የፍስክ ምግብ የማይመገቡ ሰዎች ወደኛ ስለሚመጡ ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ የፍስክ ምግቦች ለማዘጋጀት ቢቀሉም ዋጋቸው ከፍተኛ ስለሆነም የጾም ምግቦች የተሻሻለ ገቢ ያመጣሉ፤›› በማለት ትገልጻለች፡፡ የጾም ምግቦች ዝግጅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው አያይዛ ትናገራለች፡፡ ከፍስክ ምግቦች አንፃር የጾም ምግቦችን ማዘጋጀት የሰው ኃይልና ጊዜም ይጠይቃል፡፡ የተለያዩ ዓይነት የጾም ምግቦችን ማዘጋጀትም ቀላል አይደለም፡፡ ዝግጅቱ ቢከብድም የጾም ወቅት ከሌላው በተለየ አስደሳች እንደሆነ ትገልጻለች፡፡

በጾም ወቅት የአትክልት ተራና እንደ ሀሌታ ያሉ ቤቶች ደንበኛ የሆኑት አቶ ባልቻ መንገሻ የሚሠሩት መገናኛ አካባቢ ነው፡፡ ምሳ ሰዓት ላይ ከወዳጆቻቸው ጋር በጾም ምግቦች ታዋቂ ወደሆኑ ቤቶች ጐራ ይላሉ፡፡ በሥራ ምክንያት ወደ ቃሊቲ፣ መርካቶ፣ ሣር ቤትና ሜክሲኮ አዘውትረው እንደሚሄዱና በየአካባቢው ጥሩ የሚባሉ ቤቶች ደንበኛ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ባለቤታቸው የወር አስቤዛ ለመግዛት ወደ አትክልት ተራ ሲሄዱ የሚያደርሷቸው አቶ ባልቻ፣ ‹‹በጾም ወቅት ከአትክልትና ፍራፍሬ በብዛት እንሸምታለን፤›› ይላሉ፡፡

አቶ ባልቻ የጾም ምግቦችን በልዩ መንገድ የሚያዘጋጁ ቤቶች መበራከታቸው መልካም ቢሆንም በምግብ አዘገጃጀት ረገድ ንጽህናቸውን የማይጠብቁ እንዳሉም ይናገራሉ፡፡ የማይበስሉ የጾም ምግቦች ለከባድ በሽታ እንደሚያጋልጡና እሳቸውም አምና በፍልሰታ ጾም በበሉት ቲማቲም ቁርጥ ሳቢያ ታመው እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ እንደ ሰላጣ ያሉ ቅጠላ ቅጠሎችና ሌሎችም የጾም ምግቦች አሠራር ንጽህና ትኩረት እንዲቸረውም ያሳስባሉ፡፡

እንደ እሳቸው ሁሉ ለጾም ምግቦች ዝግጅት ጥንቃቄ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጡት የጣይቱ ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አያሌው ታደሰ ናቸው፡፡ በሆቴሉ በጾምና በፍስክ ወቅትም የሚዘጋጅና ቬጋን ብፌ ወይም የጤና ምግብ የሚባል ብፌ አለ፡፡ አብዛኞቹ ምግቦች አትክልት ነክ ናቸው፡፡ ሰላጣ፣ ካሮት፣ የጥቁር ጤፍ ዳቦ፣ አትክልት የተቀላቀለበት መኮረኒ፣ የምስር ፍትፍትና ሌሎችም ዓይነቶች ይቀርባሉ፡፡ ለጾም ምግቦች የሚሆኑ አትክልትና ፍራፍሬዎች ከሚገዙበት ጊዜ ጀምሮ በሚዘጋጁበትና በሚቀርቡበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ ይናገራሉ፡፡ በዝግጅት ወቅት አትክልት ፍሬሽ እንዲሆኑ በማድረግና የሚደባለቁትን ንጥረ ነገሮች በማመጣጠን ረገድም እንደሚጠነቀቁ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የጤና ብፌ እስካልን ድረስ ከዓመት ዓመት መቋረጥ የለበትም፡፡ ሰዎች ይህን አመጋገብ ከጾም ውጪ ቢለምዱትም መልካም ነው፤ አትክልት ማዘውተር ለራስ ሐኪም እንደመሆን ነው፤›› ይላሉ፡፡

ብዙ ተጠቃሚዎች በምሳ ሰዓት ወደ ሆቴሉ እንደሚያመሩ የሚናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የጾም ወቅት ደንበኞቻቸው እንደሚጨምሩ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ብዙዎች በጾም ወቅት ብቻ ሳይሆን ሌላ ጊዜም ከጨው፣ ከቅባትና ከሥጋ ነፃ ወደሆኑ ምግቦች እያመዘኑ ነው፡፡ ተጠቃሚዎችም አትክልት ነክ ምግቦችን ደስተኛ ሆነው ይመገባሉ፤›› ይላሉ፡፡ ደንበኞች ወደ ጤና ብፌ እንደሚያደሉም ያክላሉ፡፡

በጾም ወቅት የተለያዩ ምግቦችን ቤታቸው እያዘጋጁ የሚመገቡ ሰዎች ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ የተለያዩ ዓይነት ግብአቶች ይጠቀማሉ፡፡ ከአኩሪ አተር የሚዘጋጀው ቴስቲ ሶያ በጾም ወቅት ጥቅም ላይ ከሚውሉ ምግቦች መሀከል ይጠቀሳል፡፡ ቴስቲ ሶያን ከቲማቲም፣ ቃሪያና ሽንኩርት ጋር በማብሰል አልያም ከሩዝና መኮረኒ ጋር የሚጠቀሙም አሉ፡፡ በድርጅቱ በሽያጭና የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የምትሠራው ወ/ሮ ኤልሳ ሰይፉ እንደምትናገረው፣ እንደ ቴስቲ ሶያ ጾም የሌላቸው ምግቦች በስፋት ከሚሸጡበት ወቅት አንዱ የዓቢይ ጾም ነው፡፡

‹‹በጾም ወቅት የሽያጭ መጠናችን ይጨምራል፡፡ ተጠቃሚዎች ስለ ቴስቲ ሶያ አሠራር እየደወሉም ይጠይቁናል፤›› ትላለች፡፡ ብዙዎች ተመጣጣኝ ምግቦችን ከዓመት እስከ ዓመት ቢጠቀሙም ጾምን በማስታከክ አመጋገባቸውን የሚያስተካክሉም አሉ፡፡ ቀደም ካሉ ጊዜያት ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት የጾም ምግቦች በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚዘወተሩና እነዚህ ምግቦች በሌሎችም አካባቢዎችም እየተስፋፉ መምጣታቸው መልካም እንደሆነ ታክላለች፡፡

ወ/ሮ ሙሉነሽ አበጀ የጾም ወቅትን ሙሉ በሙሉ ቤታቸው በመመገብ ከሚያሳልፉ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ እሷና ባለቤቷ ከቤታቸው ውጪ በሚሠሩ የጾም ምግቦች አዘገጃጀት ስለማይተማመኑ ቤታቸው ይበላሉ፡፡ ምስር ክክ፣ አተር፣ ሽንብራ ዓሳ፣ ጐመን፣ ፎሶሊያ፣ ስልጆና ጥቅል ጐመን ከሚያዘወትሯቸው ምግቦች መሀከል ናቸው፡፡ ‹‹የበሰሉ የጾም ምግቦች ከቤት ውጪ የምንበላባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም እምብዛም አይደሉም፡፡ ያልበሰሉ ምግቦች ግን ከቤት ውጪ ፈጽሞ አንጠቀምም፤›› ትላለች፡፡ የጾም ምግቦች ከሚያቀርቡ ትንንሽ ሽሮ ቤቶች ጀምሮ እንደ ክትፎ ቤቶች ያሉና በፍስክ ምግብ የሚታወቁ ቤቶች የጾም ምግብ ማቅረባቸው ለተጠቃሚ ጥሩ መሆኑን ግን ትስማማበታለች፡፡

በጾም ምግቦች ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሥርዓተ ምግብ ባለሙያዋ ዶ/ር ዘላለም ደበበ፣ የጾም ምግቦች ከጤና አኳያ የጐላ ጠቀሜታ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ የፍስክ ምግቦች የራሳቸው የሆነ ጥቅም ቢኖራቸውም ቅባት ነክ ነገሮችን መቀነሱ ጤናማ ያደርጋል፡፡ በተያያዥም በጾም ወቅት የሚበሉ ምግቦች ጤናማ ቢሆኑም ከጾም ውጪ ባሉ ወቅቶች ከሥጋ ነክ ምግቦች ጋር ማመጣጠን አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

በይበልጥም ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራስን በመከላከል ረገድ ተጠቃሽ የሆኑ አትክልት ነክ ምግቦችን ከማዘውተር በተጨማሪ የጾምና የፍስክ ምግቦችን አመጣጥኖ መመገብ በጤና ባለሙያዎች እንደሚመከር ዶ/ር ዘላለም ይገልጻሉ፡፡ የጾም ምግቦች ዝግጅት ላይ መወሰድ ያለበትን ጥንቃቄም ዶክተሯ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሁሉም ዓይነት ምግቦች በጥንቃቄ መሠራት አለባቸው፡፡ የፍስክ ምግቦች በንጽህና ካልተሠሩ ለከፋ አደጋ ያጋልጣሉ፡፡ የጾም ምግቦችም እንደዚሁ ናቸው፡፡ የጾም ምግቦች ቶሎ ሊበላሹ ይችላሉ፡፡ ፍሬሽ እንደሆኑ ተዘጋጅተው ቶሎ ጥቅም ላይ ካልዋሉ ይበላሻሉ፡፡ በንጽህና መቅረብና መያዝም አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡

የሃይማኖት ሕግጋትን በመከተል ከሚጾሙ ሰዎች በተጨማሪ በተለያየ ወቅት በራሳቸው ፈቃድ በተለያየ ምክንያት የሚጾሙም አሉ፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በጾም ወቅት የሰውነት የኮሌስትሮል መጠን ይቀንሳል፡፡ የተከማቸ ፋት ይቃጠላል፡፡ የደም ዝውውር ይጨምራል፡፡ ካንሰርና አልዛይመር ለመሰሉ በሽታዎች ተጋላጭነትን ከመቀነሱ ባሻገር ለአእምሮ እንቅስቃሴ ፍጥነትም እንደሚረዳ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ጾምና የጾም ምግቦች በጥምረት ለዚህ ውጤት እንደሚያበቁም ተመልክቷል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...