ሰሞኑን ለፓርላማ የቀረበው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ከሰማሁት አንድ አሳዛኝ ድርጊት ጋር ስለተገጣጠመብኝ፣ ይህንን ገጠመኝ ለመጻፍ አብቅቶኛል፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴርን ህልውና ያሳጣል የተባለው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ምሥረታ ዜናን ስሰማ ነገሩ ግራ ቢያጋባኝም፣ ነገር ግን የሚመሠረተው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጠንካራ አመራር በነፃነት ሥራውን ካላከናወነ ውጤቱ ‹‹ውኃ ቢወቅጡት እንቦጭ›› እንዳይሆን ያሠጋኛል፡፡ ለዚህ ሥጋቴ ደግሞ የፍትሕ ሥርዓቱ ብልሽትሽት ማለትና የተጠያቂነት መጥፋት ትክክለኛ መልስ ይሆናል፡፡ ሕዝብ ፍትሕ አጥቶ እሪሪሪ እያለ ባለበት በዚህ ወቅት፣ መንግሥት የፍትሕ ሚኒስቴር ሙሉ ሥልጣን ለሚቋቋመው አዲሱ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መስጠት መፈለጉ የችግራችንን ግዝፈት ያመላክታል፡፡ እስቲ ወደ ገጠመኜ ልውሰዳችሁ፡፡
ጓደኛዬ የሚሠራው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ በትምህርቱም ሆነ በሙያው፣ እንዲሁም በሥነ ምግባሩ የተመሠገነው ይህ ወጣት ጓደኛዬ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለሁለት ዓመታት ያህል ሠርቷል፡፡ አሁንም እየሠራ ነው፡፡ በቅርቡ ስለ ሥራው ስንወያይ በክፍለ ከተማው ውስጥ የሚታየውን የመልካም አስተዳደር መጓደል፣ የአንዳንድ ሹማምንትን ማናለብኝነትና የሕዝቡን በደል በምሬት ነገረኝ፡፡ በቅርቡ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት በአካባቢው ባለሀብት በሆኑ ሁለት ግለሰቦች አቤቱታ ይቀርብለታል፡፡ ከስድስት ዓመት በፊት እነሱ ዘንድ ትሠራ የነበረች የፋይናንስ ሠራተኛ ከደንበኛ ለተሰጣት ትዕዛዝ በፋይናንስ ሕጉ መሠረት ደረሰኝ ትቆርጣለች፡፡ ሥራውም ይጀመራል፡፡ በዚህ መሀል እሷ ሌላ የተሻለ ሥራ ታገኝና መሸኛዋን ተቀብላ ትሰናበታለች፡፡
ሠራተኛዋ የቆረጠችው ደረሰኝ ለአገር ውስጥ ገቢ መሥሪያ ቤት ጠቀም ያለ የተጨማሪ እሴት ታክስ የሚያስገኝ ሲሆን፣ በዓመታዊ ግብር ወቅትም መንግሥት ጠቀም ያለ ገቢ ያገኛል፡፡ ባለሀብቶቹ ግን ከስንትና ስንት ዓመታት በኋላ ለመንግሥት ያላግባብ ግብርና መቀጮ እንድንከፍል አድርጋናለች በማለት አቤቱታ አቅርበው፣ ግለሰቧ በፖሊስ ተፈልጋ ትያዛለች፡፡ ለአሥር ቀናት ያህልም ታስራ ምርመራ ይደረግባታል፡፡ በኋላም ምርመራው ሲያልቅ ፍርድ ቤት ቀርባ ክርክሩ ሲጀመር በነፃ ትሰናበታለች፡፡ ፍርድ ቤቱ ግለሰቧ ለራሷ ሳይሆን ለመንግሥት ገቢ የሚሆነውን ገንዘብ በትክክል ደረሰኝ በመቁረጥ በማስታወቋ ምንም ተጠያቂነት የለባትም ብሎ ነው ያሰናበታት፡፡ ከመነሻውም የክፍለ ከተማው ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ሳያምንበት የተከሰሰችው በማይታወቅ ‹‹የበላይ አካል›› ግፊት መሆኑም ታወቀ፡፡
ጓደኛዬ በቁጭት እንደነገረኝ ግለሰቧ የመንግሥት ሕግ በሚፈቅደው መሠረት ኃላፊነቷን በመወጣቷ ከዓመታት በኋላ ‹‹በበላይ አካል›› ትዕዛዝ ታስራ ከርማ በነፃ ብትለቀቅም፣ አሁን ደግሞ ‹‹ክሱ ተሻሽሎ›› እንደገና ፍርድ ቤት ቀርባለች፡፡ 40 ሺሕ ብር ዋስትና አስይዛ ‹‹ተሻሻለ›› በተባለው ነገር ግን ‹‹በበላይ አካል›› ትዕዛዝ ተከሳ ቀጠሮ ላይ ናት፡፡ ይኼ ‹‹የበላይ አካል›› ትዕዛዝ የሚባለው ኢፍትሐዊና አስመራሪ ተግባር አንዲት የሁለት ልጆች እናትን መከራ እያበላ ነው፡፡ ሕግ አክብራ መንግሥት እንዲጠቀም ባደረገች ‹‹ክስ ተሻሻለ›› ተብሎ ትንከራተታለች፡፡ ስንቶች እናቶችና አባቶች አገር እያጠፉ ባሉ ‹‹የበላይ አካላት›› መከራ ሲያዩ እከ መቼ ዝም ይባላል? መንግሥትስ ቢሆን ሰሞኑን እንዲህ ግራ ግብት እስኪለው ድረስ የሚያሳስበው ይኼ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር አይደለም ወይ? ኧረ በሕግ አምላክ?
ጓደኛዬ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ይህንን ጉዳይ በአስቸኳይ አጣርተው ዕርምጃ ካልወሰዱ መንግሥት እንደሌለ ይቆጠራል ነው ያለኝ፡፡ እኔም በዚህ የተነሳ ነው ይህንን ለመጻፍ የተገደድኩት፡፡ አንድ ዜጋ መንግሥት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ባደረገ፣ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ፍትሕ ቢሮ ራሱ ሳያምንበት ‹‹በበላይ አካል›› ትዕዛዝ እንዴት ክስ ተመሥርቶበት ይሰቃያል? ከላይ የተጠቀሱት አካላት በፍጥነት ተንቀሳቅሰው ስለ ፍትሕ ሲሉ ይህንን ሕገወጥ ተግባር ያስቁሙ፡፡ ‹‹የበላይ አካል›› የተባለውን ግለሰብም ሆነ ቡድን ያጋልጡ፡፡ ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን ይመለከተኛል የሚል ዜጋ በሙሉ እንዲፋረዳቸው እጠይቃለሁ፡፡
መንግሥት በመልካም አስተዳደር ችግሮች ምክንያት ራሱን ለማፅዳትና ሕዝቡን ለመታደግ ላይ ታች ሲል፣ ወደ ኋላ የሚጎትቱት መኖር የለባቸውም፡፡ ሕዝብን ማስከፋት፣ ማበሳጨትና ወደ አመፅ መገፋፋት በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ አንድ ዜጋ ሲከፋውና ያላግባብ ሲወነጀል ለምን መባል አለበት፡፡ በሕግ አንድ ዜጋ ያላግባብ ከሚሰቃይ አንድ ሺሕ ወንጀለኞች ቢፈቱ ይሻላል ይባላል፡፡ አንድ ዜጋ ቢያጠፋ እንኳ ማስተማር እንጂ ድራሹን ለማጥፋት መነሳት ያሳዝናል፡፡ የማንም ሙሰኛ ሥልጣኑን ያላግባብ እየተገለገለ ሕግን ለሕገወጥ ድርጊት ሲጠቀም ማየት ያንገበግባል፡፡ መንግሥት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ኃላፊነቷን የተወጣችውን ይህቺን የልጆች እናት መንግሥት ካልታደጋት ማን ይታደጋት? ጓደኛዬ ግን አንድ ጥሩ ነገር አለ፡፡ ‹‹ይዘገያል እንጂ ሁሉም የእጁን ያገኛል፤›› ነበር ያለው፡፡ በሰው ተስፋ ብንቆርጥ እንኳ መመኪያችን ፈጣሪ መሆኑን ማንም አይዘንጋ እላለሁ፡፡ (ቶማስ ወርቅነህ፣ ከጎተራ ኮንዶሚኒየም)