ፍርድ ቤትን ማሻሻል ፈተና ነው፡፡ ቀልጠፋ ማድረግ፣ ተደራሽ ማድረግ፣ ወጪ ቆጣቢና ፍትሐዊ ማድረግ ፈታኝ ነው፡፡፡ የአገራችን መንግሥትም ይህንን ቀድሞ ተረድቶታል፡፡ በፌዴራልም ሆነ በክልል መፍትሔ ለመስጠት የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ መርሐ ግብሮችን አቅዶ ፈጽሟል፡፡ በአማራ ክልልም እንዲሁ፡፡ በአማራ ክልል መቀመጫ ባህር ዳር የፍትሕ ቢሮ ቤተ መጻሕፍት ያገኘሁት የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ መጽሐፍት የማሻሻሉን አጀንዳ እያሰብኩ ቀልቤን ሳበው፡፡ ግንቦት 2007 ዓ.ም. በታተመው የሕግ መጽሔቱ ቅጽ 1 አቶ ግርማ ጌታቸው የተባሉ ጠበቃ ‹‹በፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም በአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች ያስገኘው ውጤት›› በሚል የጻፉት ጽሑፍ፣ የፍርድ ቤት ማሻሻያው በአማራ ፍርድ ቤቶች ለውጥ ማምጣቱን የሚዳስስ ብቻ ሳይሆን ትኩረት የሚሹ የፍርድ ቤቶች የአሠራር ክፍተቶችን የሚፈትሽ ነው፡፡ ጽሑፉን አንብቤ እንደጨረስኩ በክልሉ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያው ያመጣው ለውጥ አስደሰቶኛል፡፡ ደስታው እኔን ብቻ እንዳይሆን ሥጋት አለኝ፡፡ በጽሑፉ የተገለጡት ለውጦች በእርግጥ የክልሉን የፍርድ ቤቶች አሠራር ይወክላል? በክልሉ የሚሠሩ ጠበቆችና የሕግ ባለሙያዎች ምስክርነት ይደገፋል? እንዲያ ከሆነስ ጸሐፊው አልፎ አልፎ የሚጎበኛቸው በክልሉ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋሉ የመዛግብት ክምችት፣ የባለጉዳዮች መጉላላት፣ የተደራሽነት ማጣት ክልሉን አይገልጹም? የሚሉ ጥያቄዎች በሕሊናዬ ቢነሱም፣ ትክክለኛ ፍርድ የሚሰጠው የክልሉ ነዋሪና በክልሉ የሚሠሩ የሕግ ባለሙያዎች በመሆናቸው በዚህ ጽሑፍ በጸሐፊው የተገለጹትን የማሻሻያ ውጤቶች ሳልገልጽ አላልፍም፡፡ በጽሑፉ ከተገለጹ አመርቂ ውጤቶች በላይ ግን ጸሐፊውን የሳበው አቶ ግርማ ትኩረት የሚሹ በማለት ያቀረቡዋቸውና አሁንም ማሻሻያው ያልፈታቸው የአሠራር ክፍተቶችን ነው፡፡ እነዚህ ክፍተቶች የአማራን ክልል ብቻ ሳይሆን የፌዴራል ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የአገራችንን ፍርድ ቤቶች የሚገልጽ በመሆኑ ለውይይት፣ ለምርምርና ለመነሻ ይሆን ዘንድ የጸሐፊውን ጥናት መሠረት አድርገን በዚህ ጽሑፍ አንዳንድ አንገብጋቢ ጉዳዮችን እንመለከታለን፡፡ አመርቂ ውጤቶቹን እናስቀድም፡፡
አመርቂ ውጤቶች
ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ፕሮግራም በዳኝነት ሥርዓቱ የሚታዩ ሦስት ዋና ዋና ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ነው፡፡ ለሕዝቡ ፍላጎት ፈጣን ምላሽ አለመስጠትና ተደራሽ አለመሆንን መቅረፍ፣ ሙስናና በሥልጣን አላግባብ መገልገልን ማስቀረት፣ እንዲሁም ለፍትሕ ተቋማቱ በቂ በጀት ያለመመደብ አሠራርን ማስተካከል ነው፡፡ ይህን መሠረት አድርጎ እንደ ፌዴራልና ሌሎቹ ክልሎች የአማራ ክልል መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጥናትና ውጤት ተኮር ምዘና ሥርዓት የተገበረ ሲሆን፣ አቶ ግርማ ሦስት ዓበይት ለውጦች በማሻሻያው መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
የመጀመሪያው የክልሉ ፍርድ ቤቶች ቅልጥፍና ተሻሽሏል፡፡ ከዚህ አንፃር የአማራ ፍርድ ቤቶች የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች በባህርይና በውስብስብነታቸው በመለየት፣ በገቢና በወጪ የፍርድ ቤቶቹን የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ በማውጣት እንዲሁም ዳኞች በዕረፍት ጊዜያቸው ጭምር በመሥራታቸው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ችለዋል፡፡ የ2006 ዓ.ም. መረጃ ብንመለከት እንኳን ፍርድ ቤቶቹ ከቀረቡባቸው 571,552 መዛግብት ለ533,740 ያህሉ እልባት ሰጥተዋል፡፡ በዚህ መነሻ መሠረት ‹‹የአማራ ክልል ፍርድ ቤት የማጣራት አቅማቸው ወደ 100% ተጠግቷል፡፡›› እንደ አቶ ግርማ ትንተና የፍርድ ቤቶች የመጨናነቅ ሁኔታ (Conjestion Rate) ለፍርድ ቤቶች የቀረቡ ጠቅላላ መዝገቦች ውሳኔ ካገኙት ጋር ሲነፃፀር ወደ 1% የቀረበ በመሆኑ አመርቂነቱን ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ አቶ ግርማ የፍርድ ቤቱ የዳኝነት አገልግሎት ከወጪ አንፃር አነስተኛ መሆኑ ተጨማሪ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሁለተኛው አመርቂ ውጤት የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት ሲሆን፣ በክልሉ የተዋቀሩት ፍርድ ቤቶች፣ የተዋቀረ ችሎት አሠራርና ጉዳዮችን በፕላዝማ ችሎት መዳኘት ተደራሽነቱና ማጠናከራቸውን ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የፍርድ ቤቶች የአገልግሎት ወጪ የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ መሆኑ ተደራሽነቱን ጨምሮታል፡፡ እነዚህ ወጪዎች ቀጥተኛ ወጪ (ለዳኝነት፣ ለጠበቃ፣ ሰነድ ለማስገልበጥ ወዘተ. የሚወጡ) እና ቀጥተኛ (ሕጋዊ) ያልሆኑ (በሙስና መልክ፣ ለፍርድ ቤት ሠራተኞች፣ ለዳኞች ወይም ለፍትሕ ደላሎች የሚከፈሉ ወጪዎች) በክልሉ እየቀነሱ መምጣታቸውን አቶ ግርማ ይገልጻሉ፡፡
አቶ ግርማ በመጨረሻ የሚገልጹት ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት መዳበርንና በፍርድ ቤት የአሠራር ሥርዓት ለውጥ የተተገበሩትን (የወንጀልና የፍትሐ ብሔር የሥራ ሒደት መደራጀት፣ የቀጠሮ ፖሊሲ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃ) በመጥቀስ የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ አመርቂ ውጤት አምጥቷል፡፡
እነዚህ አመርቂ የተባሉት ውጤቶች በአማራ ክልል መገኘታቸውን ማረጋገጥ ባንችልም፣ ክፍተቶች አለመኖራቸውን አሳምኖ መከራከር አይቻልም፡፡ በፌዴራልና በሌሎች ክልሎች ያለውም ተሞክሮ እነዚህን መደምደሚያዎች አሜን ብለን ለመቀበል እንድንቸገር ያደርጉናል፡፡ በአንድ ጉዳይ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎችን ያለምክንያት መቅጠር፣ የጉዳዮች መብዛትና በፍጥነት አለመጠናቀቅ፣ በሰዓት ተቀጥሮ ሙሉ ቀን ፍርድ ቤት መዋል፣ ለደጋፊ ሠራተኞችና ለዳኞች የሚወጡ ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎች ከመቀነስ ይልቅ መጨመራቸው፣ የፍርድ ቤቶች የመረጃ ተቋማት የማይሠሩ፣ ከቴክኖሎጂው ጋር ያልዘመኑ መሆን ወዘተ. አሁንም ፍርድ ቤቶቻችንን አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና ፍትሐዊ አድርጎ ለመስጠት ፈተና ሆኖባቸዋል፡፡ ለማሳያ ሁለት በዚህ ሰሞን ያስተዋልናቸውን ሕዝባዊ ጉዳዮች እናንሳ፡፡
አንዱ የአማራ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ላይ የሰጠውን የሰላ ትችት ማስታወስ ነው፡፡ ይህንን ውይይት ጸሐፊው በአማራ ክልል ቴሌቪዥን በቀጥታ አይቶታል፡፡ የክልል ምክር ቤቱ አባላት በፍርድ ቤቶች ቅልጥፍና ማነስ፣ የጥራት ችግርና የሙስና መንሰራፋት ላይ ላነሱዋቸው ጥያቄዎች የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ችግሮቹን ለመቅረፍ እየጣሩ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ የችግሮቹን መንሠራፋት አልደበቁም፡፡
ሁለተኛው ማሳያ በዚህ ሰሞን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግቢ ያነበብኩት ማስታወቂያ ነው፡፡ በፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጉቦ በሚቀባበል የሚያሳልጡና የፍትሕ ደላሎችን እንድታጋልጡ የሚል መማፀኛ ነው፡፡ በፍርድ ቤት አገልግሎት ላይ የራሳቸውን ገበያ የፈጠሩ ‹‹የፍትሕ ደላሎች›› መስፋፋታቸውና ፍርድ ቤቱም ለመታገል መጣሩን መግለጹ የሙስናና ብልሹ አሠራር የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ነው፡፡ አንድ ጠበቃ ‹‹ፍርድ ቤት የራሱ የሆኑ ዳኞቹን ሥነ ምግባር ይጠብቁ እንጂ የውጭ ደላሎችን እንዴት ሊቆጣጠር ይችላል፤›› ሲሉ የሰጡት አስተያየት፣ አሁንም ወደ ውጭ መመልከት ችግሩን እንደማይቀርፈው ያሳምናል፡፡
ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች
አቶ ግርማ ጌታቸው የአማራ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ለውጥ ማምጣቱን ቢገልጹም፣ አሁንም የክልሉን ፍርድ ቤቶች ውጤታማነት የሚፈታተኑ በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን አልካዱም፡፡ ጸሐፊው ክፍተቶቹን በጥልቀት የዳሰሱ ሲሆን፣ ችግሮቹ የፌዴራሉንም ሆነ የሌሎቹን ክልሎች እውነታ የሚያሳይ በመሆኑ በአጭሩ ለማቅረብ እንሞክር፡፡
የፍርድ ጥራት መጓደል
የፍርድ ጥራት በቀጥታ ከዳኞች ጥራት ጋር እንደሚገናኝ የሚገልጹት አቶ ግርማ፣ የተሻለ የትምህርት ዝግጅትና የተሻለ ተቋማዊ ግብዓቶች ባሉበት በዚህ ወቅት የጥራቱ መጓደል አሳሳቢ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አቶ ግርማ በክልሉ የሚታየው የፍርድ ጥራት መጓደል ለይግባኝና በሰበር ችሎት በር የሚከፍት፣ የመዝገብ መጨናነቅን የሚፈጥርና የፍርድ ቤቶችን ቅልጥፍና ውጤት የሚያሳጣ ነው፡፡ መቼም ስለ ፍርድ ጥራት መጓደል በዚህ ዘመን ማንሳት ሞኝነት ነው፡፡ ለአብነት የምናገላብጣቸው ፍርዶች የሰበር ገዥ ፍርዶች ሳይቀሩ በሕግ ትንተናና በወሳኝ ፍሬ ነገር ትንተና ብዙ ጉድለት እንዳለ ይነግሩናል፡፡ አቶ ግርማ ለፍርድ ጥራት መጓደል ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ፡፡ የፍርድ ጥራት ከሚጓደልባቸው ውስጣዊ ምክንያቶች መካከል ዳኞች ከውሳኔ ጥራቱ ለብዛቱ አጽንኦት መስጠታቸው፣ የሥነ ሥርዓት ሕጉን መሠረት አድርገው ችሎት የማይመሩ መሆናቸው፣ ዳኞች የሚፈጽሙት የሥነ ምግባር ጉድለትና ዳኞች የፍርድ አጻጻፍ ዕውቀትና ክህሎት ክፍተት ያለባቸው መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለጥራት መጓደል አስተዋጽኦ ካላቸው ውጫዊ ምክንያቶች ውስጥ በአንዳንድ ሕጎች ላይ ክፍተት መኖር፣ የሕግ ትምህርት ጥራት መጓደል፣ ለሕጉ አፈጻጸም አጋዥ የሆኑ ተቋማት በአግባቡ አለመደራጀት፣ የተከራካሪ ወገኖች የአቤቱታ ጥራት መጓደል ይገኙበታል፡፡
አቶ ግርማ ያነሷቸው የፍርድ ቤት ጥራት የመጓደል ምክንያቶች ከዚህም ሊሰፉ ይችላሉ፡፡ ችግሩ ግን አገራዊ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ፍርዶች ዳኞቹ ተመልሰው ሲመለከቱዋቸው እንኳን የማይገቧቸው፣ ለአስፈጻሚ ፍርድ ቤቶች ግልጽ ያልሆኑ፣ እርስ በርስ የሚቃረኑ ሐሳቦች የያዙ፣ ጭብጦችን በከፊል እንጂ በምልዓት የማይተነትኑ ናቸው፡፡
የባለሙያ ፍልሰት መጨመር
አቶ ግርማ የክልሉን መረጃ መነሻ በማድረግ የዳኞች ፍልሰት በብዛት እንደሚስተዋል ይገልጻሉ፡፡ ዳኞች የሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛ መሆኑ፣ ሌላ ሥራ ለመሥራትና ኑሮአቸውን ለመደጎም አለመቻላቸው ከሙያው ከመፍለስ ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ የዳኛ ፍልሰት ጉዳይ ከጥንት ጀምሮ የነበረ የፍርድ ቤቶቹ ችግር ሲሆን፣ የሚመለከታቸው ክፍሎችም ይህንን ችግር ለመቅረፍ የሚወስዱት መፍትሔ ችግሩን ሲቀርፍ አይስተዋልም፡፡ አቶ ግርማ በጫና ምክንያት፣ በሥነ ምግባር ጉድለት ምክንያት፣ በአቅም ማነስ ምክንያት የወጡ ባለሙያዎች ስለመኖራቸው ባይገለጹም፣ ቁጥራቸው ቢያንስም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቅርብ ጊዜያት አስተውለናል፡፡ በኦሮሚያ ፍርድ ቤቶችም በሥነ ምግባር ጉድለት ከሙያው የፈለሱ ብዙ ዳኞች መኖራቸው በየጋዜጣቹ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የቢሮ ችግርና የትራንስፖርት ችግር
ጸሐፊው ያነሱዋቸው ሌሎች የዳኝነት አካሉ ችግሮች የማስቻያ አዳራሾች ችግርና የዳኝነቱን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ የትራንስፖርት እጥረት በክልሉ መንሰራፋቱን ይገልጻሉ፡፡
እንደማጠቃለያ
በአማራ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሕግ መጽሔት ከቀረበው የአቶ ግርማ ጽሑፍ ሦስት በጎ ጎኖችን አስተውያለሁ፡፡ የመጀመሪያው በክልሉ ተግባራዊ የተደረገውን የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ትግበራ መፈተሻቸው ነው፡፡ የሚተገበሩ ግን ጥቅምና ጉዳታቸው፤ ተፅዕኖአቸውና ያመጡት ለውጥ ሳይፈተሹ ብዙ ጥናቶች፣ ፖሊሲዎችና አሠራሮች ሲያልፉ ስለምናስተውል ይህ ፍተሻ በጎ ጅምር ነው፡፡ ሁለተኛ በክልሉ አመርቂ በማለት ያነሷቸውን ነጥቦች በአኃዝና በምክንያታዊ ትንተና ለማቅረብ መሞከራቸው ነው፡፡ በክልሉ የሚሠሩ ባሙያዎች እንዲተቹት፣ እንዲቀበሉት ወይም እንዲነቅፉት መነሻ ይሆናል፡፡ በመጨረሻም ያነሱት ችግር በተለይ ከፍርድ ጥራት መጓደል ጋር የተያያዙት የአማራ ክልል ብቻ ችግር ሳይሆን የሌሎችም ችግር የሆነውን ነጥብ ማንሳታቸው ነው፡፡ የጥራት ጉድለት ባለበት ሁኔታ ቅልጥፍናም ሆነ ተደራሽነት ዋጋ አይኖረውም፡፡ የችግሩ መንሰራፋት ጸሐፊው በመግቢያቸው በአመርቂ ውጤትነት የገለጿቸው በጎ ጅምሮች መሬት ያልረገጡ ለመሆናቸው አስረጂ ነው፡፡
የአማራ ፍርድ ቤቶች ተሞክሮ ግን የሌሎቹንም ገላጭ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶቻችን የፍርድ ጥራት ጉድለት አለባቸው፡፡ የፍርድ ጥራቱ ከሙስና፣ ከችሎታ ማጣት፣ ከመዛግብት ብዛት የተነሳ ያልጠሩ መሆኑ ችግሩን ያከፋዋል፡፡ አቶ ግርማ በአማራ ክልል እንደተገኙ የገለጿቸው የቅልጥፍና፣ የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት፣ የወጪ መቀነስ፣ የተደራጀ የመረጃ ሥርዓት መኖር በሌሎቹ መኖራቸውን ጸሐፊው ይጠራጠራል፡፡ በአማራ ክልል ባለው አጭር ተሞክሮም የአማራ ክልል ፍርድ ቤቶች የቅልጥፍናን ደረጃ፣ 100% የሚደርስ የማጣራት አቅም፣ የፍርድ ቤቶቹን ተደራሽነት እጅጉን ይጠራጠራል፡፡ ሰፊ ጥናት በክልሉ ባለሙያዎች ሲሠራ የምንመዝነው ጉዳይ ነው፡፡ ለማንኛውም አንባቢውም፣ ፍርድ ቤቶችም፣ መንግሥት፣ ባለድርሻ አካላትም ፍርድ ቤቶችን ማሻሻል ፈታኝ መሆኑን ከአማራው ተሞክሮ መረዳት እንደሚችሉ ጸሐፊው ያምናል፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡