Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በካይዘን አማካይነት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ የፋብሪካዎችን ወጪ ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ የጃፓኑን የካይዘን ሥርዓት መተግበር ከጀመረች ጀምሮ በአምራች ኩባንያዎችና በግንባታ ተቋማት በኩል ከዚህ በፊት ለብክነትና ለሌሎች ኪሳራዎች ይዳረግ የነበረውን የአሠራር ችግር በመቅረፍ፣ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ፡፡

በአዲስ አበባ ለሦስት ቀናት በተስተናገደውና ከ12 አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ልዑካን የተሳተፉበትና ‹‹የካይዘን የዕውቀት ልውውጥ ሴሚናር›› የሚል ርዕስ በተሰጠው ስብሰባ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ካይዘን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ታደሰ እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ በሚገኙ ልዩ ልዩ ፋብሪካዎችና ግንባታ ተቋማት በኩል ሲተገበር በቆየው የካይዘን አሠራር ሥርዓት አማካይነት ከዳነው ወጪ ባሻገር፣ አገሪቱ ሁለተኛውን የካይዘን ምዕራፍ በመተግበር በጥራት ቁጥጥር፣ በምርት ሒደት፣ በፖሊሲ ቀረፃና በመሳሰሉት መስኮች ላይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችለው ሁለተኛው የካይዘን ደረጃም ይበልጥ ለውጥ ይጠበቃል፡፡

ከመጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተካሄደው ሴሚናር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከኬንያ፣ ከጋና፣ ከታንዛንያ፣ ከካሜሩን፣ ከቱኒዝያ እንዲሁም ከዛምቢያ የመጡ ተወካዮች በየአገሮቻቸው እየተተገበረ ስላለው የካይዘን ሥርዓት አብራርተዋል፡፡

ከጃፓን የተቀዳውና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣጥሞ በመተግበር ላይ የሚገኘው ካይዘን፣ መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቡ በምርትና አገልግሎት መስኮች ጥራትን ባልተቋረጠ የለውጥ ሒደት ወቅት ማረጋገጥ የሚያስችል ሥርዓት መሆኑ ይነገርለታል፡፡

የመጀመሪያው የካይዘን ደረጃ የሥራ አካባቢን ለምርትና ለአገልግሎት ተግባራት ምቹ እንዲሆን በማድረግ መለወጥ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ የማምረቻ ቁሳቁሶችንና ግብዓቶችን በአግባቡ ለሥራ ምቹ እንዲሆኑ አድርጎ ከማዘጋጀትና ከማስተካከል ጀምሮ ንጽህናና ቅልጥፍናን ማስጠበቅ ዓላማው ነው፡፡ ሁለተኛው የካይዘን ደረጃ ደግሞ ከዚህ ሒደት ላይ ያለ ሆኖ ምርትንና አገልግሎትን በተሻለ የጥራት ደረጃና በጥራት ቁጥጥር ሥርዓት እየተመራ እንዲመረት የሚያስችል ሥርዓት የሚዘረጋበት ነው፡፡ በዚህ መስክ አማካሪ የሚሆኑ ባለሙያዎችን በማስትሬት ደረጃ ማሠልጠን የተጀመረ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ ምሩቃንም ወደ ካይዘን ሥርዓት መቀላቀላቸውን አቶ ጌታሁን አስታውቀዋል፡፡

በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ሦስተኛ ደረጃ የሚባለውን የካይዘን ሥርዓት መተግባር ትጀምራለች ያሉት አቶ ጌታሁን፣ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ለዚህ ደረጃ የሚያግዙ አምስት ባለሙያዎች በካይዘን ሥርዓት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዲያጠኑ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አስካሁን በአምራች ኢንዱስትሪዎች አካባቢ ሲተገበር ከቆየው ባሻገር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስና በሌሎች የአገልግሎት መስኮችም ካይዘን ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ኢትዮጵያ በካይዘን ሥርዓት ትግበራ ከሌሎች አገሮች የተሻለ ውጤት እያገኘች መጥታለች ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ወደፊት ከጃፓንና ከደቡብ ኮሪያ በመቀጠል ሦስተኛ የካይዘን ማዕከል እንድትሆን መታሰቡን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ምሳሌ መሆን የሚያስችላት አቋም ላይ መድረሷንና ለሌሎች አገሮች በካይዘን ያካበተችውን ልምድ ለማካፈል የሚያስችል ብቃት መፍጠሯን ገልጸዋል፡፡ ይህም ቢባል ግን ኢትዮጵያም ሆነች ሌሎች አገሮች የጃፓንን የካይዘን ሥርዓት እንዲሁ ከመቅዳት ይልቅ የራሳቸውን ካይዘን እንዲያጎለብቱ አሳስበዋል፡፡

ጃፓን የምትመራበትን የአሠራርና የማኔጅመንት ፍልስፍና ከአሜሪካ እንደቀሰመች የጠቀሱት አምባሳደር ሱዙኪ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ አሜሪካ ባለሙያዎቿን ወደ ጃፓን በመላክ ስትሰጥ ከነበረው ድጋፍ ካይዘን የተባለውንና ከጃፓኖች የአሠራርና አኗኗር ሥልት ጋር እንዲስማማ የተደረገውን ካይዘንን መፍጠር እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡ በመሆኑም አፍሪካውያንም ለራሳቸው የሚስማማ ሥርዓት በመፍጠር ችግሮቻቸውን መፍታት እንዲችሉ መክረዋል፡፡ ‹‹አፍሪካይዘን›› የሚል ስያሜ ወይም ‹‹ካይዘን በአፍሪካ›› የሚል ስያሜ በመስጠት አፍሪካዊ ቃና እንዲኖረው ማድረግ እንደሚቻል ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

ካይዘን በኢትዮጵያ እንዲተገበር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን በማማከር ተካፋይ የነበሩትና የዕውቁ የኢኮኖሚ ምሁር ጆሴፍ ስቲግሊዝ የሥራ አጋር የሆኑት ፕሮፌሰር ጎ ሺማዳ፣ አፍሪካውያን የአምራች ኢንዱስትሪያቸው ለበርካታ ዓመታት እያሽቆለቆለ በመጣበት ወቅት፣ ኢኮኖሚያዊ ሽግግሩም ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ማቅናት ሲገባው በቀጥታ ወደ አገልግሎት ዘርፉ መግባቱም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ ያቀጨጨው አጋጣሚ ስለፈጠረ፣ ይህንን ሊያቃና የሚችል እንደ ካይዘን ያለ አሠራር መተግበር እንደሚገባ መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች