Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኒው ላይን ሪል ስቴት ቤት አስገንቢዎች መንግሥትን እየተማፀኑ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– መንግሥት ጉዳዩን እየመረመርኩ ነው ብሏል

ኒው ላይን ሪል ስቴት ኤንድ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለው ድርጅት ከ300 በላይ ከሚሆኑ ቤት አስገንቢዎች ጋር የገባውን ውል ሳያጠናቅቅ የሪል ስቴት ግንባታው መስተጓጐሉ እንዳሳሰባቸውና መንግሥት መፍትሔ እንዲያፈላልግላቸው አስገንቢዎች ጠየቁ፡፡

በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ ልዩ ዞን በመልካ ገፈርሳ ቀበሌ አንፎ በሚባለው አካባቢ ግንባታው 300 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት እንደተፈቀደለት በማረጋገጥ፣ ለሪል ስቴት አልሚው በተለያዩ መንገዶች ክፍያ የፈጸሙት የቤት አስገንቢዎች እንደሚገልጹት፣ ከድርጅቱ ጋር የተገባው ውል ተግባራዊ ሳይሆን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ታስረዋል፡፡

ከድርጅቱ ሪል ስቴት ለመግዛት እስከ 400 የሚደርሱ ደንበኞች መመዝገባቸውንና ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አብዛኛዎቹ ቅድመ ክፍያ የከፈሉ ቢሆንም፣ ይገነባሉ ከተባሉት ከ300 በላይ ቤቶች ውስጥ 30 ቤቶች ብቻ ከመጀመራቸው ውጭ የሚታይ ነገር አለመኖሩን የቤት አስገንቢዎቹ ተወካዮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ዲዛይን መሠረት በቦታው ላይ ይገነባሉ የተባሉት ቤቶች 600 ናቸው፡፡ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ ከተቋረጠ ከሰባት ወራት በላይ እንደሆነውም ተናግረዋል፡፡

እንደ ኮሚቴ አባላቱ ገለጻ፣ ድርጅቱ ግንባታውን በቶሎ እንዲጀምርላቸው ለቤት ግዥው ከሚከፍሉት ገንዘብ የሚታሰብ በሚል ከ97 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ለተለያዩ ወጪዎች መሸፈኛ በቅድሚያ ከፍለው ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ድርጅቱ ለቤቶቹ ግንባታ የተጠየቀውን የሊዝ ክፍያ የከፈልነው እኛ ነን በማለትም ገልጸዋል፡፡  

ይህንኑ በደላቸውን ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ቢሮ ድረስ በጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ በአቤቱታ ደብዳቤያቸው ላይ እንደጠቀሱት፣ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ለቤት ፈላጊዎች ለመሸጥ ያለውን ሐሳብ ለቤት ገዥዎች ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ የመኖሪያ ቤት ለማግኘት በሚል ተስፋ አልሚው ኩባንያ የጠየቀውን ክፍያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ ቦታው ለሪል ስቴት የተሰጠና የተፈቀደ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን በመመልከት ግንባታውን በቶሎ ለማስጀመር በቅድሚያ ክፍያ ላይ የሚታሰብ በሚል ተጨማሪ ክፍያዎችን መፈጸማቸውን በዚሁ አቤቱታቸው ላይ ገልጸዋል፡፡ በተለይ በአልሚው ስም ለቦታው መከፈል ያለበትን የሊዝ ክፍያ 33,750,000 ብር የቅድሚያ ክፍያ በቀጥታ ለመንግሥት ገቢ ማድረጋቸውን የሚያሳይ መረጃም በአባሪነት አያይዘዋል፡፡ የሊዝ ክፍያውን ከኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ መርካቶ ቅርንጫፍ ካሰባሰቡት ገንዘብ ላይ ወጪ አድርገው ክፍያ እንደፈጸሙ አስረድተዋል፡፡ ለዚህም የመተማመኛ ቼክ ከኒው ላይን ሪል ስቴት ኤንድ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መቀበላቸውን አባሪ አድርገው ያቀረቡት ሰነድ ያመለክታል፡፡

ቤት ገዥዎቹ ድርጅቱ ለተረከበው መሬት መከፈል የነበረበትን ቅድሚያ ክፍያ ከመፈጸም ባሻገር የሪል ስቴት አልሚው ለመንገድ፣ ለምንጣፍ፣ ለኤሌክትሪክ፣ ለውኃ መስመር መዘርጋትና ማስቆፈር፣ ለግንባታ ማስጀመሪያና ለሌሎች የተለያዩ ሥራዎች ማከናወኛ በሚል የተጠየቁትን ክፍያችንም ፈጽመናል ይላሉ፡፡ ከ97 ሚሊዮን ብር በላይ ለሪል ስቴት አልሚው ተከፍሏል ይላሉ፡፡

ከዚህ ውጭ በርካታ የቤት ገዥዎች አልሚው የጠየቀውን ክፍያ በደረሰኝ የከፈሉ መሆናቸውን፣ አልሚው ግን ክፍያዎችን ከተቀበለ በኋላ የቤት ሽያጭ ውሉን ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑም አስረድተዋል፡፡ ጉዳዩን ሽማግሌዎች ገብተውበት ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ውል ሲሰጥ፣ ለአብዛኛዎቹ ግን አለመሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ከድርጅቱ ጋር የቤት ሽያጭ ውል ካደረጉት ውስጥ ከ200 በላይ ለሆኑት ውሉ ሲሰጥ፣ ቤት ገዥዎችም በውሉ መሠረት የሚጠበቅባቸውን ክፍያ ቢፈጽሙም ግን ግንባታው ተቋርጧል፡፡ ከድርጅቱ ጋር በተገባው ውል መሠረት ቤቶችን ገንብቶ ለገዥዎች በ12 ወራት ውስጥ ገንብቶ ለማጠናቀቅና ለማስረከብ ግዴታ ገብቶ እንደነበር ከድርጅቱ ጋር የተዋዋሉትንና ክፍያ የፈጸሙበት ሰነዶች ያመለክታሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሽያጭ ውል ስምምነቱ ከተደረገ ከስምንት ወራት በላይ ቢያስቆጥርም፣ ይታዩ የነበሩ ጅምር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ ተቋርጠዋል፡፡

እነዚህ ግንባታቸው ተጀምረው የነበሩትን ቤቶች በመገንባት ላይ የነበሩ ሁለት ኮንትራክተሮች ሥራቸውን አቋርጠው በመውጣታቸው፣ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ መቆሙንም የኮሚቴ አባላቱ ይገልጻሉ፡፡ በግንባታው ቦታ ምንም ዓይነት ሥራ እየተሠራ ያለመሆኑንና የድርጅቱ ጽሕፈት ቤትም ዝግ በመሆኑ ሊያነጋግሩ የሚችሉት ሰው ማጣታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ መዋቅር ከመጀመሪያውኑ መዋቅር የሚባል ያልነበረው ሲሆን፣ ይባስ ብሎ በአሁኑ ወቅት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በሕግ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው በመሆኑ፣ የበለጠ ሥጋት እንደፈጠረባቸውም ገልጸዋል፡፡ የድርጅቱ ደንበኞች ይህንኑ ችግራቸውን መፍትሔ ለማግኘት ለተለያዩ የክልሉና ለፌዴራል መንግሥት በደብዳቤ ጭምር ጥያቄ አቅርበው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በሌላ ኩባንያ ለሪል ስቴት ግንባታ ቦታው የእኔ ነው በሚል በቀረበበት የይገባኛል ጥያቄ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ጉዳዩም በሕግ እየታየ ነው፡፡

ከንግድ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ጉዳዩን የሚያውቀውና ክትትል እያደረገበት መሆኑን ነው፡፡ ጥያቄ ያስነሳው የስያሜ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ሲሆን፣ ቤት አስገንቢዎቹ ክፍያ የፈጸሙት ለየትኛው ነው? ማነው ሕጋዊው የሚለው ጥያቄ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ የሚጠብቅ ነው፡፡ 

ቤት ገዥዎቹ በተለይ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ባስገቡት አቤቱታቸው ላይ የክልሉንና የአገሪቷን ሕጎችና የክልሉን መንግሥት በመተማመን የፈጸምነው ስምምነት በመሆኑ፣ የክልሉ መንግሥት የቤት ገዥዎች ላይ በቤት አልሚው በኩል እየፈጸመ ያለውን የመብት ጥሰት በመገንዘብ በጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጠይቀዋል፡፡

‹‹አልሚው እስከ ዛሬ ድረስ ያለ ድርጅቱ ምንም ዓይነት ተሳትፎና የገንዘብ ድጋፍ የለውም፡፡ ሙሉ የድርጅቱን ወጪ ያወጣነው እኛ ቤት ገዥዎች በመሆናችን የክልሉ መንግሥት በቦርድ አደራጅቶን መክፈል ያለበትን ክፍያ ከፍለን የግንባታውን ሥራ ተረክበን እንድናከናውንና እንድናስተዳድር አስተዳደራዊ ውሳኔ እንዲሰጠን እንጠይቃለንም፤›› ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ቤት ገዥዎችን ለቤቱ ግንባታ ከሒሳባችን ላይ የከፈልነውን ገንዘብ በተመለከተ በምን ሥራ ላይ እንደዋለ ወይም እንዳሸሸ ለማወቅ፣ ሒሳብ አጣሪ በመመደብ አጣርቶ ውጤቱ እንዲቀርብና ውሳኔ እንዲሰጣቸውም ለፕሬዚዳንቱ ያቀረቡት አቤቱታ አመላክቷል፡፡

ጉዳዩ በደንብ ተመልክቶ መንግሥት ጣልቃ በመግባት የቤት ገዥዎችን የሸማችነት መብት እንዲያስከብርላቸው የቤቱ ግንባታ ቦታንም በተመለከተ፣ ቤት ገዥዎች የመገንባትና የማልማት መብታችንን እንዲጠበቅ መንግሥት እገዛ ካላደረገላቸው ችግሩ ሊፈታ ይችላል ብለው እንደማያምኑም አሳውቀዋል፡፡

በስፍራው ያሉት የግንባታ ግብዓቶች ለስርቆት እንዳይጋለጡ እንደዚሁም የአገርንና የወገን ሀብት እንዳይባክን፣ አስፈላጊውን የጥበቃ ከለላ የሚሰጥበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸውም አመልክተዋል፡፡ ለሌሎች ይመለከታቸዋል ለተባሉ አካላት ጥያቄያቸውን በደብዳቤ ጭምር አስገብተዋል፡፡   

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጉዳዩን እየተከታተለና እየመረመረ መሆኑ ታውቋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የከተማ ልማት ቢሮ አቶ ቃሲም ፊጤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተለያዩ መረጃዎችን እያሰባሰብን ጉዳዩን እየመረመርን ነው፡፡ እስካሁን በባለሙያ የደረስንበትም ጉዳይ በመኖሩ ጉዳዩን አጠናክረን ምላሽ የሚሰጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡ ቦታው ለሪል ስቴት ግንባታ መወሰዱንና የአቤቱታ አቅራቢዎቹንም ጉዳይ የሚያውቁ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቃሲም፣ ጉዳዩ ለፀረ ሙስና ኮሚሽን የተያዘም ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ለሪል ስቴት ማልሚያ የሚሆነውን መሬት እንዲሰጠው የተፈቀደለት ግንቦት 2006 ዓ.ም. መሬቱ እንዲሰጠው ውሳኔ የሰጠው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መስተዳድር ምክር ቤት ሲሆን፣ 30 ሔክታሩን መሬት በከፍተኛ የሊዝ ዋጋ መነሻ ዋጋ ላይ በመመሥረት በዓመት ለአንድ ካሬ ሜትር 18.75 ብር ዋጋ ተሰልቶ ነው፡፡

በኒው ላይን ጄኔራል ሪል ስቴት ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም፣ የክልሉ መንግሥት በንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የተሰጠው ፈቃድ ላይ ካፒታሉ 1.5 ሚሊዮን ብር መሆኑን ያሳያል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች