Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፈቃድ ያላቸው አጭበርባሪዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

በምሕረት አስቻለውና በውድነህ ዘነበ

በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ባልደረባ ነው፡፡ ሲኖትራክና ሌሎች መኪኖችን አስመጣለሁ በሚል ከሰዎች ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ያጭበረበረው ዙና ትሬዲንግ ሰለባ ነው፡፡ ሲኖትራክ ለማስመጣት ለዙና ትሬዲንግ የ700 ሺሕ ቅድሚያ ክፍያ የፈጸመው ከወራት በፊት ነው፡፡ ለዓመታት ጥሮ ያጠራቀመውን ገንዘብ ይጠቅመኛል ያለው ነገር ላይ ለማዋል በማሰብ ከደንበኞች ቅድሚያ ክፍያ እየወሰዱ የሚሠሩ የተለያዩ ተመሳሳይ ቢሮዎችን በር አንኳኩቷል፡፡ እነዚህ ቢሮዎች ጋር ሄዶ እንዴት ነው የሚሠሩት የሚለውን ነገር ከራሳቸው፣ ከሌሎችም በደንብ ለማጣራት ሞክሯል፡፡ በዚህ መልኩ ጥቂት ቀደም ብሎ እንደ ዙና ትሬዲንግ ካለ ኩባንያ ጋር የገባውን ውል እንደማያዋጣው ሲገባው በመጨረሻ ማፍረሱን ይናገራል፡፡

‹‹ዙና ስመጣም ጥርጣሬ ነበረኝ፡፡ የተወሰኑ ነገሮችን ለማጣራት ሞክሬአለሁ፡፡ መኪናው ሲመጣ ጂፒኤስ እንገጥማለን፣ ጐማም እናስመጣላችኋለን የሚሉ አማላይ ነገሮች ነበሩ፡፡ ውሉም ችግር ነበረበት፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች እንድጠራጠር አድርጐኛል፡፡ ግን በመጨረሻ ሪስክ ልውሰድ ብዬ ነው የወሰንኩት፤›› በማለት ድርጅቱ በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ዕውቅና የተሰጠው፣ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ የሚያስነግርም በመሆኑ የንግድ ሥርዓቱን አምኖ መወሰኑን ያስረዳል፡፡

እንደ አንድ ግለሰብ ማጣራት ያለበትን ማጣራቱን ያምናል፡፡ ከዙና ጋር የገባው ውል መኪናው በተባለው ጊዜ ባይቀርብ ድርጅቱ ላይ የሚያስቀምጠው ምንም ዓይነት ኃላፊነት የለም፡፡ ይህን ውል እንዴት ሊቀበለው ቻለ? ይህንንም እንዳሰበበት ነገር ግን ይህ ድርጅቱ እንዳለው ባለማድረጉ ሊወስድ የሚገባውን ኃላፊነት እንዳይሸከም ነፃነት ይሰጠዋል፤ እንደሱ ያሉ ደንበኞችም በዚህ ድርጅቱን ከስሰው ካሳ እንዳያገኙ ያደርጋል እንጂ ከነአካቴው ገንዘባቸውን እንዲያጡ እንደማያደርግ ይገልጻል፡፡ ‹‹ይህንን ውል መቀበል የሁለታችንም ችግር ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግን ገንዘቤን ያሳጣኝ ውሉ ሳይሆን እንደነዚህ ዓይነት ዘራፊዎች እንደ ልባቸው እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅደው ሥርዓት ነው፤›› ይላል፡፡

በአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል የባንክ ባለሙያውን አስተያየት ይጋራሉ፡፡ ሸማቾቹ የቻሉትን ነገር ማድረጋቸውን፣ አሳልፎ ለቀማኞች የሰጣቸው ግን ሥርዓቱ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ምንም እንኳ ዜጐችን ከቀማኞች ለመከላከል የሚያስችሉ ድንጋጌዎች፣ አሠራሮችም ለማጭበርበር ምቹ እንዳይሆኑ ቁጥጥር የማድረግ ሥልጣን ያላቸው ተቋማት ቢኖሩም፣ የንግድ ሥርዓቱ ለእንደዚህ ያለ ዝርፊያ ክፍት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹እንደዚህ ዓይነት ማጭበርበሮችን በተደጋጋሚ እየተመለከትን ነው፡፡ እነዚህ ማጭበርበሮች መልካቸውን እየቀያየሩ በየጊዜው አሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ ለማጭበርበር ምቹ የሆኑ ተቋማዊ አሠራሮች፣ ክፍተቶችና የሕግ ግድፈቶች መኖራቸውን ነው፡፡ አጭበርባሪዎቹ ደግሞ የተቆጣጣሪ ተቋማቱን ደካማ ጐን በደንብ አውቀውታል ማለት ነው፤›› ይላሉ አቶ ዮሐንስ፡፡

እሳቸው እንደሚሉት ኅብረተሰቡን ከእንደዚህ ዓይነት ማጭበርበር ሊጠብቁና ሊከላከሉ የሚችሉ ሕጐች አሉ፡፡ ችግሩ የሕጉ ተፈጻሚ አለመሆን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕጉን በደንብ ጠንቅቀው በሚያውቁ ባለሙያዎች የተደራጀና አቅም ያለው ተቋም አለመኖር ነው፡፡ ይህ ሸማቾችን በማማለልና በማታለል ለሚሠሩ የማጭበርበር ንግዶች ሜዳውን ምቹ አድርጓልም፡፡ በዚህ መልኩ በተለያዩ ጊዜያት ብዙዎች ሰለባ እንዲሆኑ ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ የዚህ ዓይነት አጋጣሚዎች ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞ አመቻቻለሁ ብሎ ብዙዎችን ያጭበረበረው አስካሉካንን፣ አክሰስ ሪል ስቴትንና ዙና ትሬዲንግን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የንግድ አሠራርና የሸማቾች ጥበቃ አዋጅ 685/2002 አንቀጽ 30 ከዚያም ይህን የተካው አዋጅ 813/2006 ሸማቹን ከተጠቀሱት ዓይነት ችግሮች መከላከል የሚያስችሉ ናቸው፡፡ አዋጆቹን በመጥቀስ ሸማቹን ከእንደዚህ ያሉ ቀማኞች ለመጠበቅ የንግዱ ማኅብረሰብንም ለመቆጣጠር የሚያስችል በቂ የሕግ ማዕቀፍ አለ የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ትልቁ ችግር የተቆጣጣሪው አካል ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻል ነው ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የመቆጣጠር ሥልጣንና ኃላፊነት ያለው የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከዛ ሲያልፍም ይህ ባለሥልጣን ተጠሪነቱ ለንግድ ሚኒስቴር በመሆኑ፣ ንግድ ሚኒስቴርም ይህን መቆጣጠር ይችላል ይላሉ፡፡ ከዚያም ካለፈ ፍትሕ ሚኒስቴር ጉዳዩ የሚመለከተው ሲሆን፣ ሃይ ሳይሉ አጭበርባሪዎች እንደ ልብ የሚንቀሳቀሱበት የንግድ ሥርዓት ሸማቹን እንዲህ እየጎዳ መሆኑ ትልቅ ቀውስ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው በዋነኝነት ተጠያቂ የሚያደርጉት ግን የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን ነው፡፡

ከባንክ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝበት ሁኔታ፣ የጉምሩክና ሌሎችም ከውጭ ዕቃ ሲገባ ያሉት የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች እየታወቁ እንደዚህ ያሉ ነገሮች በዚህ መጠንና በዚህ ጊዜ እናስመጣለን የሚሉ ማስታወቂያዎች በመገናኛ ብዙኃን መነገር የማይሆን ነገር ይሆናል እንደማለት ስለሆነ አቶ ዮሐንስ ይህን ሸማቹን እንደማማለል፣ እንደማታለልም ነው የሚመለከቱት፡፡ ማስታወቂያዎች የሚያታልሉ፣ የሚያጋንኑ፣ የሚያሳስቱ ተወዳዳሪን የሚያንቋሽሹ መሆን እንደማይችሉ በግልጽ በሕግ የተቀመጠ ነገር አለ፡፡ መሬት ላይ ካለው እውነታ አንፃር የሚባለው ነገር ሊሆን የሚችል ነው ወይ? የሚል ጥያቄ አንስተው ይከራከራሉ አቶ ዮሐንስ፡፡

በመገናኛ ብዙኃን የሚነገሩት ማስታወቂያዎች ሰፊውን ሕዝብ የሚደርሱ በመሆናቸው ተፅዕኖአቸው ከፍተኛ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በዙና ትሬዲንግ እንደተጭበረበረው የባንክ ባለሙያ ነገሮችን በግራም በቀኝ የማገናዘብ አቅም የሌላቸው ደግሞ ማስታወቂያዎቹን እንደ አንድ ትልቅ መተማመኛ ሁሉ ይወስዷቸዋል፡፡ ይህን በማስመልከት ያነጋገርናቸው የብሮድካስት ባለሥልጣን ባለሙያ ግን መገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያውን ለመቀበል አስነጋሪው ከሚመለከተው የመንግሥት ተቋም የንግድ ፈቃድ ያለው መሆኑን እንዲሁም የብቃት ማረጋገጫ ዓይነት ማስረጃዎችን ከመመልከት በዘለለ ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ ይገልጻሉ፡፡

የአስካሉካን ማስታወቂያ በምሳሌነት ቢታይ ድርጅቱ እሠራለሁ ያለውን ነገር ለመሥራት ራሱ ንግድ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ ፈቃድ ኖሮት ቢሆን እንኳን ከሚመለከተው ስፖርታዊ ተቋም ተጨማሪ ልዩ ፈቃድ ያስፈልገው ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ባልሆነበት ድርጅቱ ማስታወቂያውን ማስነገር ችሏል፡፡ በሌላ በኩል የዙና ትሬዲንግ ማስታወቂያ ሲታይ ግን ድርጅቱ ማስታወቂያውን ለማስነገር ማቅረብ ያለበትን እንደ ንግድ ፈቃድ ያለ ማስረጃ አቅርቧል፡፡ ብሮድካስተሩ ከዚህ አልፎ የምትለው ነገር የሚሆን ነው አይደለም ማለት ውስጥ መግባት እንደማይጠበቅበት የብሮድካስቱ ባለሙያ ያስረግጣሉ፡፡

በተቃራኒው አቶ ዮሐንስ ግን ከጊዜም ከሁኔታዎችም አንፃር የማይሆን የማይቻል ነገር እናደርጋለን እየተባለ ሸማቹ በማስታወቂያ ሲታለል፣ እዚህ ጋርም የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ሥራውን አልሠራም ይላሉ፡፡ ይህና መሰል ማስታወቂያዎች የንግድ አሠራርን የሚጻረሩ ናቸው፡፡ ባለሥልጣኑ ማስታወቂያ ማስነገራቸውን እንዲያቆሙ ብቻም ሳይሆን አሠራራቸውም ትክክል ባለመሆኑ ጭምር ዕርምጃ መወሰድ ይኖርበት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ ባለመቻሉ ብዙዎች ገንዘባቸውን ማጣታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ያነጋገርናቸው የብሮድካስት ባለሥልጣኑ ባለሙያም ጣታቸውን የሚቀስሩት እንደዚህ ላሉ ተቋማት ፈቃድ የሰጠው ንግድ ሚኒስቴርና ተቆጣጣሪው ባለሥልጣን ላይ ነው፡፡

ከጥቂት ጊዜያት በፊት አክሲዮን ለመሸጥ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ትርፍ እናከፋፍላለን የሚል ማስታወቂያ ያስነግር የነበረ ሼር ኩባንያ በብሮድካስት ባለሥልጣን ማስታወቂያውን እንዲያቋርጥ ተደርጓል፡፡ ምክንያቱ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ሼር ተሸጦና ወደ ሥራ ተገብቶ ትርፍ ማከፋፈል የሚሆን አይደለምና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በአገሪቱ ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ያለው የባንክ መስፈርትና ሒደት እየታወቀ ከደንበኞች ጋር ባደረገው ውል ላይ ከ60 እስከ 75 ቀናት ውስጥ በቴሌቪዥን ማስታወቂያ ደግሞ በ90 ቀናት ውስጥ ሲኖትራክ እናስመጣለን የሚለው የዙና ትሬዲንግ ማስታወቂያም የማይሆን በመሆኑ፣ ይመለከተኛል የሚለው አካል ማስቆም ነበረበት በማለት ከአቶ ዮሐንስ ጋር የሚስማሙ ብዙዎች ናቸው፡፡

ግማሽ ወይም የተወሰነ የቅድሚያ ክፍያ ከደንበኛ በመውሰድ የሚሠሩ የንግድ ኩባንያዎች ላይ የሚነሳ ሌላ መሠረታዊ ጉዳይም አለ፡፡ ብሔራዊ ባንክ የግል ባንኮችን እንደሚያደርገው ከደንበኞች ቅድሚያ ክፍያ የሚወስዱ ቢዝነሶች የሚያስቀምጡት ዋስትና መኖር የለበትም ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄም ክርክርም ነው፡፡ ለምሳሌ በዙና ትሬዲንግ 700 ሺሕ ብር የተጭበረበረው የባንክ ባለሙያ ‹‹ከሰው ገንዘብ የሚቀበሉ ቢዝነሶች እንደ ባንኮች ተመሳሳይ ቁጥጥር ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ከእኔ ሰባ በመቶ ቅድሚያ ክፍያ የሚወስድ ከሆነ ሰላሳ በመቶ የሚሆን ዋስትና እንዲያስቀምጥ መደረግ አለበት፤›› የሚል አስተያየት አለው፡፡ ሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ አቶ ዮሐንስ ግን የዚህ ዓይነቱ ቢዝነስ በሁለቱ ወገኖች ውል ላይ የሚመሠረት በመሆኑ፣ ሌላ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ የሚገባበት እንዳልሆነ ያመለክታሉ፡፡

ከደንበኛ የቅድሚያ ክፍያ በመሰብሰብ የሚሠሩ ኩባንያዎች መጀመሪያ የሚያሳዩት ካፒታል እንዳለና እውነትም የሚሠሩበት መሆኑን የሚቆጣጠር ሥርዓት እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙም አሉ፡፡ ካነጋገርናቸው በዙና ትሬዲንግ ከተጭበረበሩ አንዳንዶቹ እንደገለጹልን በተባለው ጊዜ መኪናውን እንደማያገኙ ሲገባቸው ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ሲጠይቁ እሺ ይባሉ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ በመነሳት ምናልባትም የተመለሰላቸው ጥቂት ሊኖሩ እንደሚችሉ በመጠርጠር (አንድ ዓመት የጠበቁ አሉ) ለወራት በደንበኛ ገንዘብ ያለምንም ችግር መጠቀምን ዒላማ ያደረገ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እንደዚህ ዓይነቱ ሥልታዊ ማጭበርበር ከተማ ውስጥ ተለምዷል፡፡ ባለሀብቱ ኢንቨስተር ነኝ ይላል፡፡ ያለው ስሙ ነው፣ የሚሠራው ግን በሰው ገንዘብ ነው፤›› ያለ አንድ አስተያየት ሰጪም አለ፡፡

ወደ ዓረብ አገሮች እንልካለን ይሉ በነበሩ ኤጀንሲዎች ችግር ኢትዮጵያውን ላይ የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳትና ኪሳራ በመመልከት መንግሥት ዘርፉ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት በመገንዘብ ወደ ዓረብ አገር እንልካለን የሚሉ ኤጀንሲዎች በግል ከሆነ አንድ ሚሊዮን ብር፣ ሼር ኩባንያ ከሆነ ደግሞ አምስት ሚሊዮን ብር ዋስትና እንዲገቡ የሚያደርግ አዋጅ አውጥቷል፡፡ ከደንበኛ ቅድሚያ ክፍያ በሚሰበስቡ ቢዝነሶች እየደረሰ ያለውን የደንበኛ መጭበርበር በመመልከት እዚህ ላይም ተመሳሳይ አካሄድ መከተል ያስፈልጋል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡም አሉ፡፡

‹‹አሁንም ምስኪኑን ሸማቹን ከአጭበርባሪዎች የሚጠብቅ ሥርዓት አለ ብዬ አላምንም፤›› የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ለደረሰው ጥፋት በቀዳሚነት ተጠያቂ የሚያርጉ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን ቢሆንም፣ ባለሥልጣኑ እንደዚህ ያለው በከፍተኛ ደረጃ የሚፈጸም ማጭበርበር ከእኔ ቁጥጥር ውጪ ነው በማለት ጣቱን ወደ ንግድ ሚኒስቴር ይቀስራል፡፡ የባለሥልጣኑ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው ፀጋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እንደዚህ ዓይነት ቢዝነሶችን የመቆጣጠር ሥልጣንም አቅምም ያለው ንግድ ሚኒስቴር እንጂ ባለሥልጣኑ አይደለም፡፡

እሳቸው ይህን ቢሉም ከላይ የተጠቀሱት አዋጅ 813 አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 8 እንዲሁም የዚሁ አዋጅ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 11 ኃላፊነቱ የባለሥልጣኑ እንደሆነ ያመለክታሉ፡፡

የአገሪቱን የንግድ ሥርዓት አምነው በቅድሚያ የከፈሉትን ገንዘብ ያጡ ደንበኞችና የሌሎችም አስተያየት ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ንግድ ሚኒስቴርን ተጠያቂ ወደ ማድረግ የሚያመዝኑ ይመስላል፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ አማካሪና የአለ በጅምላ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን አህመድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የአሠራር ክፍተት ለተፈጠረው ቀውስ ምክንያት መሆኑን ያምናሉ፡፡ ስለዚህም በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ሥርዓቱን በመፈተሽ የተሻለ አሠራር ለመዘርጋት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሠራራችንን እንደ አዲስ እየመረመርን ነው፤›› በማለት አቶ ኑረዲን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የምስኪኑ ሸማች የንግድ ሥርዓቱ ሊያቆማቸው ባልቻለ ሕገወጥ ቢዝነሶች መጭበርበር በተለያዩ አገሮች ለተቀሰቀሱ ተቃውሞዎች ምክንያት ሆኖ ያውቃል፡፡ ስለዚህም መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ላይ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንዳለበት አቶ ዮሐንስ ያሳስባሉ፡፡ ሌሎች አገሮች እንዲህ ያሉ ማጭበርበሮች እንዳይፈጠሩ ቀድመው የሚከላከሉ ሥርዓቶችን ይዘረጋሉ የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ‹‹ሥራዎች እውቀት ላይ መመሥረት አለባቸው፤›› ይላሉ፡፡ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ሠራተኞችም እነሱን የሚመለከተውን የተናጠል ሕግ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን ሕጐች ምሉዕ በሆነ መልኩ የሚያውቁ መሆን እንደሚገባቸው፣ ይህ ካልሆነ ግን ለተቆጣጣሪው አካል የትኛውንም ያህል ሥልጣን ቢሰጠው ትርጉም እንደማይኖረው ያስረግጣሉ፡፡

ምንም እንኳ የአሠራር ክፍተት ለተጠቀሰው ዓይነት ማጭበርበር በደንብ ሁኔታዎችን ያመቻቸ ቢሆንም፣ ግለሰቦችም የሚወስኑትን ውሳኔ ማጤን፣ ባለሙያም ማማከር ይገባቸዋል፡፡ አቶ ዮሐንስም ሰዎች የባለሙያ ምክር ከሚጠይቁ ራሳቸው ባለሙያ ሆነው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ቢያጡ ይመርጣሉ የሚል አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡ በእርግጥም እየታየ ያለው ነገር ይህን አስተያየታቸውን የሚያጠናክር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ከንድፈ ሐሳብ በዘለለ በተግባር ጠቃሚ ምክር የሚሰጥ ባለሙያም በበቂ አለ ብዬ አላምንም፤›› በማለት በመንግሥትና በሸማቹ በኩልም ያሉ ክፍተቶች ለአጭበርባሪዎች ሰፊ በር መክፈታቸውን ይጠቁማሉ፡፡    

      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች