Sunday, June 16, 2024

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ መንገድ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከትጥቅ ትግል ጊዜ ጀምሮ በኢሕአዴግ ቁልፍ መሪነት ለሦስት አሥርት ዓመታት፣ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ደግሞ ለሁለት አሥርት ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆዩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ፣ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ ይመስላል፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ወንበር ላይ የተቀመጡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢንጂነሪንግ ምሩቅ ሲሆኑ፣ ለአሥር ዓመታት ያህል በማስተማርና በአስተዳደር በአርባ ምንጭ የውኃ ቴክኖሎጂ ተቋም (በኋላ ዩኒቨርሲቲ) ያገለገሉ ምሁር ናቸው፡፡ በአንባቢነታቸው፣ በታጋይነታቸው፣ ተናግሮ በማሳመንና ሰዎችን ወደ ፓርቲው ሐሳብ ለማምጣት ወደር የላቸውም ተብለው በብዙዎች የሚደነቁትን አቶ መለስን መተካት ከባድ እንደሚሆን ተተንብዮ ነበር፡፡ አሁን ግን አቶ ኃይለ ማርያም በአቶ መለስ ወይስ በራሳቸው መንገድ እየሄዱ ነው የሚለው ጥያቄ በስፋት ይደመጣል፡፡  

አቶ መለስ በፖለቲካ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ከድርጅታቸው አልፎ በአገር ደረጃ እንዲሁም ከአካባቢው አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተነገረላቸው ነበሩ፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚያሰሙዋቸው ንግግሮችና በሚያካሂዷቸው ለአፍሪካ ያደሉ ሙግቶች፣ ‹‹የአፍሪካ ቃል አቀባይ›› የሚል ቅፅል ስም እስከ ማግኘት ደርሰው ነበር፡፡ ታዋቂ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ጋዜጠኞች፣ ተመራማሪዎችና አዋቂዎች ከአቶ መለስ ጋር መነጋገር ከመፈለጋቸውም በተጨማሪ አድናቆታቸውንም ይገልጹላቸው ነበር፡፡

ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ላይ ቀላል የማይባል ነበር፡፡ ብዙ መሪዎችና ጋዜጠኞች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋቸዋል፡፡ ሐዘናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእሳቸው ወንበር ላይ ማን ይቀመጣል?›› በማለት በአፍሪካ በሕዝቧ ብዛት ሁለተኛ የሆነችው አገራቸውም ተጨንቃ ነበር፡፡

አቶ መለስ በሽግግር ላይ የነበረች አገር፣ በብሔር ብዝኃነትና በማንነት ጥያቄዎች የምትታመስ አገር፣ በታሪክ ቅራኔዎች የተሞላች አገር በዚሁ በውስብስብ ግጭቶችና ድህነት የሚታመስ ቀጣና ዕምብርት የሆነች አገር፣ የምዕራቡ ዓለምና የምሥራቁ ዓለም የፖለቲካ ፉክክር የሚያካሂዱበት አገር በብቃት መምራት መቻላቸው በስፋት ይነገርላቸዋል፡፡ በከፍተኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሽግግር ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ፣ በእሳቸው ቦታ ላይ ቆሞ መምራት የሚችል ሰው ናፍቆት የነበራት ይመስላል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን አቶ መለስ በርካታ ተቺዎች ነበሩዋቸው፡፡

የቀድሞውን መንግሥት ለመታገል በነበረው የትጥቅ ትግል ተሳትፎ ያልነበራቸውንና የአዲሱ ትውልድ አባል የሆኑት፣ ብዙ የተባለለት የድርጅቱ የመተካካት አካል ተደርገው የሚታሰቡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ምክትልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ይዘው ለጥቂት ጊዜ ቆይተዋል፡፡ በቅድመ ታሪካቸው በትምህርታቸው ምክንያት ‘ቴክኖክራት’ የሚባሉ መሪ ናቸው፡፡ በመጀመሪያ ሳምንታት የቀድሞውን አለቃቸውን ቦታ መሙላት ተስኗቸዋል ተብለው ሲተቹ ነበሩ፡፡ በአኳኋናቸውም ሆነ በፖለቲካ ትንታኔያቸው አቶ መለስን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ በመባልም ሲተቹ ነበር፡፡

ከመነሻው፣ ‹‹የእኔ ኃላፊነት የአቶ መለስ ራዕይ ማስፈጸም ነው፤›› ማለታቸውም አዲስ ፊት እንጂ አዲስ የፖለቲካ እሳቤና ርዕዮት እንዳይጠበቅ አድርጎ ነበር፡፡ ቢያንስ በአቀራረብ ደረጃ፣ በአነጋገር ዘይቤና በአተያይ አቅጣጫ ለመለየት ባለመሞከራቸው፣ ራሳቸውን መስለው በራሳቸው መንገድ ነገሮችን የሚያዩበት መድረክ እንዲፈጥሩ ሲጐተጉቱ የነበሩ በርካቶች ናቸው፡፡

በእርግጥ በብዙዎች አዲስ የፖለቲካ አቅጣጫ ተደርጎ አልተወሰደም እንጂ፣ ከዚህ በፊት ኢሕአዴግ ያልሞከረው አገሪቱን በሦስት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች እንድትመራ ማድረግ፣ ድርጅቱ ውስጥ የሚታየውን የአባል ፓርቲዎች የሥልጣን ‹‹ሽሚያ›› ለማርካትም ይሁን የጋራ አመራርን ለመፍጠር ያደረጉት ሙከራ ነበር፡፡

በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቀጥሮ የሚሠራ ግለሰብ በቅርቡ የመንፈቅ ዓመት ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ ካደመጠ በኋላ፣ ‹‹የሰውየው አልታይ ያለን የፖለቲካ ሰብዕና መውጣት ጀምሯል፡፡ አሁን ገና ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እየተሰማኝ ነው፤›› በማለት ነበር የገለጻቸው፡፡

የኃይለ ማርያም መንገድ

ቀደም ሲል ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ጀምሮ የነበራቸውን ባህሪ በመለወጥ አዲስ የፖለቲካ አካሄድ የጀመሩት አቶ ኃይለ ማርያም ለዘብተኛና የማይቆጡ፣ ጥያቄ የሚወዱ፣ እንዲሁም የመርህ ሰው የሚያስመስሉዋቸው አካሄዶችም ታይተውባቸዋል፡፡

በአገሪቱ የሚታየው የአስተዳደር ችግር የቆየ ቢሆንም እየተባባሰ መምጣቱን ዛሬ ተገንዝበዋል፡፡ በእርግጥ ኢሕአዴግ ውስጥ የሚደረገውን የመገማገምና የመጎሻሸም ባህል፣ እንዲሁም በፅኑ የተገመገመ ሰው ከአንድ ቦታ ተነስቶ ሌላ ኃላፊነት ላይ ማስቀመጥ ዛሬም ድረስ የቀጠለ ቢመስልም፣ በአሠራር ለመለወጥ የሚያስችል መንገድ እየተከተሉ ይመስላል፡፡

በአሥረኛው የድርጅቱ ጉባዔ ላይ በተለይ በዋናው መሥራች ድርጅቱ በሕወሓት ውስጥ የሰላ መገማገምና መተቻቸት በገሐድ ሲታይ በአጠቃላይ በአገሪቱ ሙስና፣ ሕገወጥነት፣ ኔትወርክ፣ እንዲሁም ሥርዓት አልበኝነት መስፈኑ በስፋት ተወስቷል፡፡ ድርጅቱም በዚህ ደረጃ ሲያምን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ሊቀመንበርነት በአገሪቱ የተንሰራፋው የአስተዳደር ብልሹነት በውል እንዲጠናናሰ እንዲፈተሽ የተደረገው በእሳቸው ጊዜ ነው፡፡ በኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን በሕዝቡ ሲቀርቡ የሰነበቱ ነገር ግን ሰሚ ያጡ ሥር የሰደዱ ቅሬታዎች፣ በአዲሱ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ተቋም ተጠንቶ የተረጋገጠው በእሳቸው ጊዜ ነው፡፡

በትግራይ ክልል ሳይቀር ለዘመናት የታፈነው የሕዝብ ቅሬታ በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት መካሄዱን ተከትሎ በባለሥልጣናት መካከል በተደረገው ውይይት፣ ጠቅላይ ማኒስትሩ ራሳቸው ችግሩን አምነው በመቀበልና ሌሎችም እንዲቀበሉ ተፅዕኖ ሲፈጥሩ ተስተውሏል፡፡

ጥናቱ ከአሥራ አንድ በላይ ግኝቶች ሲኖሩት፣ በተለይ በመሬት አስተዳደር፣ በንግድና በኢንቨስትመንት፣ በፍትሕና በመሳሰሉ አገልግሎቶች መንግሥት ያልተሳካለት መሆኑን አመላክተዋል፡፡ ሕዝብን በማሳተፍ የሚመካው ኢሕአዴግ ሕዝብን ለውይይት የሚጠራው አንድን ነገር ከጨረሰ በኋላ እንዲያፀድቅለት መሆኑ፣ ድርጅቱ በሙሰኛ ባለሥልጣናቱ ላይ ዕርምጃ እንደማይወሰድ፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተገዛ እንደሆነ፣ እንዲሁም የሹማምንቶቹ ተጠያቂነት የወረደ መሆኑን በተጠናው ጥናት መረጋገጡን ገዥው ፓርቲ አምኖ ሲቀበል በአቶ ኃይለ ማርያም ዘመን ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡

በኦሮሚያ የተጋለጠው የአስተዳደር ቀውስ

የኢሕአዴግ አመራሮች በዚሁ በአራቱ ክልሎች ላይ የተካሄደውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጥናት በተወያዩ በጥቂት ጊዜ ውስጥ፣ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ችግሩ ውስጣዊ ለመሆኑ ማረጋገጫ መሆኑን አቶ ኃይለ ማርያም ተናግረዋል፡፡

‹‹ሌላ አካል ላይ ጣት ከመቀሰር ይልቅ ችግሩ የራሳችን እንደሆነ አስምረን መሄድ አለብን፤›› በማለት ነበር ሁኔታውን የገለጹት፡፡ ቀደም ሲል በውጭ ኃይሎች የተቀሰቀሰ ተደርጎ ሲገለጽ የነበረውን ወደ ውስጥ አምጥተውታል፡፡ ‹‹በእኛ ውስጥ ባለ መበላሸት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝቡን ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ ባለመስጠት ከሕዝቡ ጋር ቅራኔ ውስጥ እየገባን መጥተናል፤›› ብለዋል፡፡ ቅራኔው ከሰሜን እስከ ደቡብ የአገሪቱ ክፍል መሆኑን ሳያመነቱ የተቀበሉ ሲሆን፣ ‹‹በትከሻው ላይ ተጣበቅንበት›› ያሉት አርሶ አደሩ፣ ‹‹ዞር በሉ ሲል አንዳንዴ በአንደበቱ አንዳንዴ በእጁ ይላል፡፡ አንዳንድ ቦታ ላይ አሁን በእጁ ነው ዞር በሉ ያለው፤›› ሲሉም በድፍረት ተጠያቂነቱን ወስደዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ በዚሁ ደረጃ የገለጹት የአስተዳደር ብልሹነት እየተነገረ ያለው ድርጅታቸው መቶ በመቶ ባሸነፈበት ምርጫ ማግሥት ነው፡፡ ተቃዋሚዎችም፣ ‹‹አሁንም ችግሩን ኢሕአዴግ አልተገነዘበውም፡፡ ሕዝቡ ሐሳብ የሚገልጽባቸው መንገዶች በመታፈናቸው የመጣ ችግር ነው፤›› ይላሉ፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የፖለቲካ መታፈን ውጤት ይሁን ወይም በራሱ ተነጥሎ የሚታይ አከራካሪ ቢሆንም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ግን በተለይ በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ግጭት ለጠፋው የሰው ሕይወትና ለችግሩ መፈጠር መንግሥታቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው በድርጅቱ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ይመስላል የሚሉ አሉ፡፡

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ‹‹ይቅር ባይነት›› እና ወደ ውስጥ የመመልከት ጉዳይ ሪፖርተር ላነጋገራቸው የተለያዩ አካላት የተለያየ ትርጉም የሰጠ ይመስላል፡፡ የኢዴፓ መሥራችና የቀድሞ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት ይህንን ይቅርታ የመጠየቅ ባህል እንደነበረው ማንበባቸውን ገልጸው፣ ‹‹ሥልጣን ከያዘ በኋላ ግን ይቅርታን እርግፍ አድርጐ ትቶ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የጠየቁት ይቅርታ፣ ተቋማዊ ይሁን ግለሰባዊ ግን ጥያቄ እንደጫረባቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይቅርታው ከረጅም ጊዜ በኋላ የመጣ ባህሪ ነው፡፡ በግልጽና በማያሻማ ቋንቋ ነው የቀረበው፡፡ የቀረበበት መንገድም ኃላፊነትን ሙሉ በመውሰድና ራስን ተጠያቂ በማድረግ ነበር፤›› በማለት አክለዋል፡፡ በደርግ ዘመን ሰው መግደል ለአብዮቱ ሲባል ልክ እንደሆነ ይገለጽ ነበር፡፡ በኢሕአዴግም ዘመን ሰው ለመግደል ‹‹ሁኔታው አስገደደኝ›› የሚባል እንደነበር ገልጸው፣ ‹‹የአሁኑ ይቅርታ ግን ሙሉ ያልተሸራረፈና በፖለቲካ ያልታጀበ መሆኑን በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን ታይቶ የማይታወቅ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አንድ የጐደለ ነገር እንዳለ ግን አመልክተዋል፡፡ ‹‹ይቅርታ የቅሬታ ማብረጃ ነው፡፡ ቂምና ቁርሾ ያበርዳል፡፡ ከመጠን በላይ ኃይል የተጠቀሙ ሰዎች ግን ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አልተጠቀሰም፡፡ እንዲሁም ለሟች ቤተሰብ በቂ ካሳ መክፈል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ ይቅርታው የተጠየቀበት ጊዜ የዘገየና ትንሽ ነው የሚሉ አስተያየቶችን አቶ ሙሼ አይቀበሉም፡፡

የመድረክ አመራር አባልና ነባሩ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ግን የአቶ ኃይለ ማርያም አነጋገር የፈጠረላቸው አዲስ ነገር የለም፡፡ ለፕሮፌሰሩ ይቅርታው እንዲደርስ የተፈለገው መንግሥት ለዕርዳታ እጁን ለሚዘረጋለት ዓለም አቀፍ ማኅብረሰብ እንጂ ሰለባ ለሆነው ሕዝብ አይደለም፡፡

‹‹ለተራ ሰው ይቅርታ የተጠየቀ ሊመስለው ይችላል፡፡ የአቀራረቡ ጉዳይ ካልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስም ሲያደርጉት የነበረ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህቺ በኢሕአዴግ የተመረጠች ታክቲክ ነች፡፡ ይቅርታ አልጠየቁም፡፡ የደረሰውን ጉዳት ዘርዝረው አላቀረቡም፡፡ ሕዝቡ እንዲቆጣ በማድረጋችን ይቅርታ ነው የተባለው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹20 ዓመት ሙሉ አጥፍተናል እየተባለ የት አለ በተግባር ለውጥ የመጣው?›› ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅላጼ ቀይረው ነው የቀረቡት፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ግጭት የጠበቁትን ያህል ኢሕአዴግ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ‹‹እስቲ ማነው ተጠያቂ የተደረገው? ለጉዳዩ ተጠያቂ የሆነ የኦሮሚያ መንግሥት ማንን ከሥልጣን አወረደ?›› በማለት አሁንም ይጠይቃሉ፡፡ ከኃላፊነታቸው ተነሱ የተባሉ ሰዎች በሌላ ቦታ መሾማቸውንም ለዚህ እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡

ለአቶ ሙሼ ይቅርታው ከልብ የመነጨና በኢሕአዴግ ያልተለመደ አካሄድ ሲሆን፣ ለፕሮፌሰር ግን ሥልት ነው፡፡ አቶ ሙሼ ኢሕአዴግ በአዲሱ አመራር እየተለወጠ መምጣቱንና በምርጫ አገኘሁት ያለውን የሕዝብ ውክልና በቂ እንዳልሆነ የተረዳ መሪ ማግኘቱን አመልክተዋል፡፡ ለፕሮፌሰር በየነ ግን የአቀራረብ ለውጥ እንጂ፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከቆየው የኢሕአዴግ ባህሪና ከአቶ መለስ አካሄድ መውጣቱን የሚያሳይ አይደለም፡፡

አቶ አበበ አይነቴ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና የስትራቴጂክ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ‹‹መንግሥት በይፋ ይቅርታ ሲጠይቅ የተለመደ አይደለም፡፡ አዲስም ጅምር ነው፤›› ይላሉ፡፡ ችግርን በፓርቲው ውስጥ መገምገም የተለመደ መሆኑን የሚናገሩ አቶ አበበ፣ በሕዝብ ፊት በግልጽ አጥፍቻለሁ ሲል ኢሕአዴግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በእኔ እምነት አንድ መሪና መንግሥት የሕዝበ አገልጋይ መሆኑን ለማሳየት ትልቅ አብነት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል ተጠና በተባለው መሠረት ከተካሄደ ድርጅቱ ቀደም ሲል ተግባራዊ ያደርግ የነበረውን ፖለቲካ ታማኝነት ቅድሚያ መስጠት አስቀርቶ፣ ብቃትን መሠረት ያደረገ እንዲሆን በር የሚከፍት እንደሚሆንም አቶ አበበ እምነታቸው ነው፡፡ ‹‹የሕዝብ አገልጋይነተ ስሜት ይፈጥራል፤›› ብለዋል፡፡

የመለስ ውርስ

አቶ መለስ የድርጅታቸው የውስጥ ፖለቲካ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ቀያሽና ተንታኝ ነበሩ፡፡ ይህ ተግባራቸው ለኢሕአዴግም ለአገሪቱም ያስገኙት ለውጥና ጥንካሬ የማይካድ ቢሆንም፣ በዚህ ጠቅላይነታቸው ድርጅታቸው ውስጥ ሌሎች መሪዎች ዕውቀት እንዳያፈልቁና የፖለቲካ ሰብዕና እንዳያገኙ አድርገዋል ተብለው ይተቻሉ፡፡ ይኼም ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ያገኙ መሪዎችም፣ ያልተገባ ትችትና ወቀሳ በመሰንዘር በአጠገባቸው እንዳይታዩ አድርገዋል ተብለውም ይታማሉ፡፡ እሳቸው በሕይወት ሳሉ እንደተናገሩት ‹‹የድርጅታቸው ፍሬ›› እንደሆኑ ቢገልጽም፣ በተግባር የድርጅቱ ፈጣሪ ሆነው ሲታዩ ነበር የሚሉዋቸው አሉ፡፡ ያለእሳቸው ድርጅቱ ህልውና የሌለው መምሰሉን በድፍረት የሚናገሩ አሉ፡፡ በእርግጥ የሕወሓት አባት ተደርገው የሚታዩ አቶ (አቦይ) ስብሓት ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹የመለስ ሞት ከድርጅቱ የአንድ ሰው መቀነስ ያህል ነው፤›› ብለው፣ ድርጅቱ በእሳቤዎችና በርዕዮተ ላይ የተመሠረተ እንጂ ከግለሰብ ህልውና ጋር ትስስር የለውም በሚል መሞገታቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ዓመት በመቐለ ከተማ በተካሄደው የድርጅቱ አሥረኛ ጉባዔም ላይ፣ ‹‹መለስ በአንድ ሺሕ ዓመት የሚፈጠር ዓይነት ሰው ነበር፤›› በማለት አቶ በረከት ስምኦን የሰጡትን አስተያየት በመቃወም፣ ‹‹ሁኔታው ከጠየቀ በየዓመቱ ሺሕ መለሶች መፍጠር እንችላለን፡፡ መሪን የሚፈጥረው ሁኔታ ነው፤›› በማለት መሞገታቸው ይታወሳል፡፡

‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሐሳብ አመንጪ ሲሆኑ፣ በተለይ ከ1997 ዓ.ም. የፖለቲካ ቀውስ በኋላ በፀደቁ አዋጆች ወይም በተቃዋሚዎች መዳከም፣ አቶ መለስ ራሳቸው እንደቀየሱት የሚታመንበት የምርጫና የፖለቲካ መሣሪያ ተደርጎ የሚወሰደው ‹‹የልማት ሠራዊት›› አደረጃጀት ሒደት፣ ድርጅቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማውን መቶ በመቶ መቆጣጠር ተችሏል ተብሎ ይታመንበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት የታየው የመልካም አስተዳደር ቀውስ የልማታዊ መንግሥት መርህ ውጤት አድርገው የተመለከቱት ተቃዋሚዎችም፣ ‹‹የአንድ ፓርቲ›› ሥርዓት መመሥረቱና የመድበለ ፓርቲ ፖለቲካ ሥርዓት መጨንገፉን ተናግረው ነበር፡፡ አቶ መለስ ግን ድርጅታቸው አውራ ፓርቲ ሆኖ እንደቀጠለ ነበር ከዚህ ዓለም የተለዩት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የቀድሞ አለቃቸውን መንገድ አልለቀቁም ተብለው የተተቹት፣ በተቃዋሚዎች ላይ በሚሰነዘሩት የሰላ ትችትና በጠላትነት የመመልከት አባዜ አንዱ ሲሆን፣ በእሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትርነት ጊዜ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው አምስተኛው ዙር ምርጫም የባሰ የሚባል ውጤት ማስገኘቱ ይወሳል፡፡ በማናቸውም የዴሞክራሲ አቀንቃኝ የሆኑ አገሮች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ፓርላማውን መቶ በመቶ ኢሕአዴግ መቆጣጠሩ አሳዛኝ መሆኑ ይነገራል፡፡

በኤርትራ ላይ ባላቸው አቋምና በተቃዋሚዎች ላይ በሚከተሉት ፖሊሲ፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ እንዲሁም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲና ቀደም ብለው በወጡ አፋኝ ተብለው በሚተቹ ሕጎች ላይ ድርጅቱ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አማካይነት ምንም ለውጥ ሳይደረግባቸው ላለፉት አራት ዓመታት መጓዙም ብዙ ይባልበታል፡፡

 

  

   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -