Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ደርባ ሲሚንቶ ሁለተኛ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ደርባ ሲሚንቶ ከአዲስ አበባ ሰሜን ምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጫንጮ ከተማ አቅራቢያ፣ ሁለተኛውን የሲሚንቶ ፋብሪካ በ300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ ነው፡፡

የደርባ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ለመገንባት የታቀደው ሁለተኛ የሲሚንቶ ፋብሪካ በዓመት 25 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ከ250 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር እንደሚገመት አቶ ኃይለ ተናግረዋል፡፡ የዝግጅት ሥራው ተጠናቆ ግንባታ ከተጀመረ ከ18 እስከ 24 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ደርባ ሲሚንቶ የመጀመሪያውን የሲሚንቶ ፋብሪካ በ351 ሚሊዮን ዶላር ገንብቶ በኅዳር 2004 ዓ.ም. አስመርቆ ወደ ምርት መግባቱ ይታወሳል፡፡ የመጀመሪያው ፋብሪካ በዓመት 25 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም አለው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው በዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ አምርቶ በመሸጥ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ኃይሌ፣ ፋብሪካው በኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቆራረጥ በቀን በአማካይ ለስድስት ሰዓት ምርት ለማቋረጥ እንደሚገደድ ተናግረዋል፡፡

የግልገል ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ማመንጨት በመጀመሩ የኤሌክትሪክ አቅርባቱ እየተሻሻለ ይሄዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ባለቤትና ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አል አሙዲ ተመርቆ የተከፈተው ደርባ ሚድሮክ፣ የሲሚንቶ ገበያን በማረጋጋት ትልቅ ሚና መጫወቱን አቶ ኃይሌ ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው ፋብሪካ በ351 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነባ ሲሆን፣ ሼክ መሐመድ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርገዋል፡፡ የተቀረው 251 ሚሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽንና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በብድር የተገኘ ነው፡፡

ለሁለተኛው ፋብሪካ ግንባታ የሚውል ብድር ከእነዚሁ የፋይናንስ ተቋማት ለማግኘት ደርባ ሚድሮክ በመነጋገር ላይ መሆኑን አቶ ኃይሌ አስረድተዋል፡፡ የሁለተኛውን ፋብሪካ ግንባታ የሚያካሂደው ቻይና ናሽናል ቢዩልዲንግ ማቴሪያልስ የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ የመጀመሪያውን ፋብሪካ የገነባው ይኼው ኩባንያ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ደርባ ሲሚንቶ በዓመት 50 ሚሊዮን ኩንታል ሲሚንቶ የማምረት አቅም ይኖረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 20 የሚሆኑ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ሲኖሩ ደርባ፣ ሙገር፣ መሶቦ፣ ዳንጎቴና ናሽናል ሲሚንቶ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ሲሚንቶ የማምረት አቅም በዓመት 15 ሚሊዮን ቶን የደረሰ ሲሆን፣ ዓመታዊ ፍጆታ ደግሞ ከስምንት እስከ ዘጠኝ ሚሊዮን ቶን ነው፡፡

አቅርቦቱ ከፍላጎቱ የላቀ በመሆኑ የገበያ ሽሚያ እየተፈጠረ ነው፡፡ የገበያ እጦት አለ በሚባልበት ወቅት ደርባ ሲሚንቶ እንዴት የማስፋፊያ ፕሮጀክት ለማካሄድ አቀደ ተብለው የተጠየቁት አቶ ኃይሌ፣ የተፈጠረው የገበያ ችግር ጊዜያዊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የተቀመጡት ግቦች በአግባቡ ወደ ተግባር ከተለወጡ የገበያው ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ይቀየራል፤›› ብለዋል፡፡

ደርባ ሲሚንቶ በቀን 2,000 ኩንታል ጂብሰም የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ ባለቤት ነው፡፡ ከፋብሪካዎቹ በተጨማሪ ደርባ በ200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ምርቱን የሚያጓጉዝበት 100 ቮልቮ የጭነት ተሽካርካሪዎች ገዝቶ ማሰማራቱ ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች