Wednesday, April 17, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ዘርፍ አፈጻጸም እያሽቆለቆለ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ማዕድን ሚኒስቴር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ በመሄዱ የዘርፉ ተዋናይ ኩባንያዎች በተገቢው መንገድ ማስተናገድም ሆነ መደገፍ ባለመቻሉ፣ አገሪቱ ከማዕድን ወጪ ንግድ ልታገኝ የምትችለውን ገቢ ከማግኘት ማገዱ ተመለከተ፡፡

መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. የማዕድን፣ የነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በጠራው ስብሰባ፣ የክልል ማዕድን ቢሮዎችና በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች በዘርፉ ችግሮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የማዕድን ማውጫ ጣቢያ አለመልማቱና ከኢትዮጵያ በኋላ ለማዕድን ዘርፍ ትኩረት የሰጠችው ኤርትራ የማዕድን ማውጫ ጣቢያ ባለቤት መሆን፣ የማዕድን ሚኒስቴርን ደካማነት ያመለክታል ተብሏል፡፡

በዚህ ውይይት የማዕድን ዘርፍ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር መፍጠር ስላለበት ግንኙነትና በማዕድን ዘርፍ ልማትና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ጥናቶች ቀርበው ውይይት ተካሂዷል፡፡

ኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ የወርቅ ማዕድናት እንዳሏት የዳሰሳ ጥናቶች ቢያመለክቱም፣ በ1972 ዓ.ም. ተገኝቶ በ1982 ዓ.ም. ተመርቆ ሥራ ከጀመረው ለገደንቢ በስተቀር እስካሁን በኢንዱስትሪ ደረጃ ወርቅ ማውጣት አልተቻለም፡፡

እንዴት ተጨማሪ የወርቅ ማውጫ ጣቢያዎች ሊለሙ አልቻሉም የሚለው ጉዳይ በማዕድን ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ላይ ያነጣጠረ ቢሆንም፣ ሚኒስቴሩ ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ በሰው ኃይል ፍልሰት በማመካኘት ሊያልፈው መሞከሩ ተስተውሏል፡፡

መንግሥት ከማዕድን ዘርፍ በሚገኝ ገቢ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱ ይታወቃል፡፡ ከወሰዳቸው ዕርምጃዎች መካከል ለማዕድን ሚኒስቴር አዲስ ሕንፃ መገንባትና አስፈላጊ ላቦራቶሪዎችን ማሟላት ይገኙበታል፡፡

ተሰብሳቢዎች እንዳሉት ግን ሕንፃው በድኑን ከመቆሙ ባሻገር ዘርፉን መጥቀም አልቻለም፡፡ የሰው ኃይል እየሸሸው እንደሆነና ያለውም የሰው ኃይል ወደ ሙስና የማዘንበል አዝማሚያ በማሳየት አገልግሎት አሰጣጡን ደካማ አድርጎታል ተብሏል፡፡

ውይይቱን የመሩት የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቴዎድሮስ ገብረ እግዚአብሔር፣ የስብሰባው ተሳታፊዎች ያለምንም ሥጋት በግልጽ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ቢጋብዙም ጥቂት ተሳታፊዎችን ብቻ አግኝተዋል፡፡

ከተወሰኑ አስተያየት ሰጪዎች በስተቀር በግልጽ መሥሪያ ቤቱን የተቸ ባይኖርም፣ ሪፖርተር በተናጠል ያናገራቸው የማዕድን ዘርፍ ተዋናዮች ግን ሐሳባቸውን በነፃነት መግለጽ ዋጋ እንደሚያስከፍላቸው ገልጸዋል፡፡ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዘርፉ ባለሀብት፣ ‹‹ከፍተኛ ገንዘብ ለማዕድን ፍለጋ አውጥተናል፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ባለሙያዎች ቂም ይዘው ፈቃድ ባያድሱልን ወይም ፈቃድ ዕደሳውን ቢያዘገዩብን ኪሳራው ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ከማድረግም ወደኋላ የሚሉ ሰዎች አይደሉም፤›› ብለዋል፡፡

ደፈር ያሉ አስተያየት ሰጪዎችም በስብሰባው ላይ ሚኒስቴሩ አዲስ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ መስጠት እንዳቆመ በማማረር ገልጸዋል፡፡ በፈቃድ ዕደሳ በኩልም በርካታ ኩባንያዎች እየተጉላሉ መሆኑን ሲገልጹ፣ ወደ በላይ አካል ሄዶ ለማመልከት እንኳ ሊደርስባቸው የሚችለውን የጎንዮሽ ተፅዕኖ በመሥጋት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አገልግሎት አግኝተው በፍለጋ ላይ የሚገኙ ተቋማት ማዕድን ሚኒስቴር ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ባለመሆኑ፣ ክልሎች ደግሞ ከዞንና ከወረዳ እንዲሁም ከቀበሌ ጋር ጠንከር ባለ መዋቅር የሚናበቡ ባለመሆናቸው ለከፍተኛ ችግር እየተዳረጉ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የማምረት ፈቃድ ያገኙ ኩባንያዎችም በቦታቸው ላይ የሠፈሩ ሰዎችን የማንሳትና መልሶ የማስፈር ችግር መኖሩ፣ አንዳንድ ክልሎች የሚሰጡት ትዕዛዝ በሌሎች መዋቅሮች ተቀባይነት የማያገኝ መሆኑ፣ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች የኩባንያዎችን የወርቅ መሬት በኃይል የሚወሩ መሆኑ እንደ መሠረታዊ ችግሮቹ ተጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በበኩሉ በኩባንያዎች ላይ የሚታዩ ችግሮችን አቅርቧል፡፡ ሚኒስቴሩ አብዛኛዎቹ የማዕድን ኩባንያዎች የአካባቢ ጥበቃ ሥራ እንደማያካሂዱ፣ የታክስና የሮያሊቲ ክፍያዎችን በወቅቱ እንደማይፈጽሙ ጠቅሷል፡፡

አቶ ቴዎድሮስ ዘርፉ የሚያስገኘው ገቢ እያሽቆለቆለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የማዕድን ዘርፍ ከቡና ቀጥሎ ሁለተኛ ደረጃ ገቢ የሚያስገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን እየተንሸራተተ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ኢንዱስትሪያላይዜሽንን እናሳድግ ከተባለ የማዕድን ዘርፍ ግብዓት መሆን አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግም የተቻለንን እናደርጋለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የማዕድን ዘርፍ የኪራይ ሰብሳቢነት የስበት ኃይል በመሆኑ ሚኒስቴሩ ትኩረት አድርጎ ይሠራል ብለዋል፡፡

ነገር ግን ተሰብሳቢዎቹ በመልካም አስተዳደር ችግር ሚኒስቴሩ እየተናጠ እንደሆነ፣ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የማዕድን መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ አካላት እኩያ ባለማዕረጎች በመሆናቸው ማንም ማንንም እንደማያዳምጥ፣ ኩባንያዎች የማዕድን ምርመራ ፈቃድ ጠይቀው በአፋጣኝ ምላሽ እንደማያገኙ፣ የካዳስተር ሥርዓት በዓለም ባንክ ድጋፍ ተግባራዊ ቢደረግም አገልግሎት መስጠት ካቋረጠ መሰነባበቱን፣ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የማዕድን ናሙና ምርመራ አገልግሎት መስጠት ስለተሳነው ኩባንያዎች ናሙናቸውን ወደ ውጭ አገሮች ለመላክ እንደተገደዱ በመግለጽ ቅሬታዎች አቅርበዋል፡፡

የማዕድን ሚኒስቴር በየጊዜው ከመሥሪያ ቤቱ በሚፈልሱበት ባለሙያዎች ምክንያት የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ እየሆነ መምጣቱን በቅርቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች