ኤፈርት ኢንቨስትመንት ግሩፕ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥ ዕውን ይደረጋል ያለውን የአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል የኬሚካል ኢንዱስትሪ ለመገንባት፣ ከቻይናው ሲኢሲ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ተፈራረመ፡፡
ኢንዱስትሪው ከመቐለ ከተማ 25 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አራቶ ከተማ ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ ስምምነቱ ከተፈጸመበት ማግሥት ጀምሮ ሥራው እንደሚጀመር መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡
የኬሚካል ኢንዱስትሪው ላይምስቶን፣ ጨውና ሌሎች ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም የተለያዩ ኬሚካሎችን እንደሚያመርት ተገልጿል፡፡ በዋናነትም በዓመት 60,000 ቶን ፒቪሲ ሬዚን፣ 50,000 ቶን ኰስቲክ፣ ካልሲየም ካርባይድ፣ ክሎሪን አልካላይና ሌሎችም ኬሚካሎችን ለማምረት ዕቅድ ይዟል፡፡ ግንባታው ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር የኤፈርትን አቅም በሦስት እጥፍ እንደሚያሳድገው ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ አዜብ መስፍን ገልጸዋል፡፡ ከሲኢሲ ቀጥሎ ሱር ኮንስትራክሽንና መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ በግንባታው እንደሚሳተፉም ተናግረዋል፡፡
‹‹የፕሮጀክቱን ሐሳብ ያመነጨው መለስ ነበር፡፡ ኢንዱስትሪው እንዲገነባም ብዙ ጥሮ ነበር፡፡ የተለያዩ ባለሙያዎችንም አማክሯል፤›› ያሉት ወ/ሮ አዜብ፣ ፕሮጀክቱ ዕውን ሊሆን በመቃረቡ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ሥራ ሲገባም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ትልቅ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ተነግሯል፡፡ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር አብሮ በመሥራትም አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንዲመጡ የሚያደርግ መሆኑን፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና አገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር በምታደርገው ጉዞ ላይ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የኤፈርት እህት ኩባንያ የሆነው ደጀና ኬሚካል ኢንጂነሪንግ የፕሮጀክቱ አስፈጻሚ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የደጀና ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሀፀይ በርሀ እንዳስታወቁት፣ ፕሮጀክቱ ከመነደፉ አስቀድሞ የገበያ ሁኔታና የጥሬ ዕቃ አቅርቦትን በተመለከተ ጥናት ተካሂዷል፡፡ በጥናቱ በአገሪቱ ለኬሚካል ምርት የሚጠቅሙ ጥሬዎች ዕቃ እንዳሏትና በቂ ገበያ መኖሩም ተረጋግጧል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ የመጡት የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ኢንዱስትሪዎችም ዓይነተኛ ገበያ መሆናቸው ታውቆ ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ተገልጿል፡፡
ሲኢሲ ግንባታውን በ30 ወራት እንደሚያጠናቅቅ በተርንኪይ አሠራር መሠረት አስፈላጊው ነገር ሁሉ ተሟልቶ በተባለበት ጊዜ እንደሚያስረክብም አስታውቀዋል፡፡ በዕለቱ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ፕሮጀክቱ ለበርካታ ዜጐች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ አስፈላጊውን ዕርዳታም እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1953 የተቋቋመው የቻይናው ሲኢሲ ኩባንያ እስካሁን በማማከር ሥራዎች፣ በዲዛይን፣ በፕሮጀክት ማኔጀርነት ዘርፎች በቻይናና በሌሎች አገሮች ከ50 የሚበልጡ ሥራዎችን መሥራቱ ታውቋል፡፡ በመይናማር፣ በኢንዶኔዥያ፣ በታይላንድ፣ በኢራን፣ በህንድ፣ በካናዳ፣ በኤርትራ፣ በቤላሩስ፣ በአልጄሪያ፣ በግብፅ ያከናወናቸው ፕሮጀክቶችም ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል፡፡ ‹‹የአገሪቱን ሕግ ተከትለን የገባነውን ኮንትራት እንፈጽማለን፤›› ያሉት የሲኢሲ ሥራ አስፈጻሚ ቼን ሼንግ፣ በስምምነቱ መሠረት ሥራውን በአግባቡ ከመወጣት ባለፈ የተለያዩ የቴክኒክ ሥልጠናዎች ለሠራተኞች እንደሚዘጋጁ አስታውቀዋል፡፡
በ1987 ዓ.ም. የተቋቋመው ኤፈርት ኢንቨስትመንት ግሩፕ በኢንቨስትመንት ሥራዎችና በሰብዓዊ ዕርዳታ ረገድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ተብሏል፡፡ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአገልግሎት፣ በእርሻ፣ በግንባታ፣ በማዕድንና በንግድ ላይ የተሰማሩ 13 ኩባንያዎችን በሥሩ ከፍቶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በማኑፋክቸሪንግ መስክ ሼባ ሌዘር ኢንዱስትሪ፣ ማይጨው ችፑድ ፋብሪካ፣ ብሩኅ ተስፋ፣ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ፣ መሰቦ ሲሚንቶ፣ አዲስ መድኃኒት ማምረቻ፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣ በሥሩ ከሚገኙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ትራንስ ኢትዮጵያ በአገልግሎት፣ ጉና ትሬዲንግ ሐውስ በንግድ፣ ሱር ኮንስትራክሽን በግንባታ፣ ኢዛና ማዕድንና ሳባ ድንጋይ በማዕድን ዘርፍ እንዲሁም ሕይወት የግብርና መካናይዜሽን በመካናይዜሽን መስክ የተሰማሩ የኤፈርት ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በኬሚካል ዘርፍ ሲሳተፍ የመጀመሪያው ሲሆን፣ ለግንባታ የሚያስፈልገውን ወጪ ከእናት ድርጅቱ ተቀማጭና ከባንክ ተበድሮ ለመሸፈን ማቀዱን ወ/ሮ አዜብ ገልጸዋል፡፡