ሚድሮክ ጎልድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ቡለን ወረዳ፣ ወርቅ ለማምረት የሚያስችለውን አዲስ ፈቃድ ሊሰጠው ነው፡፡
የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሚድሮክ ወርቅ በክልሉ ሲያካሂድ የቆየውን የአዋጭነት ጥናት አጠናቆ ፈቃድ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቧል፡፡
‹‹ሚድሮክ ወርቅ ያቀረበው የአዋጭነት ጥናት የተሟላ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ፈቃዱን ይሰጠዋል፤›› በማለት አቶ ቶሎሳ አረጋግጠዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በደርግ ዘመን የለማውን የለገደንቢ የወርቅ ማዕድን ከቀድሞ ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በ172 ሚሊዮን ዶላር ግዥ በመፈጸም የኢትዮጵያን ማዕድን ዘርፍ የተቀላቀለው ሚድሮክ ወርቅ፣ የወርቅ ግኝቶችን በማስፋት ላይ ይገኛል፡፡
ከለገደንቢ በተጨማሪ በዚሁ ጉጂ ዞን ሳካሮ አካባቢ ሁለተኛውን የወርቅ ማውጫ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ግንባታ በመግባት ላይ ይገኛል፡፡
ሚድሮክ ከሁለቱ ወርቅ ማውጫዎች በተጨማሪ በወርቅ ማዕድን ፍለጋ በስፋት በመግባት በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ ላለፉት አሥር ዓመታት ፍለጋ በማካሄድ፣ በግንቦት 2007 ዓ.ም. የሚድሮክ ሊቀመንበር ሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በተገኙበት በይፋ ክምችት መገኘቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ቡለን ወረዳ ሲካሄድ በቆየው የአዋጭነት ጥናት መሠረት፣ በዓመት 2,300 ኪሎ ግራም ወርቅ ማምረት ይቻላል፡፡ በዓመት ከዚህ የወርቅ ወጪ ንግድ 87.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝ የሚድሮክ ወርቅ ጥናት መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህም ከገቢ ግብርና ከሮያሊቲ መንግሥት በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር የሚያገኝ ከመሆኑ በላይ፣ ለ620 ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ሚድሮክ ጎልድ ይህንን ሥራ ለመጀመር 200 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት የሚያደርግ መሆኑ፣ ወርቁን ለማምረት ወቅቱ ያፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚጠቀም በጥናቱ ተገልጿል፡፡
ሚድሮክ ጎልድ በመተከል ዞን ባገኘው የወርቅ ፍለጋ ፈቃድ ሦስት ቦታዎች ላይ በዋናነትም ጀላይ፣ ፌቲንና ቻሎ በተባሉ ቦታዎች ፍለጋውን አከናውኗል፡፡
በእነዚህ ቦታዎች ላይ ባካሄደው ጥናት በአጠቃላይ 50.6 ቶን የወርቅ ክምችት ማግኝቱን አስታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብቸኛው የወርቅ ኢንዱስትሪ ባለቤት የሆነው ሚድሮክ ጎልድ ይህንን የወርቅ ፍለጋ ካገኘ ሦስተኛው ማዕድን ጣቢያ ይሆንለታል፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር ባለፉት ስምንት ወራት 3,066.67 ኪሎ ግራም ወርቅ ወደ ውጭ ለመላክ አቅዶ 2,754.93 ኪሎ ግራም ወርቅ መላክ ችሏል፡፡ ዕቅዱን 89.83 በመቶ ማሳካት የቻለ ቢሆንም፣ ይህም የተገኘው ከሚድሮክ ለገደንቢ ወርቅ ማውጫ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ዓመት ዓለም አቀፉ የወርቅ ገበያ ዋጋ የወረደ (አንድ ወቄት 1,000 ዶላር) በመሆኑ፣ የዘርፉን ተዋናዮች ትኩረት መሳብ ባለመቻሉ የተላከው በሚድሮክ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
ከሚድሮክ ጎልድ በተጨማሪ በኤፈርት ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሥር የሚገኘው ኢዛና ማይኒንግ በትግራይ ክልል የከፍተኛ ወርቅ አምራችነት ፈቃድ አግኝቷል፡፡ በመቀጠል የእንግሊዝ ኩባንያ ከፊ ሚኒራልስ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ቱሉ ካፒ አካባቢ የወርቅ ክምችት አግኝቷል፡፡ ኩባንያው የአዋጭነት ጥናት አካሂዶ ለማዕድን ሚኒስቴር በማቅረብ ወርቅ የማምረት ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፣ የከፍተኛ የወርቅ አምራችነት ፈቃድ በማግኘት ከኢዛና ቀጥሎ ከሚድሮክ ቀጥሎ ሦስተኛው ኩባንያ ሆኗል፡፡