Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይና ባንክ የጊቤ አራት ግንባታን ፋይናንስ ለማድረግ ፍላጎት አሳየ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ ለመረከብ ጫፍ በደረሰበት ወቅት፣ የቻይና ኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ (ICBC) የፕሮጀክቱን ኤሌክትሮ ሜካኒካልና ኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች ለአገሩ ኩባንያ ለዶንግፋንግ የሚሰጥ ከሆነ ፋይናንስ ለማቅረብ ፍላጎቱን አሳየ፡፡

የቻይናው የፋይናንስ ተቋም መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ለገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጻፈው ደብዳቤ፣ የጊቤ አራት ኤሌክትሮ ሜካኒካልና ኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች ለዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን የሚሰጥ ከሆነ፣ የፕሮጀክቱን 85 በመቶ ፋይናንስ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

የቻይናው የፋይናንስ ተቋም ለግልገል ጊቤ ሦስት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ፕሮጀክት ለኃይድሮ ሜካኒካልና ለኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ፋይናንስ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ሥራ ይህ የቻይና ፋይናንስ ተቋም 500 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ያቀረበ ሲሆን፣ ሥራዎቹን ያከናወነው ዶንግፋንግ ኤሌክትሪክ ኢንተርናሽናል ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡

የጊቤ ሦስት ቀጣይ የሆነውን ጊቤ አራት በተመሳሳይ ዶንግፋንግ የሚገነባው ከሆነ፣ የፕሮጀክቱን ሜካኒካል ሥራዎች ፋይናንስ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ በኢትዮጵያ መንግሥት በጀት፣ ዶንግፋንግ ደግሞ ከቻይና ባመጣው ፋይናንስ የተገነባው ጊቤ ሦስት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት 540 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ሥራውን ጀምሯል፡፡

ጊቤ አራት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት ገንዘብ ካመጣ ብቻ ሥራው እንደሚሰጠው የተገለጸለት ሳሊኒ፣ ብድር ሊያስገኝ የሚችለውን ዋስትና ከጣሊያን ብድር ዋስትና አገልግሎት ተቋም (SACA) በማምጣት ፕሮጀክቱን ለመረከብ መቃረቡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ሳሊኒ ብድር የማግኘት መተማመኛ በማቅረብ የወለድ ምጣኔ፣ የብድር መክፈያ እፎይታ ጊዜ፣ የፍሬ ብድር መክፈያ ወቅትና የኢንሹራንስ ሁኔታው በመታየት ላይ እንደሚገኝ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የሳሊኒ ፍላጎት ሙሉ ሥራውን መረከብ (ተርንኪይ) መሆን አለመሆኑን ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ የጊቤ ሦስት ቅርፅ የሚይዝ ከሆነ ዶንግፋንግ ጊቤ አራት ላይ ሥራ እንደሚያገኝ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ጊቤ አራት 2,200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመንግሥታቸውን የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት፣ በቅርቡ 2,200 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ለቻይናው የፋይናንስ ተቋም መንግሥት እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች