Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፍትሕ ሥርዓቱ ከስያሜ ባሻገር ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል!

 ሰሞኑን ለፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ የተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ሙሉ በሙሉ እንደ አዲስ ለሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚሰጥ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በመስከረም ወር ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ የፀደቀውን አዋጅ ቁጥር 916/2008 አንቀጽ 16 ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጡትን ሥልጣንና ተግባር ሙሉ ለሙሉ ለአዲሱ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ይሰጣል፡፡ በዚህ መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር ህልውናው ያከትማል ማለት ነው፡፡ ምንም እንኳ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ኮሚቴ በፓርላማው ቢመራም፣ ወደፊት በጉዳዩ ላይ በርካታ ውይይቶችና የውሳኔ ሐሳቦች እንደሚቀርቡ ታሳቢ በማድረግ ጠቃሚ ጉዳዮችን እናነሳለን፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ከስያሜ ባሻገር ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋልና፡፡

የፍትሕ ሥርዓቱ (ሕግ ተርጓሚው) ከሕግ አውጪው ፓርላማና ከአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ጋር እየተናበበ፣ ሕዝቡ ፍትሕና ርትዕ ያገኝ ዘንድ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በዳይን ከመቅጣት፣ ተበዳይን ከመካስ በላይ በሕዝብ ዘንድ የሚያከናውናቸው ተግበራት በአትኩሮት ነው የሚታዩት፡፡ ፍርድ ቤቶች በነፃነትና በኃላፊነት ስሜት ነው ወይ የሚሠሩት? ዓቃቢያነ ሕጎች ሥራቸውን ያለማንም ጣልቃ ገብነት ያከናውናሉ ወይ? የመርማሪ ፖሊሶች ባህርይና ሥነ ምግባር ምን ይመስላል? ማረሚያ ቤቶች ሰብዓዊ መብት ያከብራሉ ወይ? የጠበቆችን ሥነ ምግባር ተቆጣጣሪ አለ ወይ? ወዘተ. የመሳሰሉት የፍትሕ ሥርዓቱን ገጽታ ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡

አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ የፍትሕ ሥርዓቱ ያለበት ደረጃ በጣም አስፈሪ ነው፡፡ ዜጎች ፍትሕ አጥተው አቤት እያሉ ሲጮሁና መፍትሔ ጠፍቶ አገር ስትተራመስ ነው የሚታየው፡፡ ሕዝብ ለፍትሕ ሥርዓቱ ያለው ምልከታ በጣም አሳዛኝ ከመሆኑ የተነሳ በየቦታው የፍትሕ ያለህ ነው የሚባለው፡፡ በሥነ ምግባራቸው ምሥጉን የሆኑ ያሉትን ያህል፣ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የተሰገሰጉ አጥፊዎች ሕዝብን መቆሚያ መቀመጫ አሳጥተዋል፡፡ ዳኞች በነፃነትና በኃላፊነት መንፈስ ሥራቸውን ማከናወን ሲያቅታቸውና ያለ ጉቦ መንቀሳቀስ ሲሳናቸው፣ ዓቃቢያነ ሕጎች ሥራቸውን በነፃነት ማከናወን አቅቷቸው የበላይ አካል ትዕዛዝና ጉቦ አላላውስ ሲላቸው፣ መርማሪ ፖሊሶች ሥነ ምግባር የሚባል አንጥፍጣፊ ከውስጣቸው አልቆ ያልተገባ ድርጊት ሲፈጽሙ ፍትሕ ቢጠፋ ምን ይገርማል? መንግሥት ሰሞኑን ከመልካም አስተዳደር ችግሮች ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ሳይቀር ከሥራ ማሰናበትና በሕግ የመጠየቅ ተግባር ውስጥ እየገባ ያለው፣ የሕዝቡ ምሬት ከመጠን በላይ በመሆኑ ነው፡፡ በአስፈጻሚው መንግሥት ውስጥ ባሉ ጉልበተኞችና ኃላፊነት በማይሰማቸው ወገኖች ምክንያት የፍትሕ ሥርዓቱ ብልሽትሽቱ መውጣቱ መታመን አለበት፡፡

በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የወጡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ የአገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ነው፡፡ ዜጎች ፍትሕ ፍለጋ ወደ ፍርድ ቤቶች ሲሄዱ የሚቀበሉዋቸው ጉቦ አቀባባይ ደላሎች ናቸው፡፡ ሕግ በትክክል እየተተረጎመ ፍትሕ መስፈን ሲገባው ገንዘብ በአቋራጭ ፍትሕ ይገዛል፡፡ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን አሳዛኝ ድርጊት እያየ በፍትሕ ሥርዓቱ ተስፋ ቢቆርጥና በመንግሥት ላይ አመፅ ቢያነሳ ምን ይገርማል? ከፖሊስ ጣቢያ ጀምሮ እስከ ፍርድ ቤት ድረስ ሕገወጥነትን የሚያበረታቱ ተግባራት ከበዙ ፍትሕ አደጋ ውስጥ ይገባል፡፡ በእርግጥም አሁንም አደጋ ውስጥ ነው ያለው፡፡ ተበዳይ ፍትሕ ማግኘት ሲገባው ወንጀለኛ በአደባባይ በነፃነት ከተንጎማለለ ለአገር ጭምር አደጋ ነው፡፡ ፍትሕን በገንዘባቸውና በሥልጣናቸው የሚያሽከረክሩ ሲበዙ ደግሞ የሕግ የበላይነት ጠፍቶ ሥርዓተ አልበኝነት ይፈነጫል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ሥር ነቀል ለውጥ የሚያስፈልገው ሕገወጥነት በመብዛቱ ነው፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ መሆን ያለበት ለፍትሕ ሥርዓቱ ከስያሜ በላይ መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል? ወይስ አያስፈልገውም? የሚለው ነው፡፡ ለዝርዝር ዕይታ የተመራው ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ከቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ጋር ሲመለስ፣ የመስኩ ባለሙያዎችና ይመለከተናል የሚሉ አካላት በነፃነት ድምፃቸውን ማሰማት አለባቸው፡፡ የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንና ተግባራት የነበሩ ኃላፊነቶች ሙሉ በሙሉ ለሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላላ ዓቃቤ ሕግ ሲሰጡ፣ በተለያዩ ተቋማት ተበታትኖ የነበረው የዓቃቤ ሕግነት ሥራን እንዲረከበው ሲደረግ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የታዩ ምስቅልቅሎችም መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሚቋቋመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በሕግ ጉዳዮች የፌዴራል መንግሥት አማካሪና ተወካይ ሆኖ እንደሚሠራ በረቂቅ አዋጁ ላይ በመቀመጡ፣ ካሁን በኋላ ፍትሕ ሚኒስቴር እንደማይኖር ማመላከቻ ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት ሕዝብን ሲያንገፈግፉ የነበሩ ጉዳዮች መቀጠል የለባቸውም ማለት ነው፡፡ ማንም እየተነሳ እከሌን ክሰስ እከሌን አትክሰስ የሚለው ተቋም ሳይሆን፣ በረቂቅ ማብራሪያው እንደተቀመጠው የሕዝብን ጥቅም በጥንካሬ ማስከበር አለበት፡፡ ከስያሜው በላይ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጣ የግድ ይለዋል፡፡

ፍትሕ የትክክለኝነት ማሳያ ነው፡፡ ፍትሕ የሕግ የበላይነት መስፈን ማረጋገጫ ነው፡፡ ፍትሕ የነፃነት ምልክት ነው፡፡ ፍትሕ ለሁሉም ተደራሽ ሲሆን፣ ዜጎች የሕግ ጥበቃና ከለላ እንዳላቸው ይሰማቸዋል፡፡ ፍትሕ የሰፈነበት ኅብረተሰብ ለሕገወጥነት ቦታ የለውም፡፡ ፍትሕ የዘገየበት ወይም የተነፈገ ዜጋ የሚታየው አመፅ ብቻ ነው፡፡ ፍትሕ ሲሰፍን ግን ዜጎች የአገር የባለቤትነት ስሜታቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡ የሀብት ክፍፍሉ ፍትሐዊ ይሆናል፡፡ ሙስና አደብ ይገዛል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይወገዳሉ፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን የፍትሕ ሥርዓቱ የተወረረው በደላሎችና በአቀባባዮች ነው፡፡ በሕግ የበላይነት የማያምን ሹም በትዕዛዝ ፍትሕን ይንዳል፡፡ ዓቃቢያነ ሕጎችን እያስገደደ ዜጎችን ያሰቃያል፡፡ ለህሊናቸው ያልተገዙ ዓቃቢያነ ሕጎች የሹማምንት ተላላኪ ይሆናሉ፡፡ በጉቦ ይጠለፋሉ፡፡ በሕጉና በህሊናቸው ተመርተው መሥራት ያለባቸው ዳኞች ፍርድ ይጓደላሉ፡፡ ሥነ ምግባር የሌላቸው መርማሪዎች መረጃ ያጠፋሉ፡፡ ማስረጃ ይሰውራሉ፡፡ በስመ ምርመራ ለበርካታ ጊዜያት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እየጠየቁ ዜጎችን እስር ቤት ያማቅቃሉ፡፡ ዜጎች በሕግ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋሉ፡፡ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ታሳሪዎች ይደበደባሉ፡፡ ምግብ፣ መድኃኒት፣ ጠበቃ፣ የሃይማኖት አባትና ቤተሰብ እንዳያገኙ ይደረጋሉ፡፡ የሕገወጥነት ማሳያ የሆኑ በርካታ አሳዛኝ ችግሮች በስፋት ይታያሉ፡፡ ከስያሜ ባሻገር ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡

በየቦታው ብሶቶች በብዛት የሚሰሙት ለሕግ የበላይነት ደንታ በሌላቸው ሹማምንትና በፍትሕ ሥርዓቱ ሰዎች በርካታ በደሎች ስለሚደርሱ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም ሆኑ የሚመለከታቸው ወገኖች በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲነጋገሩ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉትን መጠነ ሰፊ ችግሮች በድፍረት ሊያነሱዋቸው ይገባል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ በችግሮች ተተብትቦ መራመድ እየተሳነው ስለሆነ፣ ለሥር ነቀል መሠረታዊ ለውጥ መነሳት ግዴታ ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚገነባው፣ ሰብዓዊ መብት የሚከበረው፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ የሚቻለው፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የሚኖረው፣ ያለ አድልኦ መዳኘት የሚቻለው፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ የሚሰፋው፣ ወዘተ የፍትሕ ሥርዓቱ ጠንካራ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ነፃነቱ የተጠበቀ፣ ከአድልኦ የፀዳ፣ ሙስናን የሚታገልና ጠንካራ እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ፍትሕ ጥቂቶች የሚፈነጩበት ብዙኃን አንገታቸውን የሚደፉበት መሆን የለበትም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሳፋሪ ተግባር በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የሕዝብ አገልጋይ ይሁን፡፡ ይህንን መልካም ምኞት ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ግን ከስያሜ ባሻገር ሥር ነቀል ለውጥ ሲደረግበት ነው!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...