Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየድርቁ ተጎጂዎች ቁጥር ሊከለስ ነው

የድርቁ ተጎጂዎች ቁጥር ሊከለስ ነው

ቀን:

– መንግሥት በድርቅ አካባቢዎች ለውኃ ፍላጎት 1.5 ቢሊዮን ብር መድቧል

በታኅሳስ ወር 2008 ዓ.ም. የተገለጸው የ10.2 ሚሊዮን የድርቅ ተጎጂዎች ቁጥር በድጋሚ ሊከለስ ነው፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ዳይሬክተር ጀረሚ ኮኒዲክ በድርቅ የተጎዱ የተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችን ከጎበኙና ከአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ በሰጡት መግለጫ፣ መንግሥት የተጎጂዎች ቁጥርን እንደሚከልስ ጠቁመዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከፌዴራል መንግሥትና ከክልል መንግሥታት የተውጣጡ ባለሙያዎች የድርቁ ተጎጂዎች ቁጥር ሁኔታን እያጠኑ መሆኑ ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ውስጥ የሚካተቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች፣ መሬት ላይ ያለው ሁኔታና በቅርብ ክትትል የሚገኙ መረጃዎች እንደሆኑ ተጠቁመዋል፡፡ በተለይም ወቅቱ የበልግና የዝናብ ወቅት በመሆኑ በበልግ አዝመራ ግምገማ ላይ መመሥረት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የበልግ ዝናብ ጥሩ ካልሆኑ የተረጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል፣ ጥሩ ከሆነ ግን በተቃራኒው የተጎጂዎች ቁጥር ሊቀንስ እንደሚችል አክለዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ድንገተኛ አደጋ ዕርዳታ ዳይሬክተር ሚስተር ጀረሚ በበኩላቸው፣ የድርቁ ሁኔታ እስከ መስከረም ወር ድረስ አሳሳቢ እንደሚሆንና በዚህ ወቅት ለሚያስፈልገው የዕርዳታ ፍላጎት መዘጋጀት ይገባል ብለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብና እርሻ ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ ይጠበቅ የነበረው የበልግ ዝናብ መዘግየቱን በመግለጽ እስከመጪው የመኸር ወቅት ድረስ አስፈሪ ችግር መደቀኑን ገልጿል፡፡

ዋነኛው የመኸር ዝናብ ወቅት በኤልኒኖ ክስተት ሳቢያ በበርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ዝናብ ባለመዝነቡ የተረጂዎች ቁጥር 10.2 ሚሊዮን መድረሱን የሚገልጸው የተመድ የምግብና እርሻ ድርጅት፣ ይህ የመኸር ወቅት የአገሪቱን የምግብ እህል 75 በመቶ የሚሸፍን እንደሆነ ጠቁሟል፡፡

ቀሪው የእህል ፍላጐት የሚሟላው በበልግ ወቅት የእርሻ ሥራ በመሆኑና የበልግ ወቅት ዝናብም በመዘግየቱ፣ እስከመጪው መስከረም ያለው ወቅት ከባድ ፈተና እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡

በድርቁ ተጐጂ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችና የቤት እንስሳቶቻቸው በአስከፊ ደረጃ የተቸገሩት በውኃ እጦት መሆኑን የምግብና እርሻ ድርጅቱ ይገልጻል፡፡ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የቤት እንስሳት መሞታቸውንም ጠቁሟል፡፡ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ባለፈው ሐሙስ በፓርላማ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት የውኃ ችግሩን ለመቅረፍ 1.5 ቢሊዮን ብር መመደቡን ገልጸዋል፡፡

ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ 122 ውኃ መሳቢያ ጄኔሬተሮችና 117 ፓምፖች ችግሩ በታየባቸው አካባቢዎች መከፋፈላቸውን፣ በዘላቂነትም የውኃ ችግሩን የሚቀርፉ 379 አዲስ ጉድጓዶች መቆፈራቸውን አስረድተዋል፡፡ የውኃ ጉድጓዶች በደረቁበት ወይም በሌሉበት አካባቢ ደግሞ መንግሥት 209 የውኃ ቦቴዎችን አሰማርቶ ውኃ በመቅረብ ላይ መሆኑን፣ ሰሞኑንም ዩኒሴፍ ተጨማሪ 100 ቦቴዎችን ማሰማራቱን ገልጸዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ