Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በርካታ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸው መጨናነቅ ተፈጠረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አገሪቱን ለኪሳራ ይዳርጋል ተብሏል

ከውጭ የተገዙ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ በመድረሳቸው፣ በጂቡቲ ወደብ ከፍተኛ መጨናነቅ ተፈጠረ፡፡ ወደብ የደረሱትን ዕቃዎች በፍጥነት ማንሳት ባለመቻሉ አገሪቱን ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ክፍያ እንደሚዳርግ ተመለከተ፡፡

በአሁኑ ወቅት ሦስት መርከቦች በተመሳሳይ ሰዓት ዕቃ ሲያራግፉ፣ ከ20 በላይ የሚሆኑ መርከቦች ዕቃ ለማራገፍ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ መርከቦች በየዕለቱ ወደ ወደቡ እየደረሱ ሲሆን፣ የጫኑትን ዕቃ በፍጥነት ማንሳት አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በአገሪቱ የሚገኙ 9,000 ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ ጂቡቲ ወደብ ተንቀሳቅሰው ስንዴና ማዳበሪያ እንዲያጓጉዙ ብሔራዊ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በዚህ ጥሪ መሠረት በአገሪቱ የሚገኙ የከባድ ተሽከርካሪ ባለንብረቶች በሙሉ ወደ ጂቡቲ ወደብ መንቀሳቀሳቸው ታውቋል፡፡ መንግሥት በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ግዢ መፈጸሙ ይታወቃል፡፡ ይህ ስንዴ በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ወደብ ደርሷል፡፡ በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከተገዛው ስንዴ በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ዋጋ ለማረጋጋት በመቶ ሺሕ ቶን የሚቆጠር ስንዴ በማስገባት ላይ ይገኛል፡፡ ከስንዴ በተጨማሪ በተያዘው ምርት ዘመን መንግሥት 812 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ በሁለት ዙር ጨረታዎችን ፈጽሟል፡፡ ይህ ማዳበሪያም በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ መድረሱ ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች ዝናብ እየጣለ በመሆኑ ማዳበሪያውን ማስገባት አጣዳፊ በመሆኑ፣ በትራንስፖርት ብሔራዊ ኮሚቴ ታምኖበት ቅድሚያ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ከእነዚህ ሁለት ገቢ ዕቃዎች በተጨማሪ ለረዥም ጊዜ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በማጋጠሙ፣ ከወራት በፊት መንግሥት ከራሱ የገንዘብ ምንጮች 2.5 ቢሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ለንግዱ ማኅበረሰብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ይህንን የውጭ ምንዛሪ የተጠቀሙ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት የገዟቸው ብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ጂቡቲ ወደብ መድረሳቸው ታውቋል፡፡ እነዚህ ዕቃዎች በተመሳሳይ ወቅት ወደብ መድረሳቸው የጂቡቲ ወደብን ከማጨናነቃቸው በተጨማሪ፣ የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ድርጅት ሊሸከመው ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ በአገር ውስጥ ያሉት ከባድና ድንበር ተሻጋሪ ተሽከርካሪዎች የተከማቹትን ዕቃዎች በፍጥነት ማንሳት ስለሚያዳግታቸው መንግሥት ከጎረቤት ሱዳን ዕርዳታ ለማግኘት እየጣረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ መንግሥት ከሱዳን በርካታ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ተከራይቶ ከሱዳን ወደብ ወደ ጂቡቲ ወደብ በማንቀሳቀስ የመፍትሔው አካል ለማድረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቷል፡፡

የዲሜሬጅ ክፍያ ያሠጋቸውና በተለያዩ ጨረታዎች ተሳትፈው አሸናፊ የሆኑ የግል ኩባንያዎች፣ ከስንዴና ከማዳበሪያ ጎን ለጎን የእነሱም ዕቃዎች ሊጓጓዙ እንደሚገባ እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡

በሎጂስቲክ ተዋናዮች አካባቢ የገቢ ንግድ በፕሮግራም የማይመራበት ምክንያት አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ገቢ ዕቃዎች በየትኛው ጊዜ እንደሚገቡ ቀደም ብሎ ቢታወቅና ዕቅድ ቢወጣ፣ አገሪቱ ለከፍተኛ ወጪ እንዳትዳረግ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ማሪታይምስ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አበራ አስተያየት እንዲሰጡ ሪፖርተር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች