ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎች ጋር የጋራ ምክር ቤቱን በማጠናከር፣ የምርጫ ሕጎችና አዋጆች በሚሻሻሉበትና በብሔራዊ መግባባት አጀንዳዎች ላይ መጋቢት 14 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ተወያዩ፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ አባል የሆኑም ያልሆኑም ፓርቲዎች ውይይቱን በተመለከተ የተለያዩ አቋሞች አንፀባርቀዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የጋራ ምክር ቤቱ አባላት ከሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምክር ቤቱን ማጠናከር ስለሚቻልበት፣ እንዲሁም በብሔራዊ መግባባትን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም የጋራ ምክር ቤቱ እንዲጠናከር መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ገልጸው፣ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተም እንዲሁ ልዩነቶች እንደተጠበቁ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መሥራት እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼን ቢሉም፣ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የሆኑም ያልሆኑም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በውይይቱ ላይ የተለያየ አቋም እያራመዱ ነው፡፡
‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተያየት ከፍተኛ የሆነ አድልዎ ያለበት ነው፡፡ በተለይ ገንዘብን በተመለከተ ባደረጉት ንግግር የምክር ቤት አባላት ለሆኑ ፓርቲዎች የተወሰነ ገንዘብ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡ ይኼ ማለት ደግሞ ፓርቲዎችን የምክር ቤቱ አባል ለማድረግ የሚያስገድድ አሠራር ነው፤›› በማለት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ ሲናገሩም፣ ‹‹አገር ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ ነገር ግን ብሔራዊ እርቅ የሚመጣው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሉት መሠረት ሳይሆን፣ ሁሉም የሲቪክ ማኅበረሰብ አባላት፣ ፓርቲዎችና ሌሎች ያገባናል የሚል ወገን ሁሉ ተሰብስበው መሆን አለበት፡፡ ይኼ ግን ሊሆን አልቻለም፡፡ እነሱን በሚያመቻቸው መንገድ ብቻ ማድረጉ ለአገሪቱ ዘላቂ ሰለም ሊያመጣ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ያገባኛል የሚል አካል ሁሉ መሳተፍ አለበት፤›› ብለዋል፡፡
በተመሳሳይ የሰማያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ‹‹የተካሄደው ውይይት ለገዥው ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ከመሥራት የዘለለ ምንም ፋይዳ የለውም፤›› ብለው በጋራ ምክር ቤቱ የሚሳተፉ ፓርቲዎችም ኢሕአዴግን ከማጀብ የዘለለ ምንም ድርሻ እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡
‹‹የጋራ ምክር ቤቱ አባላት የሚባሉት ከኢሕአዴግ ገንዘብ የሚቆረጥላቸው ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ይኼ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ ግንባታ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ የሌለው ነው፤›› ሲሉ ውይይቱንና የውይይቱን ተሳታፊ ፓርቲዎች ክፉኛ ተችተዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባት የሚለው ጉዳይም ቢሆን መንግሥትና ፓርቲዎቹ በሚሉት መንገድ የሚፈታ እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡ ‹‹አገሪቱ ውስጥ በርካታ ችግሮች በየሥፍራው እየተከሰቱ ባሉበት ሁኔታ ዝም ብሎ ብሔራዊ መግባባት ማለት ቀልድ ነው፤›› በማለት ብሔራዊ መግባባት በንግግር ሳይሆን በተግባር ሊገለጽ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
‹‹የጠቅላይ ሚኒስትሩና የፓርቲዎቹ ውይይት ምንም አዲስ ነገር የለውም፡፡ አገሪቷ ውስጥ የተከሰተውን ችግር አስመልክተው እንኳን አልተወያዩም፡፡ ስለዚህ ጠቀሜታው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፤›› በማለት የተከራከሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ናቸው፡፡
‹‹አገሪቱ የምትፈልጋቸው አንገብጋቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አሉ፡፡ ነገር ግን የተደረገው ውይይት ከዚህ ቀደም የሚያደርጉት ዓይነት ውይይት ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባትን አስመልክቶ የተደረገው ውይይትም ቢሆን ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው እንዳልሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ብሔራዊ መግባባት የሚባለው ተጨባጭ በሆኑ በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ውይይት እንጂ፣ በአንድ የተወሰነ ጉዳይ ላይ ተከልሎ የሚደረግ ውይይት መሆን የለበትም፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በበኩላቸው፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጋራ ምክር ቤቱ መጠናከር እንዳለበትና መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ የያዘውን አቋም አወንታዊ በሆነ መልኩ ተመልክተነዋል፤›› ብለዋል፡፡
ብሔራዊ መግባባትን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡት ቃል ሲፈጸም ለማየት በተስፋ እንደሚጠብቁም እንዲሁ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ቃል የተገቡ ነገሮች በተግባር ሲፈጸሙ አለማስተዋላቸውን በመግለጽ፣ አሁንስ ኢሕአዴግን እንዴት ማመን ይቻላል የሚል ጥያቄ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን የገለጹት ዶ/ር ጫኔ፣ መንግሥት ቁርጠኛ ነው የሚል ምላሽ ማግኘታቸውንና ይኼንንም በተስፋ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡
‹‹ውይይቱ በአጠቃላይ ሲታይ ስምምነት የተደረሰበት ነው፤›› በማለት የገለጹት የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፣ ‹‹በቀጣይም አገራዊ መግባባት በመፍጠር በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የክርክር መድረኮችና ኮንፈረንሶች እየተዘጋጁ ፓርቲዎች ተሳትፏቸው እንዲጠናከር ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ ያካተተው የኢሕአዴግን የሚያጅቡ ፓርቲዎችን ብቻ እንጂ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አባል አይደሉም ለሚለው ወቀሳ፣ ‹‹የምክር ቤቱ አባላት በሰላማዊ መንገድና በመቻቻል ፖለቲካ ላይ ልዩነቶቻችን ተጠብቆ እንሠራለን ብለው ያመኑ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሕገወጥትነትን እያጣቀሱ በሥነ ምግባር መገዛት የማይፈልጉ ደግሞ ምክር ቤቱ ውስጥ አልገቡም፡፡ ልዩነቱ ይኼ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ኢሕአዴግ ሲፈልግ የሚያስገባው ሲፈልግ ግን የሚያስወጣው ፓርቲ የለም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስምንት ፓርቲዎችን በአባልነት የያዘ ነው፡፡ በአገሪቱ ዋነኛ የሚባሉት መኢአድ፣ ሰማያዊና መድረክ በአባልነት አይሳተፉበትም፡፡
የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ፓርቲዎች የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 662/2002ን መፈረም ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ መድረክና ሰማያዊ ያሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አዋጁ የኢሕአዴግን ሐሳብ የሚያንፀባርቅ በመሆኑ፣ ሁሉም ፓርቲዎች በእኩልነት ተነጋግረው የሚያፀድቁት ሌላ የሥነ ምግባር ሕግ እንዲረቀቅ ይጠይቃሉ፡፡