በኢትዮጵያ ጥንተ ህልውና
በክብረ ወሰኗም ÷ ሀብተ ብልፅግና
ታፍሮና ተከብሮ ÷ ጥንቱን እንደ ጸና
የሕዝቡ ህሊና፤
ጥርጣሬ የለው ÷ እንበለ ምስጋና
ላበው ተጋድሎ ÷ መዋዕለ ዜና፡፡
ግና፣
ዓለም ወረተኛ ÷ ፍቅሯም ውስጠ ወይራ
ዓይነ ዓዋጅነቷም ÷ የለው ባለ ጋራ፡፡
ውበት ደም ግባቷ ÷ ወትሮ እየጎላ
ቢያማልል ወንድ ሁላ ÷ ቢያስቀና ሴት አውላ፤
ቀልቡ መች ይዞለት ÷ ፍላጎቱ ይሞላ
‘ሚያነሳ ‘ሚጥለው ÷ ደግሞ ሌላ ሌላ፡፡
የምድሩ ልምላሜ ÷ ያየሩ ጠባይ
ጋራ ሸንተረሩ ÷ መልኩ አማላይ
ወዙም ጥርት ብሎ ÷ ከመ ገጸ ማይ
የሰው ፊት ያሳያል ÷ ለሱስ ባይታይ፡፡
ያቺ የንጋት ጀንበር ÷ ያቺ ብሩህ ፀሐይ
የምትመላለስ ÷ መች ያለ ጉዳይ
ጎሕ ሲቀድ ማለዳ ÷ ወገግ ሲል ሰማይ
የቀኑም አባዜ ÷ የሰዉም ይለይ፡፡
ሠርክ ኾነ ማለዳ ÷ ቀንም ኾነ ማታ
እየተዟዟረ ÷ የጊዜው ኹኔታ
በቀድሞ ይዞታ ÷ በኖረበት ቦታ
ቢሹት የሚያገኙት ÷ አገሬ እንዴታ!
- ኃይለ ልዑል ካሣ
(ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም.)