በጥንታዊ የግሪክ አፈታሪክ ፓንዶራ በምድር ላይ የመጀመሪያዋ ሴት ነበረች። የአማልክት አምላክ ዜዑስ፡ የጥበብ አምላክ የሆነችውን ሔፋስቱስ፡ ፓንዶራን ከምድር አፈርና ውኃ አድቦልቡላ ትሠራት ዘንድ አዘዛት። ሌሎች አማልዕክትም እንደየችሎታቸው ለፓንዶራ ስጦታ አበረከቱላት—አፍሮዳይት ቁንጅናን፣ አፖሎ ሙዚቃ፣ ሔርመስ ደግሞ የንግግር ችሎታን ሰጧት። ስሟ ፓንዶራም ትርጉሙ ‹‹ሁሉ–የተሰጣት›› ማለት ነው።
ፕሮሚትየስ ከገነት እሳትን በሰረቀ ግዜ፣ ዜዑስ ተቆጣ፤ ብቀላም ይሆን ዘንድ ፓንዶራን አሳልፎ ለፕሮሚትየስ ወንድም ሰጠ። ፓንዶራም በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን እንድትከፍት ያልተፈቀደላት ትንሽ ሳጥን ተሰጣት። ይሁን እንጂ በተፈጥሮ አለቅጥ የተቸራት ጉጉቷ በዛና ፓንዶራ ያንን ሳጥን ከፈተችው። ነገር ግን በሳጥኑ ተከድኖ ተቀምጦ የነበረው ‹‹ክፋት›› ከሳጥኑ አምልጦ ወጣ፤ በመላው ምድርም ተሰራጨ። ፓንዶራ ተቻኩላ ሳጥኑን ለመዝጋት ሞከረች፤ ነገር ግን በሳጥኑ ውስጥ የነበረው ሁሉ ድሮ ወጥቶ አልቋል—ከአንድ ነገር በስተቀር። ያም ‹‹ተስፋ›› ነበር። ፓንዶራ በሠራችው ሥራ ሁሉ አዘነች፤ ተጸጸተችም። የተጣለባትን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣቷ የዜዑስን የቁጣ ውርጅብኝ በፍርኅት መጠባበቅ ጀመረች። ዜዑስ ግን አልቆጣትም—ይህ እንደሚሆን ያውቅ ነበርና።
ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው ‹‹ቡክ ፎር ኦል››