Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ድንጉጥነት መደመር በጥበብ ሠፈር

በፍፁም ይላቅ

ጥሩ አርቲስት የማይደነግጥ ትዕቢተኛ ነው፡፡ ትዕቢቱ ግን የልብ ጥመት ያለበትና በመጽሐፉ ያጠፋል የተባለው ዓይነቱ ሳይሆን የመንፈስ እንቢተኝነት፣ በነፍሱ የማዘዝና ተራ ነገሮችን የመናቅ ድፍረትን ያዘለውን ነው፡፡ ድንጉጥ ሰው ጥሩ አርቲስትነት ትን ይለዋል፡፡ መደንገጥ ሲባል በዛቻ የሚመጣ ላብ መጠመቅ ብሎ መተርጎም እዚጋ እንዳይመጣ፡፡ ለመደንገጥ ያለን አቅም ካለመረዳት፣ የያዙትን የሙያ መሣሪያ ፈቶ መግጠም ካለመቻል፣ በክህሎት ሳይሆን በቸርነት የሚመጣን ካባ መሞቅ፣ ሐሳብ ሸጦ ኑሮን መግዛት አለመቻል፣ ልብን ሳይሆን የጊዜ ሚዛንን ማዳመጥ፣ ጥሩ አርዓያን መሸሽና ሥር ያለው ፍልስፍና ላይ መለገም፣ ነፃና ደፋር ሙያተኛ በመሆንና መደዳ ግለሰብነት መሀል ያለውን ልዩነት አስምሮ፣ ሌሎችም እንዲቀበሉት ከማድረግ መጉደል . . . ወዘተ የሚመጣ ነው፡፡ መደንገጥ መማረክ ነው፡፡ መደንገጥ አለመደርጀት ነው፡፡ ነፃ መንፈስ ከደፋር ሰው አይነጠልም፡፡ ድንጉጥም ከመመሳሰል እንዲሁ፡፡ በመደመር አምላክ ምስክርነት እናውራ ከተባለ ከጥቂት ነጠላ ንጥር ሰዎች ውጪ አብዛኛዎቻችን ጅምላ የኢትዮጵያ የጥበብ ውልዶች ከችግራችን አንዱ ድንጉጥነት ነው፡፡ የደነገጠ የትንሽዬ ገንዘብም፣ ሞቅ ያለ ሰላምታ ቀብድም የሕይወት ስንቅ ይሆነዋል፡፡ የደነገጠ የያዘው የሙያ መጠሪያ ስለማይዋሀደው የሚሰጠው ሁሉ ይበዛበታል፡፡ ድንጉጥ አርቲስት ስሙ ትንሽ ግድግዳ ላይ የተጻፈች ቀን ማመን ያቅተዋል፡፡ ወይም ራስን የመለጠፍ የፌስቡክ መብቱን ተጠቅሞ የሚመጡ ‹‹ላይክ›› አረማመዱን ይጫኑታል፡፡

ከሐሳብና ከጠራ ፍልስፍና ግንባታ ቀድማ የምትመጣ ‹‹አርቲስት›› የምትባል ሰውነት የሚሸከማት ጠንካራ ልብ ከሌለ በነጠላ ቃለ መጠይቅም፣ በድግስ ወንበርም፣ ሌላው ቀርቶ በታክሲ ክፍያም በቀላሉ ክው የማለት ዕጣ ይኖራታል፡፡ እኔ ትልቅ ነኝ ያላላ ደፋር ማንም በተራ ሊያዘው ይዳዳል፡፡ ድንጉጥ መታዘዙ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አስደናቂው መከፋቱ ነው፡፡ ለድንጉጥነት ኑሮ የሚባል ወረቀት ቀርቶ ዕድሜ የማይበቃው የጦስ ዶሮ በየዘመኑ ሲሰዋለት ኖሯል፡፡ የኑሮን እውነትና ኃይል ያለማወቅ አንድ ሸክሙን ያልጀመረ ጨቅላ አሊያም በድን መሆን ይፈልጋል፡፡ ኑሮ ምክንያት ለመሆን አይቻልም፣ አይባልም፡፡ አሳዛኙ ስንደነግጥ የኖርን አብዛኞች ከድንጋጤያችን ውስጥ በዘመናትም ኑሮን ማሸነፍ አለመቻላችን ነው፡፡ አንዱ ግድርድር ‹‹አባቴ ቅኔ በጣም መማር እፈልጋለሁ፡፡ ግን ደሃ ነኝ ምን እየበላሁ ልማር?››  ያላቸው አንድ ምጡቅ የቅኔ ምሁር ‹‹ታዲያ ምን እየበላህ ደደብክ?” የሚል ያልደነገጠ ጠቢብ መልስ አጉርሰውት ነበር፡፡ ዕውቀትና ክብር አልጠላም ግን ምን ላድርግ መናጢ ነኝ በሚል ለፍርድ በሚቸግር መንገድ የመጣው ምስኪን ምናልባት ጠብቆ የነበረው ችግር የለውም፡፡ ደሃ ከበላ መች አነሰው . . . አሊያም እኔ አበላሃለሁ ጠቢብ ሁን የሚል የኑሮና የሞራል ስፖንሰርሺፕ ይመስለኛል፡፡ ያገኘው ግን የድፍረት ጉርሻ ነው፡፡ ሆድ መሙላት አለመሙላቱን ግን እሱ ያውቃል፡፡ የጠቢቡ ቋጠሮ ግን ለመደደብ ያገኘኸው ምግብ ዕውቀትን ለመድፈር እንዴት ጠፋ? . . . ወይም ባታውቅም፣ ብትፈራም ትንሽ ሆነህ ከትልቅ እኩል ከመሞት አትቀርም ነው፡፡

ጅምላነት ክፉ ነው፡፡ ከክፋቱ አንዱ ድክመትን እኩል ማከፋፈሉ ነው፡፡ ድክመትን የጋራ አድርጎ የአዕምሮ ጥያቄን ማስመለጡ ነው፡፡ የመፍትሔ ዕድልን ከችግር ፈጣሪው ጋር በድብስብስ አስመልጦ ንፁኃን ሊያስይዝም ይችላል፡፡ ብዙው አንድ በሆነበት ማንም ማንንም ምንም የማለት ዕድልም፣ ድፍረትም አይኖረውም፡፡ ጅምላነት ለነጂ ሺን አንድ አድርጎ ስለሚሰጠው ሕይወቱን አቅላይ ነው፡፡ ግለሰብ እንጂ ጅምላ አዕምሮ ስለሌለው ሺሕ ቢሆንም የሚደፈር ነው፡፡ የሙያ ውክልና የምትባል ቅጥያ በድፍረት በግላቸው ‹‹ለምን?፣ እንዴት?፣ . . . ›› የማይሉ ድንጉጦች ከያዘች ውክልናዋ ዕዳ ይሆናል፡፡ እኔ የእኔ የሚሉት ነገር የሌላቸው ሰዎች ተሰብስበው የሚሆኑት ብዙ ምንም የሌላቸው እኛዎች ነው፡፡ ያለሐሳብ የሚጨመቅ መፍትሔ ብዙ ቁጥርም ይሁን ጥሪ ግድ የማይለኝ ለዚያ ነው፡፡ ያለግለሰብ ጥሩ ሐሳብ በሚቀመር የቁጥር ማኅበርና ራሽን ማን መጣ?፣ . . . ማን አልወሰደም?፣ . . . ማን አዘነ?፣ . . . ማን ከፋው?፣. . . በሚል ልብ ማውለቅ አስፈላጊነቱ ምንም አልደመቀልኝም፡፡ የነገሩ ከፍታ ልቡ ውስጥ ሥሩን የሰደደ ካለ አንድ ሺሕ ቀርቶ አንድ ይበቃል፡፡ አንድ ሙያ ቀርቶ አገርም ዕጣዋ የሚመከር በጣት ቁጥር ሰዎች ልክም አይደል፡፡ ከሌለ በአንድ ሚሊዮን የአዳራሽ ሠልፍም አይመጣም፡፡ ነገሮች ያልተፈቱት፣ የማይፈቱት፣ ውክልናዎች መፍትሔ ማስተላለፍ ያቃታቸው፣ ውጪና ውስጥ ባለ ቁጥር ማነስ አድርጎ መተንተን ምንጩን ከመሠረታዊ አምክንዮ በፀዳ ብሽሽቅ የማስላት ውጤት ነው፡፡ ያሳለፍነውንም ጊዜ አውቆም ይሁን በዝንጉነት መዝለልም አለበት፡፡ ያለፈን መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ዛሬን ለተሻለ መነሻ አለመጠቀምም ብኩንነት ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ያለፈውም፣ የአሁኑም፣ መምጫው ባይታወቅም የፊቱም ከስብሰባና ድግስ የፀዳ ኑሮ እንኖራለን የሚለው ስለማይጠበቅ ወደ አዳራሽና ግንባር ‹‹ይለፍ›› የሚል ፈቃድን እንጂ፣ አርቲስት የመሆን መግቢያ መውጫ ቪዛ ሆኖ አያውቅም፡፡ መሰላል የሆናቸው ላይጠፉ ይችሉ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወንበር ማግኘትና ማጣቱ የጥበብ ዕጣ ፈንታችንን ለምን በትጉ ፈታነው? የሚለው ዋዛ ጥያቄ መሆን የለበትም፡፡ ‹‹ . . . አይ እኔ እኮ ድግሱ ምናምን አይደለም. . . የሙያ ጉዳይ ቢጤ ነበረኝ . . . ›› ከተባለ በኩነቱ ላይ የቀረበ ሙያዊ መፍትሔና የወኪል ጥያቄ አልነበረም፡፡ ከዚህ በፊት በነበሩት ላይም ቢሆን ልምዳችን አይመሰክርም፡፡ ‹አይ ነገሩ ነው እንጂ ጩቤ ሰው አይጎዳም› ዓይነት ታዘብኩሽ ከሆነ ደግሞ ጩቤ ሰው ካልጎዳ ትዝብቱ ብቻውን በነገር መድከም ይሆናል፡፡ ታዛቢ ዕድሜና ጉልበት ይኑረው እንጂ ‹‹ተያየን!›› ለማለት በየቀኑ ከእዚህ እጥፍ አለለት፡፡ የማሊያ ለዋዋጩን፣ ቃል ለዋጩን፣ . . . የእውነተኛው ዓለም ተዋኙን ምናምን ለመናገር እኛ የግል ድፍረት ይኑረን እንጂ ምክንያቱም የቁጥር እጥረትም የሚገጥመን አይመስለኝም፡፡ ‹‹እንዴ! ዱርዬ አርቲስት ድግስ መሀል አይቼ . . . ያውም አባባ ጃንሆይ ሳሎን . . .›› ካልን (በእርግጥ ጃንሆይ ሳሎን ብዙ ዱርዬ አይተናል) ከድግሱ በላይ ሰውዬው ሙያው ውስጥ ድንኳን መጣሉ ለሙያ አብዮት የቀረበ ነው፡፡ ከሙያው ባለቤትነት ከተፋታ ከድግስ አይደለም ከኑሮም ሊርቅ ይችላል፡፡ ለዱርዬነቱ የሥርዓት ከለላ አለበት ዓይነት ባይ ከሆነም መፍትሔው የሥርዓት እርማት ነው፡፡ ያኔ ልክ ያልሆነ ከለላም ተከላይም ከለላ የሌለው ስጥ ይሆናሉ፡፡ የሚወድቁበትን ንፋሱ ይጨነቅበት፡፡ እኛ ደግሞ ስለዘላቂ የሙያ መንገዳችን፣ ስለዘላቂው የሙያ ዕጣችን ወግ (ጽሑፉም ዋና ዓላማው ይኼው ነውና!)፡፡

በሀቅ ምስክርነት (በነጠላ መደመር አምላክ ይሁንብኝ) ከጥሪው አጥር ውጪ መሆን የጥሩ አርቲስትነትና ተገፊነት. . .፣ ከአጥሩ ውስጥ መከሰት የችግር አካል መሆኑን አጋጣሚው አላሳየም፡፡ በድምር ውጤት ከአጥሩ ውጪም ውስጥም የተሻለ የጥበበኝነት የጎላ ማንነት ማስመስከሪያ አልታየም፡፡ ወትሮም ጥበብ በሐሳብ ዙሪያ እንጂ በኩነትና በድግስ ዙሪያ አይብላላም፡፡ የጥሪ ድራማው ባለድርሻ አካላት ከግራ ቀኝ ቢያላትሙትም ሁሉም ሊጠራም ሊሆንም ባይችልም እንዲያው ግን ልቅም ተደርጎ ሁሉም ቢከተት የተሻለ ውጤት ከአሁኑ ነበረው፡፡ አስብሎ ስሞታ የሚያስቀርብ . . . በሚኒስቴር ደረጃም ይቅርታ የሚያስጠይቅ ምን ዓይነት የአንጀት መተንተኛ አግኝተን ነው?፡፡ በእርግጥ ተበድለንም በድለንም ይቅርታ አለመድንም፡፡ ይቅርታ መስማቱ ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ በዕለቱ ጠብ የሚልም ሆነ ቀድሞ የከሸፈ ጥያቄና አስተያየት ይዞ የገባ ሰው ይጠፋል የሚል ግምት የለኝም፡፡ የቱም ያልሆነው ግን ሁነቱ ከመነሻው በተጻፈለት ዕጣ ፈንታው ነው፡፡ ታዲያ የመነሻ ሐሳቡን ትቶ ምንድን ነው ውጤቱ ላይ አተካሮ? ለሚለው የሚመልሰው ባለቤቱ ነው፡፡

ጅምላነት ክፋቱ ወቀሳን በግለሰብ ደረጃ አያከፋፍልም፡፡ ማንም ኃላፊ ባልሆነበት ማንም ተጠያቂ አይሆንም፡፡ ማንም መሪ በሌለበት ምንም ተከታይ የለም፡፡ ከዚህ የሚታለበው “እኔ ምን ላድርግ ችግሩ የሁሉም ነው . . . ” የሚል የምክንያት ወተት ነው፡፡ ወተቱ ለአገርም ለሙያም የሚጠጣ አይደልም፡፡ ረግቶም ቅቤ አይወጣውም፡፡ በግሉ የማይቆም ደፋር አብሮ የግሳንግስ ጽዋ ጠጪ መሆን ዕጣ ፈንታው ነው፡፡ ድንጉጥና የሙያ መሠረቱ እንደ ነገሩ የሆነ ማኅበረሰብ አብረውም ሆነ ሥሩ ያሉትን አንጥሮ የሚያወጣበት እሳት የለውም፡፡ አብሮ ከመንደድ ውጪ፡፡ በመደበኛ ቀን የሌለ የመለያ መሠረት ደግሞ በጥሪ ወቅት አይመጣም፡፡ ሠርግ ሙሽሮች ፍቅራቸውን የሚያውጁበት ዕለት እንጂ፣ ፍቅር የሚጀምሩበት ቀን አይሆንም፡፡ ስለዚህ ከጥሪ ካርድ በላይ የቁጭትም፣ የንዴትም፣ የስኬትም፣ የውድቀትም፣ የወቀሳም፣ የሙገሳም፣ የግምገማም፣ የመለየትም፣ የማንጠርም፣ የመደመምም ሆነ የመደመር አንኳር መሆን ያለበት የሚያኖረው ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ በሸሸበት እንኳን የጥሪ ካርድ መያዝ ሙሽሮቹን ከነመፈጠራቸው የማያውቅ ድንኳን ሰባሪ ‹‹አስተባባሪ›› የሚል የቤተ ዘመድ ቦታ ሊወርስ ይችላል፡፡ በግሌ ግድም አይሰጠኝ፣ ጉድም አያስብለኝ፡፡ ቁም ነገሩ ከውስጡ ከታጠበ የድንጉጥ ካርድ ሽሚያ በነጠላው የሚያመለክተው ልፍስፍስነትን ነው፡፡ የድንጉጥ ካርድ አዳይነት በነጠላው የሚያመለክተው ምርኩዝ አዳይነትን ነው፡፡ እዚህ መሀል መባል ካለበት ‹‹ታዲያ ሙያን እዚህ ምን ዶለው?›› የሚለው ሀቅ ነው፡፡ አብዛኛው ድራማ ‹የሙያ ቂም ያባውን ድግስ ያወጣዋል› ዓይነት ነው፡፡ እንደ ጥበብ ሙያ ያለቦታው በጅምላው የተቀረቀረ ሌላ ብሔር ነው፡፡ የብሔር ተሳትፎን መቁጠር ጥበብን ካርታ ላይ ሥሎ የድምር ቁማር መጫወት ነው፡፡ የጥበብ መጉላት፣ የጥበበኝነት ልክና ጥራት እንጂ፣ የብሔር ኮታ ለጥበብ ምጣድ ማሰሻ መሆን የለበትም፡፡ ተፈጥሮውም ለዚያ አልተሠራም፡፡ ቁማር ያማረው ራሱን እንጂ ሕዝብን አስይዞ አይደለም መቋመር ያለበት፡፡ በግል መበላላት ይቻላል፡፡

የጅምላ ድንጉጥ አንዱ ገጹ የሚያውቀውንና ያለውን ተሻምቶ መቀበሉ ነው፡፡ ከጅምላ ስብስብና ግብዣ የሚወጡ አንዳንድ ምስክርነቶችና መደመሞች ምንጫቸው ያለመረጋጋት/ድንጉጥነት ይመስላሉ፡፡ የተባለውን ከተባለው በላይ፣ ያለውን ሰው ካለው ለጥጦ በመተንተን መጠመድ በውስጡ ልክ ያልመሰለን ለማስረፅ መዋተትን ያሳብቃሉ፡፡  መነቃቃትን ከደካማ ድንጋጤ መለየት ያስፈልጋል!፡፡ የሞረሞረው እንጂ ቁንጣን የያዘው በጨዋነትም ይሁን በርብርብ ቡፌ ሥር አይገኝም፡፡ በአጋጣሚ ቢገኝም እንደ አዲስ አይራብም፡፡ የቱንም ነገር ማን አለው ከሚል፣ የተባለው ምንድነው ብሎ ማሰብ የመደመር ምቀኝነት አይመስለኝም፡፡ የተባለው አመለጠኝ ነው ወይስ ነገሩን የተናገረው ሰውዬ አመለጠኝ የሚለው ነው ቅድሚያችን ብሎም መመርመር የግል ድፍረትም ነው፡፡ እንደ ባለሙያ እንጂ እንደ ግለሰብ ያልተመለመለ የግለሰብ ምክር እንጂ የሙያ ምክር የሚያሻው አይሆንም፡፡ በድጋሚ መነቃቃት ከመደንገጥ ይለያል የሚለው መድመቅ ይፈልጋል፡፡ ሠርገኛ የሙሽራ የክብር እንግዳ እንጂ ክብር ገባሪ አይደለም፡፡ ሙሽራ የጀማው መሰብሰብ እምብርት ምክንያት ነውና ቆሞ መቀበል፣ አክብሮም የታሪክ ዕለት ገጽ ላይ መሥፈር፣ መፈለግ፣ ስሙን በሆታ ማጉላት…፣ የጨዋ ፍላጎት ነው፡፡ የእድምተኛ ፈንጠዚያ ፍቅር እንጂ ማሽቃበጥ አይባልም፡፡ ነውርም ነው፡፡ ሆኖም እድምተኛ ሙሽራን በዕለቱ ከፍ አድርጎ የሚያስቀምጠው ፍቅርም፣ ሠርግም፣ ኑሮም ስለማያውቅ አሊያም ምንም ስለሌለው አይደለም፡፡ በድንኳን በመገኘቱ የደነገጠ ካለ ቀድሞውንም ተፈልጎ የተጠራው ለንጉሡ ዋጋ ስላለው እንጂ፣ ምናምንቴ ስለሆነ እንዳልሆነ በቅጡ አላብላላም ማለት ነው፡፡ ውለታ የሚጎላበት ሳይገባው ሾልኮ የገባ ተሳቃቂ ነው፡፡ መሳቀቅ ከመደንገጥ ባለትዳር ነው፡፡

እድምተኛ ለሙሽራ ትከሻና ዳንኪራ እንጂ የኑሮ ቁልፍ አያቀብልም፡፡ ሙሽራ ለሠርጉ ሺሕ እድምተኛ አረማመድና እስክስታ አመታትን አያስጠናም፡፡ መብትም፣ ችሎታም የለውም፡፡ አዳራሹን ብቻ ያቀናጅ ሌላውን ሌላው በግሉ ይወቅ፡፡ አንድ ሺሕ ሠርግ ሲበላ የኖረ ሠርገኛም አጎራረስ ሙሽራው ከመድረክ ያሳየኝ ብሎ ሳይጨርስ ኩም አድራጊ ታዛቢ ቢያዝበት፣ እስክስታ የሚባለውን ነገር እንዳለ በዛሬው ሠርግ አየሁ ብሎ አቅሉ ሲላላ የቅርብም ይሁን የሩቅ ትዝብትና ኩርኩም ቢጎበኘው ድሮም የሐበሻ ነገር የሚል ብሶት አያዋጣውም፡፡ ‹‹ዕድሜዬን የጨረስኩበት አጥንቴን የከሰከስኩበት ሰፊውን ያገለገልኩበት፣ . . . ከሚለው የሙያ ሕይወት ውስጥ በድንገት ኦ! . . . ኦ! አሁን ነገሩ ገባኝ፤›› የሚያስብል ምስክርነት አገኘ ማለት እሱ አጥንቱና ዕድሜው የትና እንዴት እንደባከኑ ቁጭ ብሎ ማሰብ ዘላቂ ሥራው ይሆናል፡፡ ሰው ስለራሱ ሲያወራ ግን ማመን ያስፈልጋል፡፡

ጅምላ ሆሆታ፣ ጉርሻና እስክስታን ብቻ ሳይሆን ሙሽራና እድምተኛን ሊቀላቅል ይችላል፡፡ በሠርጉ የመግቢያ ካርድ የሚጠየቅ ማንነቱ ከድንኳን ሰባሪ ያልተለየ ነው፡፡ በጅምላ ስንደነግጥ ግለሰብነትን ከሙያ ባለቤትነት መለየት ይሳነናል፡፡ ያልተረጋጋ ሰው የሚናገረውን በማንኛውም ግለሰብ አስተሳሰብ ውስጥ ሆኖ በባለሙያነት መጠሪያ ይጠቀመዋል፡፡ በብዛት ከአንድ ‹ባለሙያ› የሚመጣው አስተያየት ከተራው ግለሰብ አለመራቁ የጥበብ ዓላማችንን መናቂያ ወይም ለመደፈር መነቃቂያ እንዲሆን ካደረጉብን ጥርቅም ትዝብቶች አንዱ ነው፡፡ ሁሉም አንድ ከሆነ ደግሞ የሚገጥመን ሙያውን በቅጡ የማያውቁ ሰዎች እንኪያ ሰላምታና ልብ አውልቅ የፌስቡክ ወሬ ማሞቂያነት ነው፡፡ የጠራ ግለሰባዊ አስተሳሰብና ልዩነት የሌለው የመከነ መቀነስና መደመር ይወልዳል የሚለው ሐሳቤ ነው፡፡ የጋራ ጉዞ፣ ስብሰባ፣ የደቦ ድግስ፣ የጋራ መዘመር፣ . . . ወዘተ የራስ ነገር ይዞ ነው እንጂ በጠንካራ ተከልሎ፣ ከደካማ ተደማምሮ አይደለም፡፡ አሜሪካኖቹ ‹‹ያለው ብቸኛ የግለሰብ ታሪክ እንጂ ታሪክ የለም›› ሲሉ የጋራ አገርና ሙያ የለም ለማለት አይመስለኝም፡፡ ታሪክ የእያንዳንዱ ነጠላ ሰው የሕይወት ጥርቅም ነው ለማለት ሽተው ነው፡፡ ለብቻው ጠንካራ ሰው ወይም አርቲስት ያልሆነ ሰው ከማንም ተደምሮ ወይም የማንንም ስብከት አመንዥጎ የታሰበው ማማ ላይ ይወጣል ብሎ ማሰብ ስንፍና ነው፡፡ የሚደመር ብቻ ሳይሆን የሚቀነስም መንፈስና ሰው አለ፡፡ የግለሰብን አቋምም የራስን ድርጊት ለመከላከል በደቦ መሰማራት የጅምላ ክፋት ነው፡፡ ራስንም በተቀመረ አጀንዳ/ጥቅም ወጥሮ በሌላ ጎራ ላይ የሚዘምት ወታደር እንጨት ፈላጊ ድንጉጥ ሐረግ ነው፡፡

ድንጉጥነትን ጊዜና ሰው በመቀየር መፍታት ዳገት ነው፡፡ መታገልም ያለብን አንድን ነጠላ ክስተት ሳይሆን በዘላቂነት የሚያኖረንን ሰብዕና ያልገነባንበትን አስተሳሰብና ባህል ነው፡፡ የፌስቡክ ፊደል መጫን በቻለ ሁሉ የንቀት ቅብብል በጥበብ ዓለም ሰው የጠናበት እሱ ከድንጋጤውና ግድርድርነቱ ሳይወጣ ደፋሮች እየተቀያየሩ ስለሚመሩት ነው፡፡ ቪክቶር ፒንቹክ (Victor Pinchuk) ‹‹ጥበብ፣ ነፃነትና ፈጠራ ከፖለቲካ በፈጠነ ማኅበረሰብን ይቀይራሉ›› ሲል ነፃ የሚለው ተሳስቶ የገባበት ቃል አይመስልም፡፡ የእኛ የመንፈስ መላላት ያመጣብን የጅምላ ፍረጃ ባላፈው ታሪክ ዛሬን መታየት፣ ገና ሳናወራ የመታወቅ ተገማችነት ነው፡፡ ሕይወትን የለዘዘ ከሚያደርጋትና ድህነትን ከሚያጎላው ነገሮች መሀል አለመብላት ብቻ ሳይሆን ኦዲየንስ ማጣት ነው፡፡ ተናግሮም፣ ተናዶም፣ ተንትኖም፣ ቀልዶም፣ ተችቶም፣ አድንቆም ኦዲየንስ ማጣት ያስከፋል፡፡ የቲያትር አዳራሽ ብቻ አይደለም የነጠላ ሰው ጉዞም የራሷ ኦዲየንስ ትሻለች፡፡ ኦዲየንስ የሚመጣው ደግሞ ሲከበሩ ነው፡፡ እንደ ግል ሳየው ለቅጂ መሹለክና የሽያጭ ማነስ ችግር ብሶት ከዓቃቤ ሕግ ግንዛቤ በላይ እንደ ትልቅ ባለሙያ መከበር ዋጋ አለው፡፡ ሰው ለሚያከብረው በተሻለ ራሱንና ሳንቲሙን ይከፍላል፡፡ ወይም በተሻለ ይሰማዋል፡፡ እሱን የት አየን ላለ ጠያቂ የቴዲ አፍሮ አልበም ከታሪክ በላይ ሲሸጥ የት ነበርክ? የሚለው ምሱ ነው፡፡ ወይም ከመከበርና ሙሉ ከመሆን ማዶ በተናገርነው/በጻፍነው ተቀጪ እንጂ ተደናቂ መሆን አንችልም፡፡ የአደባባይ ሰው በሕይወቱ የሚሰጠው መርገምትም ይሁን ፍሥሐ ትልቅ ነው፡፡

ጅምላነት በዚህ ጽሑፍ የተጠቀሰው የጋራ ሸንጎን በመፈንቅለ መንግሥት ለማስወገድ አይደለም፡፡ ግለሰባዊ አስተሳሰብ እንጂ ግላዊነት የተጠናወተው ባለሙያም ሆነ ነጠላ ሰው ለመፍጠርም አላሰበም፡፡ ይልቅስ የግል አቋም መጉደልና ድንጉጥነት የደፋር ሰብዕናን አስተሳሰብ ሲገዳደሩ ያየ ነው፡፡ ዝምታው የማያስፈልገው ወይም መለስለስ ያልተፈለገው ሙሉ ለሙሉ ታጥበው እንዳያልቁ ከመሥጋት ነው፡፡ አርቲስትነት ከግለሰብ ፍልስፍና ወደ ጋራ ባህር የሚቀዘፍበት እንጂ በጅምላ ውቅያኖስ የሚዋኝበት ከሆነ ይመነምናል፡፡ አርቲስት ሰው ሲሆን በጋራ ይኖራል እንጂ ሐሳቡም፣ መንፈሱም፣ ትዝብቱም፣ ትዕቢቱም፣ ድፍረቱም የጅምላ አይደለም፡፡ ጆን ተትል (John R.Tuttle) የተባለው ሰው ‹‹Freedom in Art›› ብሎ በሰየመው ወረቀቱ ‹‹ነፃ ነፍስ ለመመሳሰል ፍፁም አትሞክርም፡፡ መመሳሰል የማይጠይቅ የልማድ መንፈስ ማስቀጠያ ነው፤›› ብሎ ጥሩ ያግዘናል፡፡ የሙያ ዕድር አስፈላጊነቱ የግል ነፍስ ነፃነትን የማስከበሪያ ቦይ መፍጠር እንጂ ነፍስን መተካት አይደለም፡፡ መንግሥት አርቲስት የሚባለው ሰው መጀመርያ እንደ ዜጋ እኩል ቀጥሎ እንደ ጥሩ አሰላሳይና የሐሳብ መሪ ህልው ሆኖ መኖሩ እንጂ ምን ዓይነትና እንዴት ዓይነት ጥበብ ሊኖር ይገባል የሚሉ ዓይነት ጉዳዮች ባለቤት አይደለም፡፡ ጥበብ የገሀዱ ዓለምም የመንግሥትም ሪፖርት አይደለም፡፡ የአንድ ነጠላ አርቲስት ጥርቅም የነፍሱ ትንፋሽ ነው፡፡ ትንፋሹን ከፈለገ ከወንዝ፣ ከመንግሥት፣ ከሚኖርበት ሕዝብ ባህሪ፣ ከጋርዮሽና የግል ልምድ ሊቀምር መብት ተሰጥቶታል፡፡ ከመነሻው ጥበብ የጋራ እውነትን ትሸፍናለች የሚል ግምት ልክ አይሆንም፡፡ የማንም ጥበበኛ ውጤት ከሚኖረው መንግሥት ባህሪ ፍላጎት ከተፃረረም ከተመሳሰለም ለመሆን ብቻ ተብሎ እስካልተከወነ ድረስ ልክም ስህተትም የሚል ጎራ የለም፡፡ ዋናው ከጥሩ የግል ፍልስፍና ወይም ጨዋ ሰብዕና ከተወለደ፡፡ ደንግጦ ሳይሆን ይመንበት ብቻ፡፡ ነፃነት ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ተቃርኖን መግለጽን ይጨምራል፡፡ ማሽቃበጥንም ጭምር፡፡ ክልክሉ እኛ በሚል ጋሻ ብዙኃኑን ጦርነት መማገድ ወይም ግለኛ ድልን ማደን ነው፡፡ ስህተቱ ለየቱም ቁም ነገር የግል ዓይን፣ ደፋር ልብ መጥፋቱ ነው፡፡ ጉለቱ ነፃ መንፈስ ሲጎል ነው፡፡ በዚህ በትልቁ የሚሞተው ትልቁ ምሥል ነው፡፡

የአደባባይ ሥራ ያለን ሰዎች ሰው የወደደን በግል ችሎታና ሥራችን ነው፡፡ የመወደዱ ዋና ምንጭም ዝነኛ ስለሆንን አይደለም፡፡ አንድ ሥራ ስለሠራን ነው፡፡ መንከባከብም ያለብን ዝናችንን ሳይሆን እሱን ክብር የሰጠንን ሙያ ነው፡፡ በግል፡፡ ከእሱ ውጪ እከሌ የሚባል ተራ ሰው እንጂ ትልቅ ተከባሪ አርቲስት ብሎ ነገር የለም፡፡ በክብርም የትም አንጋበዝም፡፡ ስለዚህ መወደጃው ይኑረን ሌላው ይወለዳል፡፡ ለማጠቃለል የእኔ የሚለው ረብ ነገር ያለው ጥበበኛ፣ የቱንም ለማረጋገጥ መላላጥም ሆነ ምስክር መቁጠር አያሻውም፡፡ ካለው በጥበቡ በኩል ይወጣል፡፡ ደፋር እኔነት ያለው የጅምላ ቅርቃር አያስፈልገውም፡፡ ድንጉጥ ባህሪ ትንሽ ሆኖ ትልቅ የመባል ያልተገራ የስም ረሃብ ነው፡፡ የረሃቡ ማስታገሻ እንደታሰበው አንጀት የሚያርስ ምግብ ሳይሆን አንጀት የሚያርስ ንቀት ሊሆን ይችላል፡፡ ጎበዝ ችግር የለም የትም እንሂድ ግን አንደንግጥ፡፡ አርቲስት ነን በጅምላ አንደመር፡፡ ካከበርነውና ከተዋሀደን አስደንጋጩ እንጂ ድንጉጥ እኛ አንሆንም፡፡ መልካም የነጠላ መደመር ጊዜ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles