Thursday, February 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያ በዕውቀቱ ዘርፍ የፀረ ቅኝ አገዛዝ አማራጭን በፅኑ መመልከት አለባት

በሱራፌል ወንድሙ

ይህ ሰዓትናፍራ ማኅበራዊ ግንኙነታችን፣ ሐሳብና እንቅስቃሴአችን፣ ዕድል አጥቶ ለኖረው ተስፋችን፣ ብዙ ዕድል የምንሰጥበት እንደሆነ ይገባኛል። ለዚህ ያበቁንን ሁሉ ሳከብራቸው እኖራለሁ። ሲጨቁኑን የኖሩት ዳግም ገንነው እንዳይጫኑን ተስፋችንን መጠበቅና መንከባከብ እንዳለብንም ይገባኛል። በዚህ መሀል ነው ስለሐሳብ ማንሳት የፈለኩት። ታዲያሳቤ አንገብጋቢ የሚባሉ ጉዳዮችን ካለማገናዘብ ወይም እነዚህ ሁሉ ዛሬ ወይም ነገ መደረግ አለባቸው ከሚል የመነጨ አይደለም።

ተስፋ የምናደርገው ምን ምን እንደሆነ መነጋገር፣ ነፃነታችን ምን ምን ይዞልን ሊመጣ እንደምንፈልግ ከወዲሁ መወያየት፣ ተስፋችንን መንከባከብ ነው ብዬ አምናለሁ። ‹‹ዝም በሉ!›› የሚሉ እነሱ ጨቋኞች ናቸው። ‹‹ሰዓቱ የድርጊት ነው!›› ለሚሉኝ፣ሳብ አልባ ድርጊት የለም ብዬ በአክብሮት እከራከራቸዋለሁ። ድርጊት ሁል ጊዜ በሆነሳብ መቀንበቡ አይቀርም። ስለዚህ ተስፋችንን የሚያለመልሙ ድርጊቶች ይወለዱ ዘንድሳብ መለዋወጡ መልካም ብቻ ሳይሆን የመዳኛም መንገድ ነው።

እናም የሚከተለውንውይይት ማንቂያ ሐሳብ የምሰነዝረው ከአንጀት በሆነ ትህትና ስለእውነት በሀቅ ለመናገር ነው። ይህች ሐሳቤ ስለአሁኗ ቅዕበት ብቻ የምሰነዝራት አይደለችም ማለት ነው። እኛን የተጫኑን ጉዶችልፍ ናቸውና እነሱን በእርጋታ እያቀለልን፣ እኔ ብቻ ከሚል ባለአንድ ዛፍ ተላቀን፣ ለልጅና ለልጅ ልጆቻችን ባለ ብዙር፣ ባለ ብዙ ፍሬ (Rhizomatic Nurturing) ዘሮችን እንድንዘራም ነው ጥሪዬ። የዓለምን ተጨባጭነት ውስብስብ በሆነውና ግጭት በተሞላበት ማኅበራዊ ሕይወታችን፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ በምናደርገው ትግል የምለካ እንጂ፣ የአንድ ተምኔት (Utopia) ሰባኪ ባለመሆኔ የዛሬ ትግልን አሳምሬ ከቁብ የምቆጥርም ነኝ።

ትናንትን እንደ ብረትውልት አንፀው ለመገንባት የሚታትሩት ሒስ አልባ (Uncritical)በሐሳብ ድርቅ የተመቱ (Intellectually Deficient), እንዲሁም ከዘመኑ የዕውቀት ዓለም በብርሃን ዓመት (Light Year) ልኬት ወደኋላ የቀሩ ነውጠኛ ሁለት ፅንፎች ብቻ የአደባባይ ንግግሮቻችንን አፍነዋቸው የሚቀጥሉት እስከመቼ ነው?

ሕወሓት (ኢሕአዴግ) ያጠፋብን ያለፉትን ሃያ ሰባት ዓመታት ብቻ አይደለም። የፈራቸውንይሎች ለዝንተ ዓለም ትምክህተኛ/ነፍጠኛና ጠባብ ብሔርተኛ ብሎ ለያይቶ፣ እርሱ ዳኛም፣ ከሳሽም፣ ፈራጅም ሆኖ ለመኖር በረዶ ቤት ያስገባው (Frozen/Static) የማንነት ፖለቲካ ዘርፈ ብዙ ችግር ውስጥ ነው የጨመረን።

ይህ አስተሳስብና ድርጊት ማንነቶች ተለዋዋጭና በውስጣቸውም ብዝኃነቶች እንዳላቸው የማይቀበል በመሆኑ እንኳንስ የብሔር ጥያቄን ሊመልስ፣ አያሌ ድርብ ድርብርብ ጥያቄዎች እንዲነሱ ሊፈቅድ ይቅርና ጭራሹኑ ሌላ በማንነት ላይ የተመሠረተ የልሒቃን የበላይነት ጭኖብን ኖረ። የልሒቃኑ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ በጅምላ ላይ የተመሠረተ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› እ ‹‹የብሔር ብሔረሰብ›› ፖለቲካ ሆነ። ወደ ዜግነትም ሆነ ወደ አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ማኅበራዊ ምኅዳሮች የሚወስደን ብቸኛ መንገድ ተደርጎ ሌሎች ሐሳቦችንና አደረጃጀቶችን የሚያገል ሆነ። ያን ዓይነቱርዓት እውነተኛ መገፋት የቀሰቀሰውን ንቁ (Dynamic/which is not based on Primordial Identity Politics) የማንነት ፖለቲካ ኃይል ማለትም የሁሉንም ታሪካዊ በደልና ሊመጣ የሚገባውን እኩልነት የተረዳውን ኢትዮጵያዊነትም ሆነ የብሔር ፖለቲከኞችን የሚገፋ፣ የሚያፍን ሆነ። የወዳጅና ጠላት፣ የመዳንና የመጥፋት (Manichean) ፖለቲካ ላይ አተኮረ። ስለሆነም ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ቋንቋችን በአንድ ነገር ላይ ለዚያውም ሆነ ተብሎ በተጣመመ ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩር ተገደደ። ጋዜጦች፣ ቴአትር ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ሳይቀሩ የብሔር ጥያቄን ጨምሮ ሌሎች ነፃነትን የመተለሚያ በሒስ የዳበረ ቋንቋናፍራ ተከልክለው ኖሩ።

በአገራችን ከሒስ አልባ የማንነት ፖለቲካዎች አንዱ ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ መነሻዋ ደቡብረቢያ ነው፡፡ ምንጫችን ሳባዊነት ማንነታችንም ሥልጡን፣ ለማሠልጠን የተፈጠርን ነን የሚለውን ትርክት የተከለው ነው። ዛሬም በዚያ ዙሪያ የሚደንሱ ተከታዮቹን ብቻ ሳይሆን፣ የትርክቱ አውራ ፈጣሪዎችና አራቢዎችን ጭምር አሠልፎ የአፍሪካ ቀንድ ጥንታዊ ግዛቴ፣ ቤቴ፣ ከሰሜን ኢትዮጵያ በታች ያሉትም መጤዎች ናቸው የሚለውን የዘመናት አዝማች እየዘፈነ አለ።

ሌላው ደግሞ የቀደመውን ሊቃወም ተነስቶ፣ ነገር ግን የጨቋኞችን የመግዣ ትርክት ገልብጦ ለብሶ ሠፋሪና ባለአገር፣ ባለቤትና እንግዳ ወይም ቤት አልባ እያለ በታሪክ አግባብ የተነሳውን የብሔር ጥያቄ ወደ ጎሰኝነት ብሎም ወደ ለየለት ዘረኝነት ወስዶታል።

ማህሙድ ማምዳኒ (Mahmood Mamdani) ‹‹ሰለባዎች ገዳዮች ሲሆኑ›› (When Victims Become Killers) በሚለው መጽሐፉ ላይ እንዳሠፈረው፣ የሩዋንዳን ጭፍጨፋ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያደረገው ጥቁር ጥቁርን መጤና ባለቤት/ባለአገር በሚል በዘር ምደባ ላይ የተቀናጀ ጅምላ ግድያ ስለነበረ ነው። ትናንትን በአገር ላይ እንደተነጠፈ ዝርግ አቡጀዲ ወስደው በማንበብ፣ የጊዜንና የሥፍራን ተለዋዋጭነትና ተቆራራጭነት በቀላል ንባብ እንደውልት ወቅረው የሚያገዝፉ ሁሉ ሳያውቁትም ሆነ አውቀው በእነፍሬድሪክ ሄግል (Friedrich Hegel) ተጀምሮ በአፍሪካ ላይ የተዘራባትን የዘረኝነት ትርክት ነፍስ ዘርቶ፣ ከአካዴሚያ ሾልኮ በየማኅበራዊ ድረ ገጹ ለብሶ እንዲዘዋወር እያደረጉት ነው። ከሴሜቲክ እስከ ግልባጩ ኩሺቲክ ቴሲስ ድረስ፣ ቅድምም አሁንም ሰዎች በአገራችን መጤዎች እየተባሉ ተሰደዋል፣ ተንቀዋል፣ ተዋርደዋል፣ ተጨፍጭፈዋል። ይኼንን በተለያየ ጊዜ ኃይል ያገኙ ፈጽመውታል። አንታረም ብለን፣ በሁኔታዎች ላይ አንነቃ ብለን፣ በትህትና መነጋገሩ ገዶን፣ በዚህም ዘመን ስንፈጽመው ሁኔታው እጅግ ይዘገንናል።

ይህንን የሚያደርጉት ፊደል የቆጠሩና በየጎራቸው የዕውቀት ጫፎች ተደርገው የሚወሰዱ ሰዎችለሆኑ ሐሳቦቻቸው እንደ ልዩ ጠበብት ሐሳብ  ይቆጠራሉ። እናም በቀላሉ ሊፀኑድል ያገኛሉ። በምሁራዊነትም ስም የሚካሄዱ ስለሆኑ ተራ የመረጃ ስህተት ያለበትንም ሆነ በዘመኑ ድንበር ዘለል በሆኑ ዕውቀቶች የተደረሰባቸውንም በሒስ የተሞሉ ዓለም አቀፋዊ ውይይቶች የሌሉ ያህል ይደብቃሉ። የመረሩ የግል ጥላቻዎች ጭምር የሚነዷቸው ግልብ ሐሳቦች እንደ ጥልቅ ጥናታዊ ውጤት ተደርገው ይወሰዳሉ። ታዲያ እኔን የሚያሳስበኝ እንደ ነጠረ ዕውቀት የሚሽከረከሩትሳቦች ለነውጠኝነት የሚያንደረድሩ መሆናቸው ነው። እነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች አንዳንዴ እንዲያውም ይህንን መሰል ሐሳባቸውን በግልፅ ነውጠኝነትን ሲጋብዙበት ይታያሉ።

እርግጥ ነው በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያዊነት የሚሉትን ሁሉ በአፄአዊነት መክሰስም ሆነ የብሔር ጥያቄ ያላቸውን ሁሉ እንደ ጎሰኛ (Adherents of Primordial Politics of Ethnicity) መቁጠር የሁኔታዎችን ተለዋዋጭነትና ዕድገት፣ እንዲሁም ውስብስብነት እጅግ አቅልሎ ማየት (Reductionism) ነው።

ይኼ ማለት ግን ሁኔታዎችን አቅልለው የሚረዱ ሁሉ አስተሳሰባቸው ዝቅ ያሉ ናቸው ማለት አይደለም። በሌሎችይወት ኪሳራ ትርፍ ማግኘት የሚፈልጉ ሆነው አስተሳሰባቸውን ሆነ ብለው የዘጉም ሊሆኑ ይችላሉ።

በአሁኑ ሰዓት አንዱ ወሳኝ ነገር በየቦታው ተደብቀው ያሉና ሁከትና መርዛማነት ያጠነውን የአደባባይ ንግግር ጠልተው፣ ንቀውና ሸሽተው፣ በየጥጉ ያሉ አሳቢዎች ወደ አደባባይ መምጣት እንዳለባቸው የማሳሰብ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያን ውስብስብ ሁኔታዎች የተገነዘቡ፣ የትናንትን ክፉ ባለመድገምና ተከትለውን የመጡትን የሐሳብም ሆነ ተቋማዊ ጭቆናዎች እንዲጠፉ በመትጋት ጭምር ለውጥ ለማምጣት የሚፈልጉ ብዙዎች አሉ። ምንም እንኳን ልሒቃን በብዙኃን ላይም ሆነለብዙኃን ለመናገር ማንም ባይሾማቸውም፣ የሕዝብ ድምፆችና አብዮታዊ ድርጊቶች በጥቅመኛና ጥመኛ ልሒቃን ተጠልፈው እንዳይጠመዘዙ በሐሳቡ ይፋለሙ። ተመሳሳይ ጥረት ስናደርግም የነበርን በሠሩዋቸው ላይ እየጨመርን የራሳችንን አዲስ ሐሳብ እያከልን ለመሄድ ተሳትፏችንን ማብዛት አለብን ብዬ አምናለሁ።

ሆኖም የፅንፈኞቹ ብሔረተኝነቶችና ጎሰኝነቶች እያስከፈሉን ያለው ብዙ ነው። እነሱን እየሞገትን አዳዲስ የሐሳብ ትልሞችን መቀባበሉም ወሳኝ ነው። የአገራችን ታሪክ ውስብስብ፣ ቁርጥርጥ ነውና በጅምላ ፖለቲካ አንዱን በሌላዋ ላይ አስነስቶ ማንም ከዚህ አዙሪት የሚያመልጥ ቢመስለው እርሱ የዋህ አሊያም የለየለት ጨካኝ ነው። ጭካኔ ሩቅ አይደለም አገሩ። ይኼው እያየነው ነው። በዕልፎች ላይ በተወረወረ ፈንጂ። በብሔራቸው እየተነጠሉ በሚጠቁ እናቶችና እህቶች እንደዋዛ ከአፋችን አምልጠውን በማይላቀቁን ይልቁንም እንደ ደግ ነገር በምንቀባበላቸው ቃላትበብላው እንብላው› ተረት፣ በእነዚህ ሁሉ ውስጥ በመካከላችን እየተዘዋወረ ነው፣ ነውጠኝነት። ይህን በአደባባይ እንደማንቀበለው መናገር አለብን።

ቱትሲዎችን መለያና መነጠያ የተደረገው በረሮ (Inyenzi/cockroach) የሚለው ክፉ ስያሜ እንዲያውም መጀመርያ ቱትሲዎች ከስደት ወደ አገራቸው ለመመለስ ይረዳቸው ዘንድ ላቋቋሙት ተዋጊ ቡድን የሰጡት ስም ነበር። በኋላ ስያሜው ስድብ፣ ስድቡም የሰውን ልጅ ወደ ተራ እንስሳ/ነፍሳትነት በማውረድ ቱትሲዎችን በሁቱዎች ለደረሰባቸው የዘር ማጥፋት አቀባበላቸው። በረሮን መግደል አካባቢን ከማፅዳት የሚቆጠር ተግባር አስመስለው። ስድቡ። በዚያ ላይ ቱትሲዎች በሁቱዎች ዓይን መጤዎች ተደርገዋል። የቅኝ አገዛዝና የዘር ትርክት ሁለቱን የአፍሪካ ማኅበረሰቦች ሠፋሪና ባለ አገር ብሎ ጥቁርና ነጭ አስመሰሎ ለፍጅት ሰጣቸው።

ይህን መሰሉ እሳት እኛንም ውስጥ ውስጡን ሲያቃጥለን አለ። አካዴሚያውም ሥሩ አውሮፓ ተኮር (Eurocentric) በሆነ ዕውቀት ሳያውቀው እግር ከወርች ተይዞ በልዩ ነን ትርክቱ (Ethiopian Exceptionalism Narrative) በመግፋት የድኅረ ቅኝ አገዛዝ ውይይቶችን (Critical Postcolonial Studies) ችላ እንዳላቸው ቀጥሏል። ችግሮቹ መሬት ላይ እንዳሉ ቢነቃም አብዛኛው የታሪክ ጸሐ ታሪክን እንደ ቅኝ ግዛት ሐሳብ ተሸካሚ ማየት ተስኖት አለ።

ኢትዮጵያ በዕውቀቱ ዘርፍ የፀረ ቅኝ አገዛዝ አማራጭን (Decolonial Option or Epistemic De-linking – [See Walter Mignolo]) በፅኑ መመልከት አለባት የሚሉትን ጥቂት ድምፆች መቀላቀል እፈልጋለሁ። እዚህ አንድ ነገር ማከልም አለብኝ። የ‹‹ኢትዮጵያ ልዩ ነች›› ትርክት በታሪክ የተለዩ ክስተቶችን ለማገናዘብ የሚረዳና ዓለም አቀፍ ጭቆናዎችን መገዳደሪያ ሆኖ የሚመጣ መሆኑንም ጭምር ብረዳም የእኔ ሙግት ይህ ዓይነቱ አመለካከት ምን ምን ነገሮችን እንዳናይ ከልሎናል? ምን ምን ተጨማሪ ጥያቄዎችንስ እንዳንጠይቅ አድርጎናል? የሚል እንጂ ያለፍንባቸውን የተወሰኑ (Particular) ታሪካዊ ዕውነታዎች ከመካድ የሚመነጭ አይደለም።

ኢትዮጵያ በአካል ቅኝ ባትገዛም በዕውቀት ገበያ የሸመተቻቸው ቅኝ ግዛታዊ ዕውቀቶች፣ የዘረኛ አውሮፓውያን ፈላስፎችና ታሪክሐፊዎች ኢትዮጵያን እንደ ነጭ አገር ድቃይ፣ ከሰሃራ በታች ካሉት አፍሪካውያን የተሻለች ነገር ግን ከነጭ ያነሰች አገር አድርገው ሥለዋታል። በዚህ መልኩ የሠሩት ክፉ ከአገር ውስጥ ከንጉሥ ዳዊትና ንጉሥ ሰለሞን ቤትና ደም ተቀድተናል ከሚለው የገዥዎች ትርክት ጋር ተዳምሮ ዛሬም ድረስ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ግዘፍ ሲነሳ ይታያል።

የቅርቦቹ ጥቃቶች የቱትሲንና የሁቱን የስም ልጠፋ ታሪክ መምሰላቸው ነገሩን በጥንቃቄ ይዘን ሰንኮፉን ፈጥነን በሐሳብ መንቀል እንዳለብን ያሳያል። እዚህ አንድ ነገር በአፅንኦት መናገር የምፈልገው ምንም እንኳን ሁኔታዎች ውስብስብ ቢሆኑም የሕወሓትና የተባባሪዎቻቸውን ወሳኝ መሪዎች ‹‹ተዉ እንዲህ ያለ ነገር አያኗኑርም፣ ታጋዮቻችንም ስለዚህ አልነበርም መስዋዕትነት የከፈሉት፣ የገዛዝብን ተከልሎ መተኮስን የመሰለ ጭካኔ የለም፣ የሁላችን ሰላምና እኩልነት በጋራ በምንገነባቸው የፍትሕ ሐሳቦችና ተቋማት ብቻ ይሁን›› የሚሉ ምሁራን እንዲወጡ የምሻውን ያህል፣ በገዥዎች ጥፋት ድሆች በጅምላ ሲጠቁ ማየት አግባብነት የሌለው ጭካኔ ነው ስል ማውገዝ እፈልጋለሁ።

እንደ ድሃ ሕይወታችን በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ተሰቅዛ እንዲህ ባሉ መጠፋፋቶች ስንጠመድ በጥጋብ ‹‹ጦር አውርድ!›› እያልን ያለንዝቦች ያስመስለናል። ዓለም አቀፉ የከበርቴ ሥርዓት በዓለም ዙሪያ ያሉ ድሆችን አበሳ እያስቆጠረ፣ እኛም ከዚህ የዓለም የሥራ ክፍፍልርዓት (International Division of Labor) ማምለጥ አለመቻላችን ሀቅ ሆኖ፣ እንዲህ ባሉ የመጠፋፊያ ድፍን ቃላት ስንፈናከትና ስንደማማ የመከራችን ውስብስብነት ዝም ድረስ ይሆንብኛል።

ድርጊቶቻችን በጊዜ የሐሳብ መዋቅር አለመዘርጋታችንን ያሳብቁብናል። የቀሩትን ለጊዜው ብንተዋቸው ከደርግ ዘመን ጀምሮ ማለም፣ ራዕይ ማበጀት፣ በምናብ መጓዝ ተከልክለን፣ ብርቅ ሆኖብን የኖርን ሕዝቦች እኮ ነን። በሐሳብ ጠኔ ተመተን ኖርን። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን እርስ በርሳቸውሐሳብ ሳይሆን በድንጋይ፣ በረጋ ውይይት ሳይሆን በአጥርና በቧንቧ ንቃይ እንዲፋለሙ ተደረጉ፣ ተፈረደባቸው። የሚዳኛቸው በሥሩ እያተጋ እንዲያለመልማቸው ሁኔታዎች የተመቻቹለትና እንዲያ እንዲሆን የተቃኘ፣ የተቃኘች መምህር/መምህርት ሳትሆን በዩኒቨርሲቲ ካድሬዎች የሚጋበዝ የፌዴራል ፖሊስ ቆመጥ ሆኖ ነበር።

የሕዝቡ ተቃውሞ የተወለደው በእዚህ መሀል ነውና ሀና አረንድት (Hannah Arendt) እንደምትለው፣ የተቃውሞው ቋንቋ ሕዝቦች ሊጥሉት በሚታገሉት ሥርዓት ጭምር የተወሰነ ሆኖ ቆይቷል። ሳናውቀው በምንፋለመው ኃይል ቋንቋ ተጠልፈናል። ሁላችንም አዋቂነታችንን ለማስመስከር ስንታትር የትሁት ጠቢብነት መላ እንደራቀን አለ። ጊዜው የሰሎሞን ዴረሳን ምክር ሰምተን ከማወቅ ወይም ከአዋቂነት ባሻገር በምናብ ነፃነቶቻችንን የምንቀርፅበት ነው። ነፃነት ማለት ራስን በማያቋርጥ ምጥ ደጋግሞ መፍጠር ነው፡፡ ቁም ነገሩ ከቦታው መገኘት ብቻ ሳይሆን ህላዌ ውስጥ ፈጠራን መውለድ ነው፤ እንዲል ፍራንዝ ፋኖን (Franz Fanon)

መገንዘብ ያለብን አንዱ ቁም ነገር ኢትዮጵያዊነትም ሆነ ብሔር ተኮር ማንነት በጎም ክፉም፣ ፍሥሐም መከራም፣ ድልም ሽንፈትም የተስተዋለበት፤ ሲላጋ ሲጋጭ፣ ሲወድቅ ሲነሳ የኖረ፣ ጥምዝምዝና እገጭ እጓ የበዛበት ነው ብለን ብናስብ ለመገነዛዘብና ወደፊት ለመራመድ መቻላችንን ነው። የጅምላ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ አራማጆች የብሔርን ጥያቄ የመደብ ጥያቄ መንትያ፣ ነገር ግን እስከ 1983 .. ድረስ ዕድል ያላገኘ በእነሱ አባባል ‹‹ነጥሮ የወጣ!›› ጥያቄ አድርገው ይሥሉታል። እንደዚያ ቢሉንም የብሔር ጉዳዮችን አጋኖ ማውጣቱ ራሳቸው የተወለዱበትን 1966 አብዮት ጭምር አዛብቶ እንደማቅረብ ነው።

በመጀመርያ ታሪክን እንደ ልብ ወለድ የመቅረጫቸው መንገድ የሚክደው የሴቶችን ጥያቄ ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያ ሴቶች ትግል ምንም እንኳን በወንዶቹ መጠለፉ ባይቀርለትም ችግሮችን ነጥሎ በማጉላት ሳይሆን በንብርብርነት የመረዳትን ሐሳብ ያስተጋባበት ማዕቀፍ ለዓለም የሚተርፍ ሐሳብ ነበር፤ ድርብ ድርብርብ ጭቆና የሚል የሐሳብ ማዕቀፍ። ሌላው የተካደው የሃይማኖት ጥያቄ የቀረበበትና በ1966 አብዮት ሰዓት የተለያዩ እምነት ተከታዮች አጋር ሆነው የወጡበትና አንድ መቶ ሺሕ ሰው የተሳተፈበት የሙስሊሞች ጥያቄ ነው።

የብሔርና ዓለም አቀፍ የወዛደርን ትግል በተመለከተም ዛሬ ከዓውዱ ውጪ ለዛሬ ዓላማ በሚበጃቸው መልኩ የሚነሳውን ዋለልኝ መኮንን መጥቀስ ይቻላል። ዋለልኝ በብሔር ጥያቄ ላይ የጻፈው (ራሱም እንደሚያምነው) ቁንፅል ጽሑፍ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ቢሄድም ነፃ የሆኑት ብሔሮች በዓለም አቀፋዊ ወዛደራዊነት ዞረው እንዲገናኙ ነበር ሶሻሊስታዊ መሻቱ። በእዚህም ዋለልኝ ትልቅ አብዮታዊ እሴትን ለመደብ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ለሀብት ወይም ካፒታል ብሎም ለዓለም አቀፋዊ ትግል ሰጥቶ እንደነበር ማየት ይቻላል።

ሌላው ቀርቶ ሕወሓት 1968 መግለጫው ላይ በዋና ይዘቱ (Essence) ሲለካ የብሔር ጥያቄ የመደብ ጥያቄ ነው ብሎ ነበር። የኃይሌ ፊዳማ ሐሳብ ይደንቃል። የብሔር ጭቆናን አብጠርጥሮ በመረዳት መፍትሔውን ሲያፈላልግ ኢትዮጵያውያን ዋናው ደመኛችን ድህነት ነው ነበር የሚለን። የኃይሌ እንጉርጉሮ ከአገሩ እስከ ዓለም አቀፋዊ ትግሉ ድረስ ያለውን ጥበብ ፖለቲካውን (Poetics Politics) ይነግረናል። ኃይሌ ፊዳ የወሰኑ ዲዶን ‹‹ ለሰለሴ ባዬቲ›› ይዞ፣ የካሳ ተሰማን ‹‹ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ›› አስከትሎ፣ ‹‹ለኧንተርናስዮናል›› በፈረንሣይኛም በአማርኛም የሚያዜም መሠረቱን ይዞ ለዓለም አቀፍ ትግል የተዘረጋ የጥበብ የፖለቲካ ሰው ነበር።

በዚያ ላይ መርሳት የሌለብን የብሔር ጥያቄ ራሱ አንድ አተያይ እንዳልነበረው ጭምር ነው። ዋለልኝን ብቻ ነጥለው ለእዚያውም እያዛቡ ሊተረጉሙት የሚጠሩት ሁሉ በብዕር ስማቸው ይታወቁ የነበሩትን እነ ጥላሁን ታከለን ጨምሮ እነ አንድሪያስ እሸቴን፣ጎስ ገብረየሱስን፣ መለሰ አያሌውንና ዓለም ሀብቱን የመሰሉ ተከራካሪዎችን ፈጽመው አያካትቱም። ጉዳያችንንም በደም ስንዋረሰው የመጣብን የውስጥ የውስጣችን ችግር ብቻ እያደረጉ ዓለም አቀፍና ክልላዊ ጂኦ ፖለቲካን ችላ ያሉ ብዙ ናቸው። በእዚህ በኩል አሁንም እንደዚህ የሚሥሉንና ራሳቸውንም ጥቅማቸውንም የዓለም አቀፉ የነጭ የበላይነትን ያንሰራፋው ከበርቴያዊ ሥርዓት ውስጥ አካተው ሲተቹ የማላያቸው ፈረንጅ ጸሐፍት (Ethiopianists) ስለ ኢምፔራሊስታዊ የዕውቀት ምርትና ጦሱ በተመስጦ እንዳስብ ይገፋኛል። የኤርትራ ተነጣዮች ከነበራቸው ወሳኝ ከለላ የመስጠት ስትራቴጂካዊ ሥፍራ የተነሳ በአገራችን የብሔር ጥያቄ ምንጮች ባይሆኑም ጥያቄውን የምንረዳበትንና የምንመልስበትን ሁኔታ ምን ያህል ተፅዕኖ እንዳሳረፉበት በቅርበት ለመመርመር የሚሹም ጥቂቶች ናቸው።

ለዚያውም የኢትዮጵያ የዘመናት ጥያቄዎችና የሕዝቦች ትግል ታሪኮች የዕለት ተዕለት ትግልንና የተራ ተርታውን ሕዝብ ታሪክ በየመልኩ ውስብስብ ቅራኔዎችን ባገናዘበ ሁኔታ ቢጠኑ ዛሬ የብሔር ጥያቄን ዋነኛ ብቻ ሳይሆን ብቸኛ ወደ ዜግነትና ፖለቲካ ማምሪያ መንገድ (avenue) ባልሆነ ነበር።

ይህ ገዥዎች ዕውነታዎቻችንን በማጣመም በስስ ፖለቲካ ሕዝብን ለመጋለብና ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ያላቸውንም ፍላጎት ያሳያል። በጽሑፌ ውስጥ አሠራጭቼ ለማሳየት እንደሞከርኩት የማንነት ፖለቲካን ከእነጭራሹ በመካድ ‹‹ሰው›› የሚለውን ሐሳብና ገላ ከታሪክ በደልና ጥቅም ውጪ አድርጌ ለማየት አይዳዳኝም። ሰዎች በማንነታቸው በሚደርስባቸው በደል ነው ማን መሆናችውን ደጋግመው ማስታወስና ማክበር የሚፈልጉት።

ኤድዋርድ ሳይድ እንደሚያስታውሰን የማንነት ፖለቲካ የሚፍቁት አይደለም። የእኔ ጥያቄ ማንነትን ወጥ አድርጎ ወደ ውጪም ወደ ውስጥም በጅምላ መመልከት ነውጠኝነትን ይጋብዛል በሚለው ሐሳብ ዙሪያ ነው። በእዚያ ላይ በሌሎች ላይ የምናየውን አፀያፊ ጭቆና ራስ መሀል ሲከሰት ታሪክ መደለዝና መካድ፣ ማንነታቸው በታሪክ ገዝፎ ጥቅማቸውን በቀላሉ እያጣጣሙ ያሉ ሰዎች የባህልም ሆነ ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥውር አገዛዛቸው እንዲቀጥል ማድረግ ከሚፈልጉቱ ተለይቶ አይታይም። ብዝኃነትን በአውራዎች መካከል የሚፈልጉና የሚገነቡትም ሳያውቁት ጭቆናን በውስጣቸው እንዳደረጁ ያስታውቅባቸዋል። ስለዚህ ጉዳዩ የብሔር ጥያቄን የመካድ ሳይሆን ሌሎች አያሌ የጭቆና ዓይነቶቸን የመግለጥና ችግራቸው በብሔር ማዕቀፍ የማይተነተኑና የማይመለሱ ጉዳዮች መኖራቸውን የመመልከት ጉዳይ ነው። አልፎም በማኅበራዊ ሕይወታችን ተነጣጥለው የማናያቸውን ጥያቄዎች ነጥሎ ማውጣቱ እውነትን ይከልላል የሚልም ነው።

 • እንዲያ ከሆነስ ዛሬ ላይ የነፃነት ጥያቄ የምናነሳባቸው ጉዳዮች የብረት ሐውልት ተደርገው ከተገነቡብን፣ ተለዋዋጭነትን ከማይቀበሉት፣ ብዙ መነሻ ምንጮችንና እልፍ መውጫ መላዎችን ሳይሆን ከዚያም ይሁን ከዚህ አንድ ሥር መምዘዝንና አንድ ዓለም መናፈቅን የዘወትር ፀሎት ካደረጉት ሒስ አልባ የማንነት ጥያቄዎች ውጭ በብዙ አቅጣጫ ተጎናጉነው ሊቀርቡ አይችሉም? አይገባቸውም?
 • ለምሳሌ ድህነት ከፆታዊ ጥቃትና ጉልበት ብዝበዛ፣ እንዲሁም ከአካል ጉዳተኝነት፣ ከብሔር ማንነትና ሃይማኖታዊ ጭቆና ጋር ሲደራረብ የሰውነት ክብር እንደምን ይፈተናል?
 • በምዕራቡ ዓለም የገንዘብና ባንክ ተቋማት፣ እንዲሁም በቻይና መንግሥት አፍንጫዋን በብድር ተሰንጋ ትንፋሽ እያጠራት ያለችው ኢትዮጵያ ምንድነው የሚበጃት?
 • 85 በመቶ የሚሆኑትን የአገራችንን ደሃ ገበሬዎች፣ ወገኖቻችንን ከዘወትር ሰቀቀን፣ ሰብአዊነትን ከሚፈታተን ድህነት ለዘለቄታው ማፋታት የምንችለው እንዴት ነው?
 • እኛ ሠልፍ በመውጣት የትግሉን ብሥራትና የሚታየውን ተስፋ በመደገፍ ውስጥ አብረን ለግፈኞች ኃይላችንንና በቃን ማለታችንን ያሳየን የአገር ሰዎች ይኼንን ፍቅርና መተሳሰብ እንዴት ወደ ወገን ደራሽነት ልንለውጠው እንችላለን?
 • ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በአገራችን ውስጥ የተፈናቀሉት፣ ከሕፃናትና አረጋውያን ቤተሰቦቻቸው ደጅ የሚባዝኑት ወገኖቻችን ምን ይበጃቸው? በአሁኑ ሰዓት እኔና እናንተ ምን እናድርግ?
 • በእስርና በዘግናኝ ድበደባ ሲንገላቱ የነበሩትን በሺሕ የሚቆጠሩ ወገኖቻችንን እንደምን መንፈስና ሰውነታቸውን መልሰን እናቋቁም?
 • ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት ችለውም ሆነ ሳይችሉ በሥራ አጥነት ተስፋቸው ተመናምኖ ለአመፅ የወጡትና አሁን አዲስ ተስፋ ለሰነቁት ወጣት ሴቶችና ወንዶች ኢትዮጵያውያን መውጫ መላ አንድ ሁለት ሐሳብ አዋጡ ብንባል ምን እንላለን? ችግሩስ እንዲያው ደርሶ ዘወር የሚል ነው?
 • ንግድ በዋናነት ለማትረፍ የሚፋለሙ ሰዎች ሌሎቹን የሚድጡበት ነውና እንዴት ያለ ሥርዓት ይሆን ድሆች ሁልጊዜም ከጨዋታ ውጪ የማይሆኑበትን መላ የሚያበጀው?
 • እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲሉ፣ እንኳንስ የኖረ ድህነት፣ ዓይን ያወጣ ሥርዓትን የፈጠረ ሌብነት እንዲሁም የብድርና የበጀት አዘቅት ኖሮብን ይቅርና እንዲያውም የውጭ መዋዕለ ነዋይ (ኢንቨስትመንት) ማግኘት ከባድ ነው። ተሳክቶልን የውጭ የቢዝነስ ሰዎችን ወደ አገራችን ስናመጣ ደግሞ ጭቆናውም ዓይኑን አፍጦ ይመጣል። ምንድነው መላው?
 • ኪነ ጥበብን በንግድ ሒሳብና ገጽታ ግንባታ አልፎም በፍራንክ ማምጫ መሣሪያዊ (Instrumentalist) እና ንግዳዊ (Entrepreneurial) አስተሳሰብ መመልከቱ የት ያደርሰናል? ኪነ ጥበብን የሰውን ልጅ ውስጠት በሒስ እንደመፈተሻ፣ እንደ ርዕዮተ ዓለማዊ የፍልሚያ ሥፍራ፣ በቅርፅ እንደመደሰቻ፣ እንደማሰቢያ ብናስባት ፖለቲካ ምን መልክ ይኖረዋል ወይም የቱጋ ነው ጥበብና ፖለቲካ የሚቆራረጡት? መልካም ሐሳብ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles