Sunday, July 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሐምሌው ፍሬ - ‹‹አባ በዝብዝ ካሳ››

የሐምሌው ፍሬ – ‹‹አባ በዝብዝ ካሳ››

ቀን:

‹‹አባ ታጠቅ›› በሚል የፈረስ ስም የሚታወቁት ዳግማዊ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ በ1860 ዓ.ም. ከተሰዉ በኋላ በመንበራቸው ላይ ለሦስት ዓመት የተቀመጡት አፄ ተክለ ጊዮርጊስ ነበሩ፡፡ ከሳቸው በኋላ ‹‹ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ዘውዱን 1864 .. የደፉት ‹‹አባ በዝብዝ›› በሚል የፈረስ ስም የሚታወቁት አፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (አራተኛ) ናቸው፡፡  

ከ187 ዓመታት በፊት ሐምሌ 5 ቀን 1823 .ም. በትግራይ ተምቤን ልዩ ስሙ መልፋ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ ከአባታቸው ሹም ተምቤን ምርጫ ወልደ ኪዳን እና ከእናታቸው ወ/ሮ ሥላስ ድምፁ  ሲወለዱ ካሳ የተባሉት አፄ ዮሐንስ፣ በአፄ ቴዎድሮስ የተጀመረውን የአንድነት መንገድ በማጠናከርና ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪዎች (ከግብፅ፣ ከቱርክ፣ ከጣሊያንና ከእንግሊዝ) ለመታደግ በጉንደት፣ ጉራዕ፣ ዶግዓሊ ወዘተ.) በርካታ ጦርነቶችን አድርገው በድል ተወጥተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ባይሩ ታፍላ ያሳተሙት ዜና መዋዕል እንደሚለው፣ በአባታቸው በኩል ጎንደር መንግሥት ከአፄ ኢያሱ ብርሃን ሰገድ ሞት ወዲህ (1747 ዓ.ም.) መጀመርያውና ኃይለኛው የትግራይ መስፍን ከነበሩት ከራስ ስሁል ሚካኤል፣ ከራስ ወልደ ሥላሴና ከደጃች ሰባጋዲስ ይወለዳሉ፡፡

አፄ ዮሐንስ በደጃች ካሳነታቸው ዘመን በተወለዱበት ሐምሌ 5 ቀን በ1863 ዓ.ም. አፄ ተክለ ጊዮርጊስን ድል ካደረጉ ወዲህ እስከ ጥር ወር ድረስ ባለው የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ለሥርዓተ ንግሥ የሚያስፈልገውን ማንኛቸውንም ዝግጅት ማድረጋቸው በታሪክ ተጽፏል፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹አፄ ዮሐንስና የኢትዮጵያ አንድነት›› በሚለው መጽሐፋቸው ስለድግሱ እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹…ድግሱም ሲሰናዳ ቆይቶ በጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም. በአክሱም ቤተ ክርስቲያን ስመ መንግሥታቸው ‹ዮሐንስ አራተኛ› ተብሎ በጳጳሱ በአቡነ አትናቴዎስ እጅ ተቀብተው በሥርዓተ መንግሥት ነገሡ፡፡ በዚሁ ንግሥ ምክንያት ሦስት ቀን በዓል ሆኖ ለግብር 4,000 ሠንጋ ታርዶና 50 ጉንዶ ማር የፈጀ 150,000 ገንቦ ጠጅ ቀርቦ በደስታ ሲበላ ሲጠጣ እንደ ሰነበተ ሙሴ ጂ. ዲወ በዝርዝር ጽፎ አትሞታል፡፡ የአገራችንም ጸሐፊ አለቃ ዘዮሐንስ የንግሡን ሁኔታ በመጥቀስ ከነገሡ በኋላ በቤተ መቅደስ ወርቅ መበተናቸውን 30 ቀን ሙሉ የደስታ በዓል መደረጉን ጠቅሰውታል፡፡››

ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹Innovation and Misoneism during the Reign of Emperor Yohannes IV (1872.1889)›› በሚለው ጥናታቸው እንደገለጹት አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሥርዓት በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በከተማ ልማት (ደብረ ታቦርና ደሴ) በዘመናዊ ሕክምና፣ በክትባት፣ በክሊኒክ ምሥረታ (ዓድዋና ጎንደር) ቅርስ ከእንግሊዝ በማስመለስ (ክብረ ነገሥትና ዕደ ጥበባት) የባርያ ንግድን የማስቆም ድንጋጌንም በማውጣት ይጠቀሳሉ፡፡

የአፄ ዮሐንስ ጦርነቶች

በአፄ ዮሐንስ ዘመን ከነበሩት ጦርነቶች በጉንደት፣ ጉራዕና ዶግዓሊ የተካሄዱት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ የጉንደትና ጉራዕ ጦርነቶች መንሥኤ የግብፅ መሪ ከዲቭ ኢስማኤል ነው፡፡ በታሪክ እንደተመዘገበው፣ ብዛት ያላቸውን የአውሮፓ ተወላጆች በገንዘብ እየቀጠረና የፓሻነት ማዕረግ እየሰጠ፣ በግብፁ ወታደር ላይ መሪ በማድረግ ራሱ በቱርክ ሱልጣን ከመገዛት ሳይድን ኢትዮጵያን በጦር ኃይል ወሮ ከሱዳንና ከሱማልያ ጋር በመደባለቅ ግዛቱን ከሜዲተራኒ ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ ለማድረስ ሰፋ ያለ ምኞት አድሮበት ነበር አባ በዝብዝ ካሳ አፄ ዮሐንስ አከሸፉበት እንጂ፡፡

እንደ አቶ ተክለ ጻድቅ አዘጋገብ፣ ‹‹በዚህ ጊዜ አንደኛ በአገር ውስጥ የነበረው መከፋፈል፣ ሁለተኛ የኢትዮጵያ በሥልጣኔ ኋላ ቀርነት፣ ሦስተኛ የስዊዝ ቦይ መከፈት አደፋፍሮት ይህ ሰፊ ምኞት አያዋጣህም፣ በከንቱ አትክሰር የሚለው የዘመድ መካሪም አላገኘም፡፡ ይልቁንም ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ‹ይገባሃል ያስፈልግሃል ግፋ በርታ› የሚሉት የውጭና የአገር ተወላጆች በረከቱለት፡፡

‹‹ይኽን የወረራ ምኞቱን ወደ ፍፃሜ ለማድረስ በ1866 ዓ.ም. በኅዳር ወር ጉንደት ላይ በ1868 ዓ.ም. በየካቲት ወር ጉራዕ ላይ ወታደር ልጆች ሁለት ጊዜም ‹ያልሠለጠነ መንጋ ወታደር ነው› ብሎ በናቀው በአፄ ዮሐንስ ጦር ድል ተመታ፡፡ የተማረከውን የግብጥ ልዑልን በሁለት ሳጥን ወርቅ ብቻ አልመለሱትም ‹‹ያገሬን አፈር ይዞ እንዳይሄድ›› ብለው እግሩን አሳጥበው አስሻገሩት፡፡

 ‹‹የሆነ ሆኖ በዚህ በሁለተኛው ድል አድራጊነት የአፄ ዮሐንስ ዝና በያለበት እየተሠራጨ ሲሄድ የግብፅ መንግሥት በአገር ውስጥም በውጭም እየተዋረደ ሄደ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም ቀድሞ በውስጡ ዘውድ የደፋ አንበሳ ያለበት ዙሪያውን ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ ዘኢትዮጵያ የሚለውን ማኅተማቸውን አስፈርሰው፣ ‹‹መስቀል ሞአ እስማኤላውያን›› የሚለውን ማኅተም አሠርተው በዚህ ማኅተም ከውጭ አገር መሪዎች ከአገር ውስጥ መኳንንትና መሳፍንት ጋር ይጻጻፉ ጀመር፡፡ መስቀል ሞዓ እስማኤላውያን፡ ማለት መስቀል የእስማኤል ተከታዮችን አሸነፈ ለማለት ነው፡፡

የሆኖ ሆኖ አፄ ዮሐንስ ሁለት ጊዜ በግብፆች ላይ ያገኙት ድል አድራጊነት በወታደርነት መስክ ዝናቸውን በያለበት እያደመቀው ሄዷል፡፡ ድል አድራጊነታቸውን በማውሳት አንዱ ገጣሚ እንደዚህ ሲል አሞግሷቸዋል፡፡

‹‹ከላይ የወረደው ከጽዮን መቅደስ

ባባቱ ሚካኤል ÷ በናቱ ሥላስ

አጨደው ከመረው፤ ያን ያሕዛብ ገብስ

ወቃው ደበደበው ሰጠው ለነፋስ

ዐሊሙ ነፍጠኛ አፄ ዮሐንስ!››  

82 ዓመታት በፊት ታዋቂው ሠዓሊ አገኘሁ እንግዳ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር መተማ ላይ ሰማዕት ለሆኑት አፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (አራተኛ) የገጠሙት ግጥምም እንዲህ የሚል ነው፡፡

‹‹ዮሐንስን ጥሩ እሱ ይያዘኝ
    እስኪ ካሳን ጥሩ በል አንተ ያዘኝ
     ቴዎድሮስን ወስዶ ካሳ አንተ ሰጠኝ

እጅግ ደስ ይለኛል ያንተ ስም ሲነሣ

የቁና ዐፈር ንፉግ አንተ ነህ ወይ ካሳ፡፡››

‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› በሚል 1928 .. በሠዓሊው የተጻፈው ተራኪ ግጥም ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ አፄ ምኒልክ ድረስ ይዘልቃል፡፡ ለዘመናዊት ኢትዮጵያ፣ 19ኛው ምዕት ዓመቷ ኢትዮጵያ በር ከፋች የነበሩት በዱሮ ስማቸው ካሳ ኃይሉ፣ በንግሥና ስማቸው አፄ ቴዎድሮስ ዳግማዊ (ሁለተኛ) ለአሐዳዊት ኢትዮጵያ መነሣት በቀዳሚነት ሲጠቀሱ፤ ማዕከላዊው መንግሥት ተጠናክሮ ‹‹ፌዴራላዊ›› በሚመስል መልኩ ለአካባቢያዊ ገዢዎች ሥልጣን በመስጠት አሐዳዊቷን ኢትዮጵያ አጠናክረው ብቅ ያሉት ደግሞ በዱሮ ስማቸው ካሳ ምርጫ በንግሥና ስማቸው አፄ ዮሐንስ ራብዓዊ (አራተኛ) እስከ መጠርያቸው ‹‹ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ናቸው፡፡

አገኘሁ ከመጀመርያው ካሳ (ቴዎድሮስ) በኋላ ከተክለ ጊዮርጊስን ቀጥሎ የመጡትን ካሳ (ዮሐንስ) መተማ ላይ የፈጸሙት ጀብዱና የከፈሉትን ሰማዕትነት 17 ዓመት የሥልጣን ዘመናቸው ሉዓላዊት ኢትዮጵያን በማጠናከራቸው፣ በኢትዮጵያ ድምፅነት

‹‹ዮሐንስን ጥሩ እሱ ይያዘኝ
     እስኪ ካሳን ጥሩ በል አንተ ያዘኝ

ቴዎድሮስን ወስዶ ካሳ አንተ ሰጠኝ›› ብለው ስንኞችን አሰሩ፡፡

1881 .. በመጋቢት መባቻ ቆስለው በማግስቱ ያረፉት ዮሐንስ ሰማዕት መሆናቸውንም ተከትሎም አገኘሁ ተራኪ ግጥማቸውን፡-

‹‹ዮሐንስ ካሳህን ማን ሊችለው ነው፣

ከዘውድ ይልቅ ሞትክን አንተ የመረጥኸው

እንዳንተ ለድርጎ ዐፈር ንፉግ ሰው የለም፣

በደምበር ላይ ብትሞት አይደነቅም፤›› ብለው ዘለቁበት፡፡

እንደ አገኘሁ እንግዳ ምሥጠራ የአገሬን አፈር ባዕድ ይዞት አይሄድም ብለው እግር ያሳጠቡት አፄ ዮሐንስ በደምበር ላይ መሞታቸው መደነቅ ሳይሆን ለድርጎ አፈር ንፉግ ሆነው መገኘታቸውና ‹‹እምቢ ለአፈሬ›› ማለታቸውንና ታላቅነታቸውን ያጎሉበት ስንኝ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...