Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለሕዝብ ቁጥር ዕድገት ልጓም ለማበጀት

ለሕዝብ ቁጥር ዕድገት ልጓም ለማበጀት

ቀን:

ከሃምሳ ዓመታት በፊት በኢራን ቴሄራን ከተማ በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉባኤ ላይ የቤተሰብ ዕቅድ ወይም የወሊድ ምጣኔ ሰብዓዊ መብት እንዲሆን መደንገጉ ይታወሳል፡፡ መንግሥትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይህንን አዋጅ እንዲያከብሩና እንዲያስጠብቁ፣ እንዲሁም መረጃዎች፣ ትምህርቶችና ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶች ለቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚዎች ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ የማመቻቸትና የማስተባበር ኃላፊነት የሚጥሉባቸው ኮንቬንሽኖችና ስምምነቶች በተለያዩ ጊዜ መፅደቃቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የቤተሰብ ዕቅድ ለሥነ ተዋልዶ ቁልፍ መነሻ ከመሆኑ ባሻገር የጤና የትምህርትና የመከባበር መሠረት ነው፡፡ ይህም ማለት ልጅ የመውለድ፣ ያለመውለድ፣ መቼ?፣ ስንትና ከማን መውለድ እንደሚቻል፣ እንዲሁም አቅምን ባገናዘበ መልኩ ምን ያህል ወይም በቁጥር ስንት መውለድ እንደሚያስፈልግ የሚጠቁሙ ኃላፊነቶች የተካተቱበት አካሄድ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም 700 ሚሊዮን የሚጠጉ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎት ተጠቃሚ ሴቶች ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶችን የሚጠቀሙ እናቶች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይህም አገሪቱ ሁሉን አቀፍ የሆነ የቤተሰብ ዕቅድን ለማሳካት በፈጣን ጎዳና ላይ መሆኗን ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ 35 በመቶ ወይም አንድ ሦስተኛ የሚሆኑ ያገቡ ሴቶች የመጀመርያ ልጅ ከወለዱ በኋላ ቀጣዩ የመውለጃ ጊዜያቸው ቢያንስ በሁለት ዓመት እንዲራዘምላቸው ይሻሉ፡፡ 24 በመቶ ያህሉ ያገቡ ሴቶች ደግሞ ተጨማሪ ልጅ መውለድ አይፈልጉም፡፡ የመውለጃ ጊዜያቸው እንዲራዝምላቸውና ተጨማሪ ልጅ የማይፈልጉ ሴቶች የቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው፣ ከዚህ አንፃር በአጠቃላይ 58 በመቶ የሚሆኑ የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀም እንደሚፈልጉ ማዕከላዊ የስታትስቲክስ ባለሥልጣን ዓቻምና ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል፡፡

በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም እንደሚሉት፣ እስካምና ድረስ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 94.4 ሚሊዮን ደርሷል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር ከአፍሪካ ሁለተኛ ያደርጋታል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሴቶች መብት ጥበቃና ለቤተሰብ ዕቅድ አገሪቱ ያላትን ቁርጠኝነት በሕገ መንግሥት አንቀጽ 35 ሥር በማካተት አሳይታለች፡፡ ከዚህም ሌላ የሴቶች ፖሊሲን በማውጣት የቤተሰብ ሕግን ጨምሮ በሌሎች ሕጎች ላይ ማሻሻያ አድርጋለች፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም ሰኔ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. የተካሄደውን የዓለም ሥነ ሕዝብ ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀው የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ምክትል ኮሚሽነሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ሶሳይቲና ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ ድርጀቶች በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ከሕዝብ የኑሮ ዕድገት ጋር ባጣጣመ መልኩ ለማሻሻል የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ የታመነበትና ሥራ ላይ ከዋለ 25 ዓመት የሞላው ብሔራዊ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ያስገኘው ጠንካራና ደካማ ውጤት ላይ ትኩረት ያደረገ ግምገማ ለማካሄድ ታቅዷል፡፡ ኢኮኖሚው በ1996/97፣ እና በ2008/09 በየዓመቱ በአማካይ 10.7 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ፣ በአንፃሩም የድህነት መጠኑ በ1987/88 ዓ.ም. ከነበረበት 45.5 በመቶ በ2007/08 ወደ 23.5 በመቶ ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡ በሕይወት የመቆየት ዕድሜ ጣሪያ በ1992 ዓ.ም. ከነበረበት 51.9 የዕድሜ መጠን በ2007 ዓ.ም. ወደ 64.7 ዕድሜ ከፍ ማለቱንም አብስረዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሰሃርላ አብዱላሂ ‹‹በ2012 ዓ.ም. ተጨማሪ 6.2 ሚሊዮን ሴቶች፣ አዋቂዎችና ልጃገረዶች የቤተሰብ ዕቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት እየሠራን ነው፡፡ በቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድርሻ ግብዓት ማቅረብ ቴክኒካዊ ዕገዛ በማድረግ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን የእናቶችና ሕፃናት ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

ጽንስ ማቋረጥ ወንጀል እንደሆነ፣ ይህም ሆኖ ግን የሚፈቀድበት ሁኔታዎች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡ ከሁኔታዎቹም መካከል አንደኛው ጽንሱ በእናትየው ጤንነት ላይ አደጋ የሚያስከትል ሆኖ ከተገኘ ጽንሱ ራሱን የቻለ የጤና ችግር ያለበት ሆኖ ከተገኘ በጤና ባለሙያዎች ውሳኔ ጽንሱ እንዲቋረጥ ይደረጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በሕግ በተፈቀደ አግባብ ፅንስ የሚቋረጥበት አካሄድም አለ፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መረጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ተወካይ ሚስ ጊላን ሚልሰን፣ ‹‹ኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥሯ በየዓመቱ ሦስት በመቶ እየጨመረ የመጣና በዓለም ውስጥ በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ከሚገኙት አገሮች አንዷ ነች፡፡ አሁን ያለውም የሕዝቧ ቁጥር ከ30 ዓመታት በኋላ ወደ 200 ሚሊዮን እንደሚያድግ ይገመታል፤›› ብለዋል፡፡

የወሊድ መጠን ቅነሳው ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተከናወነ የድህነት ቅነሳን ለማፋጠን፣ በወሊድ ሳቢያ የሚከሰተውን የእናቶችና ሕፃናት ሞት መጠንን ዝቅ ለማድረግና የአገሪቱ የፆታ እኩልነት አጀንዳን በማሻሻል ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

ከተወካይዋ ማብራሪያ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 ዓመት የሆኑና በገጠር ከሚኖሩ አምስት ሴቶች መካከል አንዷ ብቻ የስምንተኛን፣ ከአሥሩ ደግሞ አንዷ የአሥረኛን ክፍል ትምህርት ታጠናቅቃለች፡፡ ከፍ ብሎ በተጠቀሱት የዕድሜ ክልሎች የሚገኙና በገጠር ነዋሪ ከሆኑት ሴቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ማንበብና ፍፁም አይችሉም፡፡

ልጃገረዶችን ማስተማር ለአገሪቱ የልማት አጀንዳ ዋና ስትራቴጂ እንደሆነ፣ ይህም ሁኔታ የወሊድ መጠን ቅነሳን ከማፋጠኑም ባሻገር ምርታማ የሆነ ግብረ ኃይልን በመፍጠር ረገድ የጎላ አስተዋጽኦ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ድርጅት (ዩኤንኤፍፒኤ) ተወካይ ሚስ ቢታና ማአሳ፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቱ በታዳጊ አገሮች በሚካሄደው የቤተሰብ ዕቅድ ዙሪያ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ አገልግሎቶችን በማቅረብ የጤና ሥርዓቱን በማጠናከርና የፆታ እኩልነትን በማበልፀግ ረገድ የሚያበርክተውን ዕርዳታና ዕገዛ ወደፊትም ቢሆን አጠንክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ላይም መንግሥታት፣ ፓርላሜንታውያን፣ የግሉ ዘርፍና ሲቪል ማኅበረሰብ ከጎኑ በመቆም የየበኩላቸውን ዕገዛ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...