Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መካሪ አያሳጣን!

ሰላም! ሰላም! እንደምን ሰነበታችሁ የተወደዳችሁ ኢትዮጵያዊያን! እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት እናቷ ማንጠግቦሽ ብለው ከሰየሟት እኔም ዘወትር ከማልጠግባት ውዷ ባለቤቴ ጋር 100 ቁጥር ያለበት ሻማ ለኩሰን በማብራት፣ ቡናችንን ፉት እያልን እያከበርን ነው፡፡ ባሻዬ ትኩስ ቡናቸውን ይዘው፣ ‹‹እነዚህ ታሪካዊ መቶ ቀናት ናቸው፤›› ሲሉኝ ልጃቸው ደግሞ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ የመቶ የመቶ ቀናት ዕቅድ እያወጡ መንቀሳቀስ ነው፡፡ የዓመት ዕቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ ዘመን ያለፈበት ነው፤›› እያለኝ ነበር፡፡ ባሻዬ ተገርመው የድሮ ዘፈን ማንጎራጎር ጀመሩ፣ ‹‹አታመጣው የለ እሷ ጉድ አትፈራ፣ አፈራረሰችው የጎጆዬን ጣሪያ፤›› ሲሉን ልጃቸው ያመጣው አዲሱ የቀን አቆጣጠር እንዳልጣማቸው ገብቶናል፡፡

አንድ ሁሉንም ከጥንት ጋር ማወዳደር የሚወደድ ደላላ ጓደኛዬ፣ ‹‹እነማን ናቸው የሚባሉት ለመቶ ዓመት ከሠሩት የሚበልጥ ተዓምር ነው የተሠራው፤›› ሲል ሌላው ደላላ፣ ‹‹ያልተጋነነ ነገር የት ሄጄ ነው መስማት የምችለው?›› እያለ ምሬቱን አሰማ፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰው የማያጋንነው ዕድሜውን ብቻ ነው፤›› ያለኝን አስታውሳለሁ፡፡ ባሻዬም በበኩላቸው፣ ‹‹ሰው በገዛ ገንዘቡ የገዛው ጫማ ላይ ዋጋ መጨመር፣ ካልሲ ቢገዛ እንኳን ዋጋውን ያጋንነዋል፡፡ እሺ ያልተጋነነ ምን አለ?›› አሉን፡፡

የባሻዬ ንግግር አንድ ሐሳብ አጫረብኝ፡፡ ቤትም ሆነ መኪና ሳሻሽጥ ዋጋ ጨመር ማድረግ ግድ ይላል፡፡ እሱ ብቻም አይደለም፡፡ ቤት ሻጮች ጨምረው ነው የሚናገሩት፡፡ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹በዚህ ዘመን የቀነሰው ዕድሜ ብቻ ነው፤›› ሲለኝ ብዙ አይገባኝም ነበር፡፡ ዛሬ ግን ባሻዬ እንኳን ዕድሜዎት ስንት ነው ሲባሉ፣ ‹‹ገና መቶ ቀኔ ነው፤›› እያሉ ይስቃሉ፡፡ ወዳጄ ዕድሜዎት ስንት ሆኖ ይሆን? ጨምሮ ይሆን ወይስ ቀንሷል? ወይስ ባለበት ቆሟል? በነገራችን ላይ ሰላሳ ዘጠኝ ዓመቱ ላይ የቆመውን የጓደኛዬን ጉዳይ ሳላጫውታችሁ አላልፍም፡፡ ይኼው አሥር ዓመት ገደማ ሞላው ሰላሳ ዘጠኝ ላይ ከቆመ፡፡ አርባን ፍራቻ ሰላሳ ዘጠኝ ላይ እንደቆመ አርባ ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ እንዲያውም አንድ ወዳጃችን፣ ‹‹አንተ ግን ሰላሳ ዘጠኝን እንደ ስም ነው እንዴ ያወጡልህ?›› በማለት ቀልዶ አስቆበታል፡፡  

የባሻዬ ልጅ ፌስቡክ ላይ አንብቦ ካካፈለኝ፣ ‹‹አምላኬ ሆይ ከመቶ ቀናት በፊት የኖርኩትን ዕድሜ አትቁጠርብኝ፤›› ያለችው ጉብል ከዚያ በፊት ምናልባት ሰላሳ ዘጠኝ ዓመት ላይ ቆማ ይሆናል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ ‹‹ኢትዮጵያ የመቶ ዓመታት ነው ወይስ የመቶ ቀናት ታሪክ ያላት?›› ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ ሌላው ደላላ፣ ‹‹አንተ ያለፈውን እየናድክ የምትሄደውን ነገር ጠቅላዩ እንኳን እንደማይስማሙበት ዕወቅ፤›› እያለ ሲከራከረው ነበር፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ደግመህ አትጠይቅ፤›› ብሎ ሲቀልድበት ተባብረን ሳቅን፡፡

ማንጠግቦሽ የመቶ ቀናት ዕቅድ አውጥታ ግድግዳ ላይ ለጥፋለች፡፡ እኔንም እንዳወጣ እየጎተጎተችኝ ነው፡፡ ከእሷ ዕቅድ ውስጥ ጥቂቶቹን ላድርሳችሁ፡፡ የመጀመርያው የበደሏትን ጎረቤቶቿን ይቅር በማለት ያቆመችውን ቡና የመጠጣት ሥነ ሥርዓት እንደገና መጀመር፡፡ የማትጠቀምበትን ልብስ ሰብስባ ለቸገረው መስጠት፡፡ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ውስጥ መሳተፍ፣ ወዘተ፡፡ ታዲያ ይህችን ልበ ቀና ሴት ማን ይጠግባታል?

ባሻዬ የመቶ ቀናት ዕቅዳቸውን እንዳጫወቱን ከሆነ፣ በመጀመርያ አስመራ ካለው አንዱ ቤተስኪያን ተሳልመው መምጣት ነው፡፡ ከአስመራ መልስ ደግሞ ለተጨማሪ ፀሎት ወደ እስራኤል የመብረር ዕቅድ አውጥተዋል፡፡ እንግዲህ ሌሎቹም ዕቅዶቻቸው በዚህ ዙሪያ ያጠነጠኑ ናቸው፡፡ ያደለው እንደዚህ እየዞረ ቤተስኪያን ይስማል፡፡ ሌላው ደግሞ አስመራ ሄዶ ኮረዳ ለመሳም ይመኛል፡፡

የባሻዬ ልጅ አጠር አድርጎ ጠቅላያችን በ100 ቀናት ውስጥ ያከናወኑትን ሲያወራ እሱ ራሱ የእሳቸው አማካሪ ነው የሚመስለው፡፡ ‹‹እስር ቤቶች ባዶ ቀርተዋል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አዳፋ ስማቸው ተፍቆ በአዲስ ተስፋ አገራቸው ተገኝተው ወደ ሰላማዊ ትግል ገብተዋል፡፡ ከሥልጣናቸው ጋር በዘለዓለማዊ ቃል ኪዳን የተጋቡ ሰዎች ከሥልጣናቸው በሰላም ተሸኝተዋል፡፡ የሰበር ዜና ሱስ ውስጥ ጨምረውናል፡፡ አንፃራዊ የፕሬስ ነፃነት አምጥተዋል፡፡ በየአገሩ የታሰሩ ወገኖቻችንን ለአገር ለምድራቸው አብቅተዋል፡፡ ቢሊዮን ዶላሮች ይዘው ከቸች ብለውልናል፡፡ እነሆ የዶላር ዋጋ ዛሬ በጥቁር ገበያ ሳይቀር በቂጡ ዘጭ እንዲል በጎ ጅምር አሳይተዋል፡፡ ከኤርትራዊያን ወንድሞቻችን ጋር የነበረውን ፀብ ሽረው ወደ ፍቅርና ሰላም ጠርተዋል፡፡ ምሕረትን፣ ፍቅርንና ይቅርታን ያለ መጠን ሰብከዋል፡፡ እነዚህንና ተዘርዝረው የማያልቁ የሺሕ ቀን ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ በተለይ ስብሰባን ከሥራ ቀን ሸኝተውልናል . . . ›› አለ፡፡

የባሻዬ ልጅ ብዙ ሰው የማድነቅ ባህሪ ባይኖረውም፣ ሰሞኑን ግን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲጎዘጎዝ ነበር፡፡ ለእሳቸው ማን ያልተጎዘጎዘ አለ? ባሻዬ እንኳን፣ ‹‹እግዜሩ ዕድሜያቸውን ያርዝምልኝ፤›› ነበር ያሉት፡፡ ከዚህ የባሻዬ ፀሎት ጋር አሜን በማለት መደመር ሳያዋጣ አይቀርም፡፡ እኛም ታዲያ እንደ አቅሚቲ የመቶ ቀናት ዕቅድ ማውጣታችን አልቀረም፡፡ በመጀመርያ ያው የመላው ደላሎች ማኅበር በቀን አሥር ብር እየቆጠበ በዓመት የሚገኘውን ገቢ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች መስጠት፣ በገንዘቡም ንፁህ የመጠጥ ውኃና ላይብረሪዎች መገንባት፣ መቼም ከእኛ በፊትም የነበሩ ከእኛ በኋላም የሚፈጠሩ ደላሎች እንደዚህ ሊያስቡ እንደማይችሉ እርግጠኛ ነን፡፡ ምክንያቱም ይኼ ትውልድ ትንሽ ከበድ ያለ ነው፡፡

እኛ በዚህ ዘመን ያለን ደላሎች በፈጠራ የተሞላን፣ አሸዋ ለግብፃዊያን አስማምተን የምንሸጥ ምጡቃን ነን ቢባል እንኳን ቃል ለማሳመር አይደለም፡፡ እውነታው ግን ሁሉም በያለበት ዘርፍ መምጠቅ አለበት፡፡ እነሆ ከፊታችን ብሩህ መቶ ቀናትን አስቀድመን በሚመጣው ጊዜ ታላላቅ ቁም ነገሮችን፣ ለራሳችን ብሎም ለምድራችን የምናበረክትበት እንዲሆን ከእነ መላው ቤተሰቦቼ እመኛለሁ፡፡

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ኪሳችንን ሊሰርቅ ከመጣው ሌባ በላይ ተግተን የምንጠብቀው ቀናችንን ሊዘርፍ የመጣውን ሌባ ነው፤›› ብሎኛል፡፡ ወዳጆቼ ቀን ከሚዘርፍ የቀን ሌባ እንጠንቀቅ፡፡ እሱም ስንፍና ይባላል፡፡ ስንፍናን አንቀበለው ዘንድ ሁላችንም ቆርጠን እንነሳበት፡፡ ሻማውን እናበራው ዘንድ ሁላችንም የነፍሳችንን ሻማ ጨምረን በእጃችን ላይ ያለውን ሻማ በመለኮስ በድጋሚ ወደ ገናናነት፣ በድጋሚ ወደ ከፍታ የምንደርስበት ዘመን እነሆ በደጅ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ‹‹ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ደግሞ ኢትዮጵያ እንሆናለን፤›› እንደተባለው ከፍ ከማለት በፊት ዝቅ ማለት እንደሚቀድመው ሁሉ እርስ በርስ መተዛዘን፣ መከባበር፣ መፈቃቀርና መረዳዳት ይኖርብናል፡፡ ይቅር የሚሉ ልቦች ከፍ ያደርጋሉና፡፡ ይቅር ባይነት አሸናፊ ያደርጋልና፡፡ ለፀብ የሚቸኩሉ በፍቅርና በይቅር ባይነት እንዲቆሙ አስተዋይና ይቅር ባይ ልቦች ያስፈልጋሉ፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት የጠለቀ ዕውቀት ባይኖረኝም፣ አረጋውያንና አዋቂዎችን አዳምጣለሁ፡፡ መልካም ምክር እንስማ፡፡ መካሪ አያሳጣንና፡፡ መልካም ሰንበት!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት