Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከሥራ ዓለም የመገለል ፈተና

ከሥራ ዓለም የመገለል ፈተና

ቀን:

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ተማሪ ነበር፡፡ እስከ ሦስተኛ ዓመት ድረስ  ይህ ነው የሚባል የጤና እክል አልነበረበትም፡፡ ነገር ግን ድንገት ጆሮው ላይ ባጋጠመው ችግር የጆሮው የመስማት አቅሙ ቀነሰ፡፡ ቀስ በቀስም ክፍል ውስጥ መምህራን የሚሉትን የሚያስተምሩትን ነገር መስማት ተሳነው፡፡ በሁኔታው ቢደናገጥም ተስፋ አልቆረጠም፡፡ በማዳመጫ በመታገዝ ትምህርቱን ለመቀጠል ወሰነ፡፡ ጋሻው ጥጋቡ በዚህ የመስማት ችግሩን ለመቅረፍ ቢችልም ያልጠበቀው ነገር ከፊቱ መጣ፡፡

በጆሮው ላይ የተከሰተው ችግር ከመማር እንደሚያግደው የተሰማቸው መምህሮቹ ሌላ ዲፓርትመንት እንዲቀይር ነገሩት፡፡ ይህ ምክር ሳይሆን ትዕዛዝ ነበር፡፡ ማዳመጫው የመስማት ችግሩን ስለሚቀንስ የጆሮው ችግር በትምህርቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ቢያስረዳቸውም ሊቀበሉት አልቻሉም፡፡ የሕክምና ትምህርት ከመማር እንደማያግደው የሚያረጋግጥ የሕክምና ማስረጃ ካላቀረበ በስተቀር መማር እንደማይችል አሳሰቡት፡፡ እሱም በተጠየቀው መሠረት መማር እንደሚችል የሚያረጋግጥ ማስረጃ ሰጣቸው፡፡ ትምህርቱን ተረጋግቶ ይከታተልም ጀመር፡፡

ይሁን እንጂ በዓመቱ መጨረሻ የጥጋቡ ውጤት ሳይተላለፍ ቀረ፡፡ ሁኔታው ግራ ቢያጋባውም ምናልባት በስህተት ተዘሎ ይሆናል በሚል ስለውጤቱ መምህሮቹን ጠየቃቸው፡፡ እነሱም የሕክምና ትምህርት ለመከታተል አቅም እንደሌለው አስረግጠው ነገሩት፡፡ ያቀረበው ማስረጃም ለዚህ ምላሽ እንደሚሆን ጠቅሶ ሊያሳምናቸው ሞከረ፡፡ አጋጣሚው የተከሰተው ያለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ሲሆን እስካሁን ጉዳዩ እልባት አላገኘም፡፡ አሁንም ያጋጠመው የጆሮ ችግር ከመማር እንደማያግደው የሚገልጹ የተለያዩ ማስረጃዎችን እያስጻፈ መምህሮቹን ለማሳመን እየጣረ ይገኛል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ ጋሻው ያሉ ብዙዎች በተለያዩ የአካል ጉዳቶች በሕይወታቸው ፈተና ውስጥ ይገባሉ፡፡ አካል ጉዳተኝነት በማኅበረሰቡ የእግዜር ቁጣና እርግማን ተደርጐ ይታሰብ ስለነበር፤ አካል ጉዳተኞች ከጓዳ እንዳይወጡ፣ ከማኅበረሰቡ እንዳይቀላቀሉና የቤተሰብ ጥገኛ ሆነው እንዲቆዩ ይገደዱ የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይባልም፡፡ ሁኔታው በአሁኑ ወቅት በከተሞች አካባቢ መሻሻሎችን ቢያሳይም በገጠር እምብዛም አልተለወጠም፡፡ በነፃነት አደባባይ ላይ ወጥተው ራሳቸውን እንዲገልጹ፣ ከማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉና የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ በዚህም ጥቂት የማይባሉ በራሳቸው እንዲተማመኑ ለማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ጋሻው ከጥገኝነት ለመላቀቅ የሚያደርጉት ሩጫ የሚገታባቸው፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ሳይካተቱ የሚቀሩ፣ በሥራ ስምሪት ላይ በሚያጋጥማቸው መድልዎ ሥራ አጥተው ሲንገላቱ ይስተዋላል፡፡

ችግሩ እንደቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት ዩናይትድ ኔሽን በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ በሠራው አንድ ጥናት ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑ በታዳጊ አገሮች የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ሥራ አያገኙም፡፡ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የወጣ የዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት መረጃ እንደሚለው ደግሞ በዓለም ላይ 650 ሚሊዮን የሚሆኑ አካል ጉዳተኞች ይገኛሉ፡፡ 470 ሚሊዮን የሚሆኑት ዕድሜያቸው ለሥራ የደረሰ ይሁን እንጂ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ስለማይካተቱ፣ የመማር ዕድል ስለማያገኙ እንዲሁም ሥራ ስለማያገኙ አገሮች በየዓመቱ ሊያገኙ ይችሉ የነበረውን 1.94 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚያጡ ያሳያል፡፡

ብዙ ጊዜ ቀጣሪዎች አካል ጉዳተኞችን ቢቀጥሩ በሥራ አካባቢ ችግር ሊፈጠርና   ተጨማሪ ወጪ እንደሚያስወጣቸው ስለሚሰማቸው አካል ጉዳተኞችን የመቅጠር ፍላጎት የላቸውም፡፡ ይህም በርካቶች አቅሙ እያላቸው የቤተሰብ ጥገኛ እንዲሆኑ አስገድዷቸዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ዓለም አቀፉ የሠራተኞች ድርጅትና ሌሎች ሰብዓዊ ተቋማት አካል ጉዳተኞች በሥራ የሚካተቱባቸውን ድንጋጌዎች አዘጋጅተዋል፡፡ በኢትዮጵያም በሰማንያዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ስምሪት የተመለከተ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡ ይሁንና የሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ እንዲሁ በአካል ጉዳተኞች በኩል ስለአዋጁ የነበረው ግንዛቤ አነስተኛ በመሆኑ አዋጁ ተፈጻሚነት ሳይኖረው ዓመታት አልፈዋል፡፡

ከ14 ዓመታት በኋላም የነበረውን አዋጅ የሚከልሰው አዋጅ ቁጥር 568/2008 ወጥቷል፡፡ ይህም አካል ጉዳተኞች አገሪቱ ከምትከተለው እኩል የሥራ ዕድል መርህ ጋር የሚጣጣም፣ ምቹ የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ በሥራ ላይ የሚደርስባቸውን መድሎ በፍርድ መድረኮች ለማስረዳት የሚችል አሠራር የሚዘረጋ ነው፡፡ አዋጁ በሥራ ላይ ከዋለ ጊዜ ጀምሮ የማይናቅ ለውጥ ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በቂ ነው ለማለት የሚያስደፍር ነገር የለም፡፡ ዛሬም በርካታ አካል ጉዳተኞች በሥራ ስምሪት ረገድ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እየገጠሟቸው ይገኛሉ፡፡

የመመረቂያ ጽሑፉን በአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ላይ የሠራውና በአካል ጉዳተኞችና በአካቶ ልማት ዙሪያ የጥናት ባለሙያ ዳኛቸው ቦጋለ እንደሚለው፣ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በመጀመሪያው አዋጅ ላይ የነበሩትን ክፍተቶች አሻሽሏል፡፡ ጥቂትም ቢሆን ለውጥ መፍጠርም ችሏል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተፈጻሚነቱ ሲስተጓጐል ይስተዋላል፡፡

ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው በተለያዩ የሥራ ማስታወቂያዎች ላይ አካል ጉዳተኛውን በግልጽ የማግለሉ ሁኔታ ቀርቷል፡፡ ነገር ግን በልዩ ልዩ የሥራ መደቦች የሚወጡት መስፈርቶች አካል ጉዳተኛውን በተዘዋዋሪም ይሁን በቀጥታ የሚገፉ ናቸው፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ የሚወጡ የሥራ ማስታወቂያዎች ተቀጣሪው መንጃ ፈቃድ እንዲኖረው ይጠይቃሉ፡፡ ነገር ግን ዓይነ ስውሮች መንጃ ፈቃድ ማውጣት አይችሉም፡፡ ይህም መሥፈርቱን ስለማያሟሉ በዕድሉ አይካተቱም ማለት ነው፤›› ሲል ለአንድ ሥራ የሚጠየቁ መስፈርቶች አካል ጉዳተኛውን በተዘዋዋሪ የማግለል ሁኔታ እንደሚታይባቸው ያስረዳል፡፡

ያነጋገርናቸው ብዙዎች እንደሚሉት የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት ችግር በተለይ በዓይነ ስውራን፣ መስማት በተሳናቸውና በኦትስቲኮች ላይ ጐልቶ እንደሚታይ ይገለጻል፡፡

በቂ የምልክት ቋንቋ መምህር አለመኖር መስማት በተሳናቸው ተማሪዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡ አብዛኞቹ ተማሪዎችም አምስተኛ ክፍል አይዘልቁም፡፡ ተሳክቶላቸው ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁትም በሥራ ቅጥር ላይ በሚደርስባቸው መድልዎ ሥራ አጥተው ይጉላላሉ፡፡

ወ/ሮ ቃልኪዳን ጌታነህ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ አንዳንድ ተሳክቶላቸው ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁ ቢኖሩም ብዙዎቹ ሥራ አያገኙም፡፡ ሥራ ለመቀጠር በሚያደርጉት ጥረትም የተለያዩ መጉላላቶች ይደርሱባቸዋል፡፡ በአንዱ የማኅበሩ አባል ላይ በቅርቡ የደረሰውንም እንዲህ ያስታውሳሉ፡፡

ሥራ ተወዳድሮ ለመቀጠር ወረፋ ይዟል፡፡ ነገር ግን ለሰዓታት ቢጠባበቅም አልተጠራም፡፡ ግራ የገባው ተወዳዳሪው ለምን እንደማይጠሩት በምልክት ጠየቃቸው፡፡ እነሱም ጥቂት እንዲጠብቅ ነግረውት ወደ ሥራቸው ተመለሱ፡፡ ከኋላው የተሠለፉት ተወዳዳሪዎች እየተጠሩ ማስረጃቸውን ሰጥተው ይመለሳሉ፡፡ እሱ ግን ባለበት ቀረ፡፡ አካባቢውም ጭር አለ፡፡

በነገሩ ግራ የተጋባው ሥራ ፈላጊም ውስጥ ገብቶ ሊጠይቃቸው ወሰነ፡፡ ነገር ግን ሁሉም በራቸውን ዘግተው ወጥተዋል፡፡ ሁኔታው ሥራ የማግኘት መብቱን የሚጻረር በመሆኑ ለመስማት የተሳናቸው ማኅበር ሪፖርት አደረገ፡፡

‹‹ቀጣሪዎች አካል ጉዳተኞችን በመቅጠር ተጨማሪ ወጪ እንደሚያጋጥማቸው ይሰማቸዋል፡፡ ስለዚህም በተቻላቸው ሁሉ ያርቋቸዋል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ እያሉ የሚያንገላቷቸውም ብዙ ናቸው፤›› የሚሉት ወ/ሮ ቃልኪዳን ተመሳሳይ ገጠመኞች በየጊዜው መኖራቸውን መፍትሔ ያገኙ ዘንድም ወደ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች እንደሚልኳቸው ይናገራሉ፡፡

ዕድሉን አግኝተው የሚቀጠሩትም ችግሮች ያጋጥሟቸዋል፡፡ አስተርጓሚ ስለማይኖር ከሥራ አጋሮቻቸው ጋር ለመግባባት ይቸገራሉ፡፡ ይህም በሥራቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ እንቅፋት እየሆነባቸው ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል አካል ጉዳተኛውን ያላገናዘቡ ሕንፃዎች መኖር ሥራ እንዳያገኙ ምክንያት የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ዳኛቸው ያጋጠመውን እንዲህ ያስታውሳል፡፡ ‹‹ከዓመታት በፊት ለአንድ ተቋም ባስገባሁት የትምህርት መረጃ ለፈተና ተጠራሁ፡፡ ከቦታው በሰዓቱ ብደርስም ሕንፃው ላይ መውጣት ባለመቻሌ ሳልፈተን ተመልሻለሁ፡፡ ስለጉዳዩ ለሚመለከተው አካል ለማመልከት ሞክሬም ነበር፡፡ ነገር ግን እዚያም የነበረው ሕንፃ መወጣጫ ስላልነበረው ትቼ ተመልስኩ፤›› በማለት አካል ጉዳኛውን ያላገናዘቡ ሕንፃዎች መኖርም ሌላው ፈተና መሆኑን ይናገራል፡፡

መሰል ችግሮች እንደ ዳኛቸው ባሉ የእግር ጉዳት ባለባቸው ሰዎች ላይ የተለመዱ ናቸው፡፡ ፈተናዎቹን አልፈው የሚቀጠሩ ጥቂቶችም ግን አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ጥቂት የማይባሉት ሥራ ሳይሠሩ እንዲከፈላቸው ይደረጋል፡፡ ይህም ለከፋ የአእምሮ ችግር እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ዳኛቸው ይናገራል፡፡ ‹‹አብዛኞቹ ቀጣሪዎች አካል ጉዳተኞች ይህንን ያንን መሥራት አይችሉም ብለው ደምድመዋል፤›› የሚለው ዳኛቸው በቂ መረጃ ስለማይገኝ ሁኔታውን ወደ ሕግ ለማድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ብዙዎችም በዝምታ እንደሚያልፉት ያስረዳል፡፡

ከዚህም ሌላ በማስተዛዘን ዓይነት ‹‹ይህ ዓይነቱ ሥራ እኮ ለአካል ጉዳተኛ አይሆንም፤›› በማለት አካል ጉዳተኞችን የሚያርቁ ቀጣሪዎች መኖርም ዋነኛ የችግሩ መንስዔ እንደሆነ ይነገራል፡፡

በሥራ ስምሪት አዋጁ በአንድ የሥራ ዘርፍ የተወዳደረ አካል ጉዳተኛ ከሌሎች ተፎካካሪዎቹ ጋር እኩል ነጥብ ቢያስመዘግብ፣ አልያም ያስመዘገበው ነጥብ ከሌላው ተወዳዳሪ በ3 ነጥብ ዝቅ ብሎ ቢገኝ ቅድሚያ ይሰጠዋል ይላል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ አልያም በሌላ አድሎአዊ አሠራር አካል ጉዳተኛው ሳይቀጠር ቢቀር ድርጅቱን የመክሰስ መብት አለው፡፡ በዚህም ጊዜ የተባለውን ድርጊት አለመፈጸሙን የማስረዳት ሸክሙ የሚያርፈው በተከሳሹ ላይ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡

ችግሩ በስፋት የሚስተዋለው በግል ተቋማት ላይ መሆኑን የሚናገሩት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፈለቀ ጀምበር ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በየተቋማቱ አዋጁን የማስተዋወቅና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ግፊት የማድረግ ሥራ ይሠራል፡፡ በደል የደረሰባቸው አካል ጉዳተኞችም ወደ ሕግ እንዲሄዱና ጉዳያቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢበዛ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንዲፈጸም ይረዳቸዋል፡፡

ነገር ግን ከዚህ ሁሉ አልፎ በአስፈጻሚ ተቋማት በተለይም በግል ድርጅቶች ላይ ችግሮች እንደሚታዩ፣ ይህንንም በየጊዜው በሚደረግ ቁጥጥር ለመለየት እንደሚሞከር፣ አንዳንድ ድርጅቶችም ሕጉን በሚገባ ሲፈጽሙና ለሌሎችም አርአያ የሚሆን አሠራር ያላቸው እንደሚያጋጥሙ፣ በተቃራኒ የሚሠሩ ተቋማት መኖራቸውንና ችግሩን ለመቅረፍ ቁጥጥሩን አጠናክሮ የመቀጠል ሥራ እንደሚሠራ አቶ ፈለቀ ይናገራሉ፡፡        

የቅርብ ጊዜ (እ.ኤ.አ. 2013) መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከአገሪቱ ሕዝብ መካከል 17.6 በመቶ የሚሆኑት አካል ጉዳተኛ ናቸው፡፡ 95 በመቶ የሚሆኑትም በከባድ ድህነት ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 55 በመቶ የሚሆኑት በቤተሰብ፣ በጐረቤትና በጓደኛ ላይ ጥገኛ ናቸው፡፡ ጥቂቶቹ የራሳቸውን ሥራ በመሥራት፣ በልመናና በቤት ሠራተኝነት ተቀጥረው በሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ይተዳደራሉ፡፡ ይህም የተለያዩ አገልግሎቶችን ባለማግኘት የተከሰተ ሲሆን የአካል ጉዳተኛውን መብት የሚጠብቁ ድንጋጌዎችን ተፈጻሚ በማድረግ የሚደርስባቸውን ፈተና መቅረፍ ግድ ይላል፡፡ 

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...