Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሃይማኖት መሪዎች ትውልዱን የማረቅ ሚና

የሃይማኖት መሪዎች ትውልዱን የማረቅ ሚና

ቀን:

በዓለም በርካታ ወጣት ካላቸው አህጉሮች አንዷ አፍሪካ ናት፡፡ ከአህጉሪቷ ሕዝቦች 35 በመቶው ከ15 እስከ 35 ዕድሜ ክልል ላይ በመገኘታቸው ‹‹ዘ ያንገስት ኮንቲነንት›› (ወጣቷ አህጉር) የሚል ስያሜ ተሰጥቷታል፡፡ በአፍሪካ አገሮች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶችና በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መርሆች ለወጣቶች ትኩረት የሚሰጡትም ለዚሁ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ከአህጉራዊ ስምምነቶች በተጨማሪ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣቶች ፖሊሲ በማውጣትና በልዩ ልዩ መንገዶች ወጣት ተኮር ሥራዎች ከሚያከናውኑ አገሮች ትጠቀሳለች፡፡

ወጣቶች አገር ተረካቢና የለውጥ ኃይል እንደመሆናቸው ሕይወታቸውን የሚመሩበት አቅጣጫ ከፍተኛ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ በአገራችን በተደጋጋሚ ከሚሰነዘሩ ጥያቄዎች አንዱ የኢትዮጵያ ወጣቶች እየተጓዙበት ያለው መንገድ ነው፡፡ በሱስ መጠመድ፣ የሥራ ተነሳሽነት መቀነስ፣ ስደትና ሌሎችም በርካታ ችግሮች የተጋረጡባቸው ወጣቶች ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ባለው አካሄድ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ እንደሆነ የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ፡፡ ባለድርሻ አካሎች ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ቢያደርጉም የጎላ ለውጥ አለመምጣቱን የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡

ቅዳሜ መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ የተካሄደው አምስተኛው የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ጉባኤ ያተኮረው በዚህ ጉዳይ  ነበር፡፡ ‹‹የዘመኑ ወጣቶች ላይ የተጋረጡ ችግሮችን በመቅረፍ ተግባር ላይ የአብያተ ክርስቲያናት ሚና›› በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ጉባኤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንና የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት የሃይማኖት መሪዎች፣ ተመራማሪዎችና ወጣቶች የተወያዩበት ነበር፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስለመጣው ችግር መንስዔ፣ እያስከተለ ስላለው ጉዳትና  ችግሩን በመቅረፍ ረገድ የሃይማኖት መሪዎች ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚያመለክቱ ጥናቶች ቀርበዋል፡፡ በጉባኤው የተገኙት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አባል ቤተ ክርስቲያኖች የተውጣጡ ወጣቶች ጥናቶቹን በመመርኮዝ አንዳች ለውጥ ለማምጣት ጥረት እንዲያደርጉም ተጠይቀዋል፡፡

በወጣቶች ላይ የተጋረጡ እንቅፋቶች ላይ ጥናት የሠሩት መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር ችግሮቹ ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዘው እንደሚመጡ ይናገራሉ፡፡ በቀደመው ትውልድና በአሁኑ መካከል ያለው የትውልድ ክፍተት ከማኅበራዊ መንስዔዎች አንዱ ነው፡፡ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቡ ባጠቃላይ ከወጣቱ ትውልድ ጋር ያላቸው ግንኙነት መላላቱ፣ ወጣቶችን ማረቅን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጥናታቸው ያሳያል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ በዚህ ዘመን የተንሰራፋው የቁሳዊነት አመለካከት በብዙ ወጣቶች ላይ እያጠላ ነው፡፡ ‹‹ቁሳዊነትና አንዳች እሴት ማጣት ወጣቶች ለማንነታቸው፣ ለሃይማኖታቸውና ለአገራቸው ያላቸውን አመለካከት ዝቅ ያደርጋል፤›› ይላሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋሞች ችግሩን ለመቅረፍ በቂ እንቅስቃሴ እንዳላደረጉም ያክላሉ፡፡ በርካታ ወጣቶች በአደንዛዥ ዕፆች ሱስ ቢጠመዱም፣ ከችግራቸው የሚወጡበት መንገድ አልተመቻቸላቸውም፡፡ የሃይማኖት ተቋሞችም ሕፃናትና አረጋውያንን ቢይዙም ወጣቶችን ያማከሉ አይደሉም ይላሉ፡፡ ‹‹ቤተ ክርስቲያን ትኩሱን ኃይል ወጣቱን አልያዘችም፤ ወጣቱን የመግዛት አቅሟ ደካማ ነው፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

አስተያየት ከሰጡ ወጣቶች አንዱ ተመሳሳይ ሐሳብ ሰንዝሯል፡፡ ወጣቶች በሉላዊነት (በግሎባላይዜሽን) ሳቢያ ለተለያየ ዓይነት አኗኗር እንደቀረቡ ተናግሮ፣ መንገዳቸውን የሚያስቱ ነገሮች ስለበዙ የሃይማኖት ተቋሞች ውጤት ተኮር እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡ በወጣቶች ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳድሩ ተቋሞች ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛውን ድርሻ እንደምትወስድ ገልጾ፣ ‹‹የሃይማኖት ተቋሞች›› አቀራረብ ዕድሜያችንና የወቅቱን ችግሮች ያማከለ ቢሆን ይመረጣል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡

‹‹በዘመኑ ወጣቶች ላይ የተጋረጡ ችግሮች መፍትሔዎች፤›› የሚል ጥናት የሠሩት ዶ/ር ገመቺስ ደስታም ተመሳሳይ የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡  ለትውልዱ የሚሰጠው ቦታ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ስለሚወስን በችግሩ ላይ መረባረብ እንደሚያሻ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ወጣትነት ታላላቅ ውጤቶች የሚገኙበት በተቃራኒው ደግሞ በስሜታዊነት ለሚመጡ ጥፋቶችም ቅርብ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋሞች የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ወጣቶችን ፈር የሚያስይዙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ እንዳለባቸው ያመለክታሉ፡፡

በጉባኤው አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማትም በወጣቶች ላይ በበቂ ሁኔታ አለመሥራታቸውን ተችተዋል፡፡ በገጠርም ይሁን በከተማ፣ ገንዘብ ያላቸውም ይሁን የሌላቸው ወጣቶች ለሱስ ይጋለጣሉ፡፡ ወጣቶቹ ከሚገጥማቸው ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ባሻገር አገሪቱ የሚደርስባት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ቤተ ክርስቲያን ምን ማድረግ አለባት? የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ጥናት ያቀረቡት ዶ/ር ኤልያስ ሌዊ፣ ወጣቶች በቀና መንገድ እንዲሄዱ በሃይማኖት መሪዎች ትምህርት መሰጠት እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ ወጣቶች የዕድሜ እኩዮቻቸውንና የአካባቢያቸውን ተፅዕኖ መቋቋም የሚችሉበት ሥነ ልቦና መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹ቤተሰብ ለልጆቹ ጊዜ መስጠት አለበት፡፡ ፈተና ሲገጥማቸው ከለላ ሊሆናቸው ይገባል፡፡ ቤተክርስቲያንም ለወጣቱ ጥያቄ ዝግጁ ሆና በትክክለኛው መንገድ መምራት አለባት፤›› ይላሉ፡፡

የችግሩ ሥር መስደድ ያሳሰባቸው ተሳታፊዎች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲፈለግ ሲያሳስቡ፣ ወጣቶቹ ከአኗኗራቸው አንፃር ያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አንዱ ወጣቶች ጊዜ የሚያሳልፉባቸው በቂ ቦታዎች አለመኖራቸው ሲሆን፣ ሌላው ለወጣቶች ሕይወት መስተካከል ኃላፊነት የሚወስዱ አካሎች ውስን የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ በተያያዥም አንዲት ወጣት ‹‹ቀድሞ የሥነ ምግባርና ሃይማኖት ትምህርት በትምህርት ቤት ይሰጥ ነበር፤ አሁን ግን በሥርዓተ ትምህርቱ የለም፡፡ ትምህርቱ ለወጣቶች ሥነ ልቦና መልካም አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ወደ ሥርዓተ ትምህርቱ ለምን አይመለስም?›› ስትል ጠይቃለች፡፡

ወጣቶች ችግሮቻቸውን ለመፍታት የምክክር መድረክ ሲያዘጋጁ ድጋፍ እንደማይደረግላቸው የተናገረች ወጣትም ነበረች፡፡ በመንግሥት፣ በትምህርት ቤቶችና በማኅበረሰቡ ዘንድ የተፈጠረው ክፍተት መሞላት እንዳለበትና ወጣቱ ትውልድ ከቀደምቶቹ ዕርዳታ እንደሚሻ ተመልክቷል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ በቀለ ኰርቶ፣ የመንግሥት እንቅስቃሴ በሃይማኖት መሪዎች ካልተደገፈ ለውጥ ለማምጣት እንደሚከብድ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጣቶችን ለማቃናትና የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የድርሻችንን እንወጣለን፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ ‹‹አገሪቱን የሚረከቡ ወጣቶች ዕድገት ላይ ካልተሠራ ነገ እኛኑ መልሶ የሚጎዳ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ጤናማ ትውልድ ለመፍጠር መረባረብ አለብን፤›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ሊቀ ጳጳስ ዘካቶሊካውያን፣ ወጣቶች የአኗኗር አቅጣጫቸውን እንዲያስተካክሉ ጠንካራ የቤተሰብ ትስስርና የሃይማኖት መሪዎች ጠባቂነት መኖር አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ዋና ጸሐፊ ፓስተር ጻድቁ አብዶ፣ ‹‹ወጣቶችን ላልተገባ አካሄድ የሚጋብዙ ነገሮች በጣም ብዙ ስለሆኑ፣ ወጣቶች ጠንካራ ሥነ ልቦና እንዲኖራቸው መሠራት አለበት፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በሃይማኖት መሪዎች፣ በተመራማሪዎችና በወጣቶች የተነሱት የመፍትሔ ሐሳቦች መሬት ላይ ወርደው ካልተተገበሩ፣ የጉባኤው መካሄድ ብቻውን መፍትሔ አልባ እንደሆነ በአጽንኦት የተናገሩም አሉ፡፡

  

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...