Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የፌዴራል ፖሊስ ተሽከርካሪ

ትኩስ ፅሁፎች

በአፍሪካ ጎዳና (ቦሌ መንገድ) መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለዳ ሲሽከረከር የነበረውና የአውራ ጎዳናውን አካፋይ ጥሶ ቁሳዊ ጥፋት ያደረሰው የፌዴራል ፖሊስ ተሽከርካሪ (ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው)

*******

ተስፋ ‘ምትባለው

            ከኤሚሊ ዲክሰን፣ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

የዶሮ ላባ አላት ተስፋ ‘ምትባለው

ቁጢጥ ብላ ነፍስ ላይ የምትቀመጠው፤

ዘፈን ትዘፍናለች አላንዳች ቃላት፤

ከቶ ሳታቋርጥ ቅምም ሳይላት፤

 

ወጨፎ ሲያናፍስ ይበልጥ የምትጥመው፣

ምን የሆነ ማዕበል ምንስ ቢከፋው

ነው ትንሺቷን ወፍ የሚያሳፍረው

ስንቱን እያጽናናች የምታሞቀው፡፡

 

አዳምጫታለሁ ከሁሉም በባሰ በብርዳማ አገር፤

ፈጽሞም እንግዳ በሆነው ባሕር፣

ምንም ቢቸግራት ምንም ብትጨነቅ፤

አንዲት ፍርፋሪ ጠይቃኝም አታውቅ፡፡

**************

የዊልያም ሼክስፒር አፅም የራስ ቅል ጠፋ

የዊልያም ሼክስፒር አፅም የራስ ቅል ከመቃብር ስፍራው መጥፋቱን አርኪዮሎጂስቶች መደምደማቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

እውቁ እንግሊዛዊ ደራሲ ሼክስፒር ከሞተ ከ400 ዓመታት በኋላ አርኪዮሎጂስቶች ከምድር በታች የሚሠረስር ራዳር እንዲጠቀሙ በተፈቀደላቸው መሠረት የሼክስፒር የራስ ቅል ከመቃብር ሥፍራው አለመኖሩን ሊያውቁ ችለዋል፡፡ የስታፎርድ ቫየሩ አርኪዮሎጂስት ኬቨን ኮልስ ‹‹የሼክስፒር የራስ ቅል ከተቀበረበት ቅድስት ሥላሴ መካነ መቃብር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ›› ብለዋል፡፡

ይህ ግኝት የሼክስፒር አፅም ያረፈው የት ነበር የሚለውን? ምስጢራዊም አወዛጋቢም እንደሚያደርገው ይጠበቃል፡፡ በመቃብሩ ላይ ጥቅስ እንጂ የሼክስፒር ስሙ የለም፡፡ አርኪዮሎጂስቱ እንደሚሉት ስለሼክስፒር መቃብር የተባሉ ብዙ ነገሮች ሲኖሩ ብዙዎች አወዛጋቢ ናቸው፡፡

***************

‹‹እኔ ሌባ ነኝ›› የሚል ጽሑፍ ያለው ልብስ መልበስ የመረጠ

የኦሐዩ ነዋሪ የሆነው ግሬድ ዴቭንፖርት፣ ከዎልማርት የሰረቀውን 52 ኢንች ቴሌቪዥን አስመልክቶ ክስ ይቀርብበታል፡፡ ፍርድ ቤት ቆሞ ሲከራከርም ሌብነቱ ይረጋገጣል፡፡

አሶሸየትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ዴቭንፖርት ጥፋተኛ ሆኖ መገኘቱን ያረጋገጠው ፍርድ ቤት የቅጣቱን ዓይነት በሁለት ከፍሎ ምርጫ ያቀርብለታል፡፡ አንደኛው ቅጣት ለ30 ቀናት ያህል በማረሚያ ቤት መቆየት ሲሆን፣ ሁለተኛው ‹‹እኔ ሌባ ነኝ፣ ከዎልማርት ቴሌቪዥን ሰርቄያለሁ›› የሚል ጽሑፍ ያለበት ልብስ ለብሶ፣ በዎልማርት ሱቅ ፊት ለፊት ለአሥር ተከታታይ ቀናት፣ በቀን ለስምንት ሰዓት ያህል መቆም ነበር፡፡

ዴቭንፖርት ‹‹እኔ ሌባ ነኝ፡፡ ከዎልማርት ሰርቄያለሁ›› የሚል ጽሑፍ ያለው ልብስ ለብሶ አሥር ቀናት ማሳለፍን መምረጡን ዘገባውን ያሳያል፡፡

‹‹እስር ቤት ከመቆየት ሌባ ነኝ ማለት ይሻላል፡፡ ቅጣቱም ምቾቴን አልነሳውም›› ማለቱም ተገልጿል፡፡

*************

ውኃና ትምህርት

ትምህርትና ውኃ ይመሳሰላሉ ይባላል፡፡ ውኃ ለምድር ዓለም ሕይወቱ ነው፤ ትምህርትም ለምድር ዓለም ሕይወቱ ነው፡፡ ለውኃ ዋጋ አነሰው ይባላል፤ ለትምህርትም ሁልጊዜ ዋጋ ሲያንሰው ነው፡፡

ውኃ ከላይ ይወርዳል፤ ትምህርትም የሚመጣው ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፡፡

ውኃ እድፍን ያጠፋል፤ ትምህርትም ነውርን ያስወግዳል፡፡

ውኃ በጠብታ ተከማችቶ ትልቅ ወንዝ ይሆናል፤ ትምህርትም ጥቂት በጥቂት ተከማችቶ ሰፊ ዕውቀት ይሆናል፡፡

ውኃ በዝቅተኛ ቦታ ይሔዳል፤ ትምህርትም ትሕትና የሌለበትን ሰው አይጠጋውም፡፡

በትምህርቱ የሚኮራ ካደባባይ ላይ የወደቀ ጥንብን ይመስላል፤ ሰው ሲያልፍ አፍንጫውን ካልያዘ አይሆንለትም፡፡

ካንዲት ኢትዮጵያዊት የተጻፈ ‹‹ምክርና ምሳሌ›› (1947 ዓ.ም.)

******************

አካልም እንደ ቋንቋ

እጅ፣ ሥራን መደብ አድርጎ፤ ቃልን አፍን አንደበትን ኃይልን ሥልጣንን ወዘተ ያሳያል፡፡

እጅ ቃል መባሉም አፍ ሲናገር እጅም እንደ ምላስ እየሠራን የቃል አጋዥ ረዳት ከቃል ጋር የሥራ ተባባሪነት ያለው ከመሆኑም በላይ፤ የቃል ምትክ፤ የቃል ልዋጭ፤ ስለ ቃል ሆኖ የቃል ንግግርን ወክሎ (በምልክት) የሚገልጽ የሚያስረዳ በመሆኑ ነው፡፡

አፍ፤ መደቡ በከንፈርና በከንፈር መካከል ያለው ክፍት ኅዋ ሲሆን፤ ምላስ በሱ ውስጥ ስላለ ቋንቋ ይሆናል፡፡

የፈረንጅ (የፍሬንች) አፍ፣ የእንግሊዝ አፍ፣ የመስኮብ አፍ፤ … ይባላል፡፡ አፌን ይዤ ሲል ጠበቃዬን፣ ተከራካሪ የሚሆንልኝን ወኪሌን አስተርጓሚዬን፤ ማለቱ ነው፡፡

‹‹እንዲሁም፤ አፉን ሲያሾል፣ አፉን ሲያሞጠሙጥ፣ አፍ አፉን አሉት፤ ቀንድ ቀንዱን አሉት›› ዝም እክም ጭጭ አሰኙት ማለት እንደሆነ የተሰወረ አይደለም፡፡

ምላስ፤ የአፍ ውስጥ ኅዋስ፣ የመብል የነገር መሣሪያ ሲሆን ያለእርሱ መነጋገር ስለማይቻል፤ አንደበት፤ ቋንቋ፤ ልሳን፤ ይባላል፡፡ ያለእሱ መሣሪያነት ቃልና ቋንቋም ሊኖር አይችልም፡፡

መሸሻ ግዛው ‹‹አጋቶን›› (1963 ዓ.ም.)

 

ከጠብታ ማር

ለምሳሌ ልጅህ ሲጋራ እንዳያጨስ ብትፈልግ ስለ ሲጋራ መጥፎነት አትስበክለት፡፡ ሆኖም ሲጋራ ማጨስ የአንድ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋች እንዳይሆን ወይም በሩጫ ውድድር እንዲሸነፍ የሚያደርገው መሆኑን ንገረው፡፡

የሌላውን ፍላጎት የመጠበቅ ነገር ከማንኛውም ነገር ጋር ማለትም ከሕፃናት ወይም ከጥጃ ወይም ከዝንጀሮ ጋር በምናደርገው ግንኙነት ሁሉ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ራልፍ ዋልዶ ኤመርሰንና ልጁ አንድ ቀን አንድ ጥጃ ወደ ጋጥ ለማስገባት ሞከሩ፡፡ ሆኖም አብዛኛው ሰው የሚፈፅመውን ስህተት ፈፀሙ፡፡ እነሱ የሚፈልጉትን እንጂ ጥጃው የሚፈልገውን አላደረጉም፡፡ ኤመርሰን ከኋላ ወድሮ እምቢ አለ፡፡ ይህን ከንቱ ጥረቱ ታይ የነበረችው ሠራተኛ ጥጃው ምን እንደፈለገ ገባት፡፡ ጠጋ አለችና ጣቷን በዘዴ ለጥጃው አጎረሰችው፡፡ ጥጃው ጣቷን መጥባት ሲጀምር ቀስ ብላ ወደጋጡ እየተራመደች ይዛው ገባች፡፡ ሠራተኛው ምንም እንኳን ድርሰት የመፃፍ ችሎታ ባይኖራትም በዚያች ወቅት ከኤመርሰን የበለጠ ማስተዋል ችላ ነበር፡፡

ከተወለድክ ጀምሮ ያደረግካቸውን ለምሳሌ ለቀይ መስቀል ማኅበር 100 ብር የሰጠህበት ጊዜ ቢኖር እንኳን ሌላውን ከመውደድ የመነጨ በጎ ሥራ ለመሥራት ስለፈለግህ ነው፡፡ ከመርዳት ፍላጎትህ ይልቅ የብር ፍላጎትህ ቢያይልብህ መቶ ብሩን ባልሰጠህ ነበር፡፡ እርግጥ አስተዋጽኦው እንድታደርግ የጠየቀህ ሰው እምቢ የማትለው ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ እውነት አለ፡፡ ብሩን የሰጠኸው ምናልባት ከሰውየው አንድ የፈለግከው ነገር ስለነበረ ነው፡፡

  • ዴል ካርኒጌ፣ ‹‹ጠብታ ማር›› (1989)

*******

‹‹ለሰው ሞት አነሰው››- መንስኤ

በአንድ ወቅት ነብር መግደል የፈለጉ ሁለት ሰዎች ነበሩ፡፡ ነብሩም አይቷቸው ሲሮጥ በመንገዱ ላይ አንድ ገበሬ አገኘ፡፡

ገበሬውም እርሻውን እያረሰ እንዲህ እያለ ይዘፍን ነበር፤

“እኔ እያረስኩ ነው
ደመናዎቹን እያየሁ
ዝናብ የሚያመጡልኝን፡፡”

ነብሩም “የዘሩን ከረጢት አቀብለኝና ከአዳኞቹ አድነኝ እባክህ፡፡” ብሎ ገበሬውን ጠየቀው፡፡

ገበሬውም እሺ ብሎ ነብሩን የዘር መያዣው ውስጥ ደበቀው፡፡ ሁለቱም አዳኞች ገበሬው ጋ ሲደርሱ ቆም ብለው “አንድ ነብር አይተሃል” አሉት፡፡

ገበሬውም “አዎ በዚህ በኩል ሄዷል፡፡” አላቸው፡፡ አዳኞቹም ሩጫቸውን ቀጠሉ፡፡

በዚህ ጊዜ ገበሬው ነብሩን “ነብር ሆይ አዳኞቹ ስለሄዱ በል ሂድ፡፡” አለው፡፡

ነብሩ ግን “ወይ እገድልሃለሁ ወይም ምግብ አምጣልኝ፡፡” አለው፡፡

ገበሬውም “ለምን ስላዳንኩህ ነው የምትገድለኝ?” ብሎት “በል አህያዋ ጋ ሄደን ትዳኘን፡፡” አለው፡፡

አህያዋ ጋም ሄደው ገበሬው “እኔ ነኝ መበላት ያለብኝ?” ሲላት አህያዋም “አዎን፣ ለምን አትበላም?” አለችው፡፡

ከዚያም ወደ ቀበሮ ሄዶ ገበሬው “ይህንን ነብር ከሞት አዳንኩት፤ ሆኖም አሁን ሊበላኝ ይፈልጋል፡፡” አላት፡፡

ቀበሮዋም “እንዴት ነው የዳንከው” ስትለው ስለአዳኞቹና ነብሩ ስለተደበቀበት የዘር ክምር ነገራት፡፡

ከዚያም ቀበሮዋ “በል እንዴት እንደነበረ አሳየኝ፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን እንደገና ደበቀው፡፡

በዚህ ጊዜ ቀበሮዋ ገበሬውን “በል አሁን አጥብቀህ እሰረው፡፡” ስትለው ገበሬው ነብሩን ጥፍር አድርጎ ካሰረው በኋላ ቀበሮዋ “በል አሁን ደግሞ ደብድበው፡፡” አለችው፡፡

ገበሬውም ነብሩን ደብድቦ ገደለው፡፡

ከዚያም ገበሬው ቀበሮዋን “ከሞት አድነሽኛልና ምን ላድርግልሽ?” አላት፡፡

እርሷም “አንድ ጥሩ በግ አምጣልኝ፡፡” አለችው፡፡

ገበሬው ግን አንድ ትልቅ ውሻ ሲያመጣ ቀበሮዋ አይታ “ለሰው ሞት አነሳው፡፡” አለች ይባላል፡፡

  • ተራኪው የማይታወቅ የትግራይ ተረት (ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ)

 

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች