Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዓለምን ያሸበሩ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች

ዓለምን ያሸበሩ ተከታታይ የሽብር ጥቃቶች

ቀን:

እ.ኤ.አ. በ2015 ማብቂያ ኅዳር ወር ውስጥ በፈረንሣይ ከደረሰውና የ130 ሰዎች ሕይወት ካለፈበት የፓሪስ የሽብር ጥቃት ወዲህ፣ የብራሰልሱ ጥቃት ከፍተኛ ጥፋት የደረሰበት እንደሆነ ተዘግቧል፡፡ ከፓሪሱ የሽብር ጥቃት በኋላ በርካታ ጥቃቶች የደረሱ ቢሆንም፣ የብራሰልሱ ጥቃት በምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን የተለየ ሰፊ ሽፋን ከተሰጣቸው መካከል እንደሆነ አስተያየት ይሰጣል፡፡

የትኛው የሽብር ጥቃት በየትኛው መገናኛ ብዙኃን ምን ያህል ሽፋን አገኘ? የሚለው ከተለያየ አቅጣጫ የሚታይና የሚያነጋግር ሲሆን፣ ከፓሪሱ ጥቃት በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች በመቶ የሚቆጠሩ ጥቃቶች መፈጸማቸው ግን  ተዘግቧል፡፡ እንደ አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሊቢያና ሶሪያ ባሉ አገሮች ያሉ ግጭቶች ደግሞ ለበርካታዎቹ ጥቃቶች ምክንያት ሆነዋል፡፡

የካሊፎርኒያው በርናርዲኖ፣ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የደረሰው የአይቮሪኮስት ጥቃት በተወሰነ ሁኔታ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን አግኝተዋል፡፡ ከጥቂት ቀናት በፊት በኢራቅ ስታዲየም ለደረሰውና 25 ሰዎች ለሞቱበት ጥቃት አሸባሪው አይኤስ ኃላፊነት ወስዷል፡፡ ከ70  የሚበልጡ ለሕልፈት የተዳረጉበት የፓኪስታን ላሆር ከተማ ጥቃትም ከጥቂት ቀናት በፊት የተፈጸመ ነው፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሳያገኙ የቀሩ በርካታ ጥቃቶች ቢኖሩም፣ ባለፉት አራት ወራት ከደረሱ የሽብር ጥቃቶች የማሊው ባማኮ ራዲሰን ብሉ ሆቴል ጥቃት ይጠቀሳል፡፡ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸው ታጣቂዎች በፈጸሙት በዚህ ጥቃት 170 ሰዎች ታግተው የነበረ ሲሆን፣ 20 ሰዎች ተገድለዋል፡፡ የማሊ ኮማንዶ በመጨረሻ ሆቴሉን በመቆጣጠር ታጋቾቹን ያስለቀቀ ሲሆን፣ ሁለት ታጣቂዎችን ገድሏል፡፡ በተኩስ ልውውጡ ሌሎች ሰባት ሰዎችም ቆስለዋል፡፡ ይህ ጥቃት በደረሰበት ሳምንት በቱኒዚያ መዲና ቱኒዝ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂዎች መኪና ላይ የአጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ደርሷል፡፡ አጥፍቶ ጠፊው ለ13 ሰዎች መሞት ምክንያት ሲሆን፣ ጥቃቱም እ.ኤ.አ. በ2016 ቱኒዚያ ውስጥ በአይኤስ ከደረሱ ሦስት ጉልህ ጥቃቶች መካከል ነው፡፡  ከፓሪሱ ጥቃት ቀጥሎ መጀመርያ ደረጃ የሚጠቀሰው የካሊፎርኒያው ናን በርናርዲኖ ጥቃት በባልና ሚስት የተፈጸመ ነው፡፡ ባልና ሚስት በፈጸሙት ጥቃት 14 ሰዎች ሲሞቱ 22 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል፡፡ ከፖሊስ ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥም ባልና ሚስቱ ሰይድ ሪዝዋን ፋሩክና ታሽፈን ማሊክ ተገድለዋል፡፡ ኤፍቢአይ እንዳለው የጥቃት ፈጻሚዎቹ በአይኤስ የተነሳሱ ቢሆኑም፣ ጥቃቱን ሙሉ በሙሉ የፈጸሙት በራሳቸው ነው፡፡

በቱርክ ኢስታንቡል አደባባይ ላይ በደረሰ የሽብር ጥቃት 13 ሰዎች ሲሞቱ 14 ቆስለዋል፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች በሙሉ የውጭ አገር ዜጎች ነበሩ፡፡ የጥቃቱ ፈጻሚ ደግሞ የአይኤስ ተከታይ የሆነ ናቢል ፋዲ የተባለ ሶሪያዊ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ በአውሮፓውያን አዲስ ዓመት (2016) የመጀመርያ ወር አጋማሽ በኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ጃካርታ  በተፈጸሙ ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች፣ አራት ጥቃት ፈጻሚዎችን ጨምሮ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ሌሎች 24  ደግሞ ቆስለዋል፡፡ አይኤስ ኃላፊነቱን በወሰደበት በዚህ ጥቃት ምንም እንኳ አሥር እንደሚሆኑ ቢገመትም ምን ያህል አሸባሪዎች እንደተሳተፉ በትክክል  አይታወቅም፡፡ 

ሰላሳ ሰዎች የተገደሉበትና 56 ሰዎች የቆሰሉበት የቡርኪና ፋሶ ኦጋዱጉ   በተመሳሳይ ጊዜ የተፈጸመው ጥቃትም በቅርብ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ትኩረት የተሰጠው ነው፡፡ በጥቃቱ 170 ሰዎች ታግተው ስለነበር የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጥቃቱ የተፈጸመበትን ሆቴል በመቆጣጠር ታጋቾቹን ለማስለቀቅ ተገድደው ነበር፡፡ አራት ጥቃት ፈጻሚዎች ሲገደሉ ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ማምለጣቸውም ተገልጿል፡፡

ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚኖርበትና ሠራተኞች ከሥራ በሚወጡበት ሰዓት በቱርክ አንካራ ከተማ የኩርድ የነፃነት ታጋዮች በሚባሉት ጥቃት የተፈጸመው ደግሞ ባለፈው ወር ነበር፡፡ በዚህ ጥቃት 29 ሰዎች ሲገደሉ 60 የሚሆኑት ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ዒላማ ያደረገ ሲሆን፣ አንድ ጥቃቱን ፈጻሚ ሕይወቱ አልፏል፡፡ በሞቃዲሾ ኤስዋይኤል ሆቴል ላይ ከአልሸባብ ጋር ግንኙነት ባላቸው ታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት 16 ሰዎች ሲሞቱ 12 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ አራት ታጣቂዎች የሆቴሉን በር በኃይል ጥሰው በመግባት ከሆቴሉ የፀጥታ ሠራተኞች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ከዚያም የሆቴሉን የመጨረሻ የደኅንነት በር ሳያልፉ አራቱም ተገድለዋል፡፡

በዚህ ወር መጀመርያ  በአይቮሪኮስት ግራንድ ባሳም መዝናኛ ላይ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ባለው ቡድን በተፈጸመ ጥቃት 18 ሰዎች ሲሞቱ 33 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ከሟቾች 16ቱ ሲቪል ሲሆኑ ሦስቱ የመንግሥት ታጣቂዎች ነበሩ፡፡ ጥቃቱ የደረሰበት ይህ ሆቴል በዳያስፖራዎች የሚዘወተር ሲሆን፣ ከጥቃት ፈጻሚዎቹ ሦስቱ ሲገደሉ ከሦስት የሚበልጡ ማምለጣቸው ተዘግቧል፡፡

በተመሳሳይ ጊዜ በተፈጸመው የአንካራው ሁለተኛ ጥቃት 37 ሰዎች ሲሞቱ 127 ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ልክ እንደ መጀመርያው ጥቃት ለዚህኛውም ጥቃት ኃላፊነት የወሰደው የኩርዲስታን ነፃነት ታጋዮች ቡድን ሰላማዊ ዜጎች ዒላማዬ አይደሉም ቢልም፣ የሕዝብ ትራንስፖርት ማዕከል ላይ ባደረሰው በዚህ የሽብር ጥቃት ሰለባ የሆኑት ብዙዎቹ ንፁኃን ዜጎች ናቸው፡፡ እዚያው ቱርክ ኢስታንቡል ውስጥ ከጥቂት ቀናት በፊት በአጥፍቶ ጠፊዎች በደረሰ ጥቃት ቢያንስ አራት ሰዎች ሞተዋል፡፡ እዚያው በገበያ ማዕከል በተሰነዘረ ጥቃትም 36 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በዚህ ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የውጭ አገር ዜጋ ቱሪስቶች ነበሩ፡፡ ለዚህ ጥቃት ግን ኃላፊነቱን የወሰደ ምንም ዓይነት ቡድን የለም፡፡

እንዲህ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ገጽታቸውን እየቀያየሩ እየተፈጸሙ ያሉት የሽብር ጥቃቶች የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ከፍተኛ ጭንቀት ከመሆን ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ በተለይም ደግሞ አውሮፓ የእንደዚህ ዓይነቱ የሽብር ጥቃት ቀዳሚ ዒላማ እየሆነች ነው በማለት፣ ከፍተኛ የቁጥጥርና የመከላከል ዕርምጃ እንዲወሰድ የዓለም መሪዎች እያሳሰቡ ነው፡፡ እንዳሁኑ ጥቃት በአውሮፓ ባልተደጋገመበት ጊዜ ምንም እንኳ ብሔርተኝነትን መሠረት አድርገው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ይደርስ በነበረ ጥቃት ሰለባ የሚሆኑ የነበሩ ቢሆንም፣ ዛሬ ግን ጥቃት በምንም ሁኔታ ለአውሮፓ እንግዳ አልሆነም፡፡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ 500 የሚሆኑ ሰዎች በሽብር ጥቃት አውሮፓ ውስጥ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በአውሮፓ እየደረሱ ባሉ ጥቃቶች ዒላማ እየሆኑ ያሉት የሕዝብ ትራንስፖርቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶች ናቸው፡፡

በመገናኛ ብዙኃን በተለይም ተፅዕኖአቸው ከባድ በሆነው የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ትኩረት የሚሰጣቸው በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ የደረሱ ጥቃቶች በመሆናቸው፣ በዚህ ጊዜ ይህን ያህል ሰዎች በአውሮፓ በሽብር ጥቃት ሕይወታቸውን አጡ ይባል እንጂ፣ በመካለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ በደረሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ከአውሮፓ ወይም ከአሜሪካ ጥቃት ሰለባዎች ጋር የማይነፃፀር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ብዙዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

የትኞቹ ጥቃቶች ትኩረት ሲያገኙ የትኞቹ እንዲሁ ታለፉ? የሚለው ጥያቄ ሆኖ፣ የሽብር ጥቃት በአውሮፓ መደጋገም የኃያላን አገሮች መሪዎችን ከመቼውም በላይ የትም ይሁን የት ስለሚፈጸሙ ጥቃቶች እንዲጨነቁ ግድ ያላቸው ይመስላል፡፡ ‹‹ሽብርተኞች ብራሰልስ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፡፡ ዒላማ ያደረጉት ግን አውሮፓን ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ዓለም ሁሉ ይጨነቃል፤›› ብለዋል የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦላንድ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ የአይኤስ አጋር በሆነ ቡድን ብራሰልስ ውስጥ በአውሮፕላን ማረፊያና በምድር ውስጥ የባቡር ጣቢያ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 31 ሰዎች ሲሞቱ ከ300 በላይ ተጎድተዋል፡፡ ይህም በስፋት በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ