Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -

  ከእህል በረንዳ የተነሳው ኢንቨስትመንት

  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሬውንም ሆነ የውጭ ቱሪስቶችን ቀልብ በመግዛት ከአገሪቱ ከተሞች ውስጥ የደቡብ መናገሻዋ ሐዋሳ ትጠቀሳለች፡፡ ከተቆረቆረች ከአምስት አሠርታት በላይ ያስቆጠረችው ሐዋሳ፣ ፈጣን ዕድገቷና ውበቷ ዓይነተኛ ሚና ከሚጫወቱት መሠረተ ልማቶቿ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁት ሆቴሎቿና ሪዞርቶቿ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡ በዚህ ረገድ በቅርቡ በተደረገው የሆቴሎች የደረጃ ልኬት ሁለት ሆቴሎችና ሁለት ሪዞርቶች የአራት ኮከብ ደረጃን እንዲያገኙ ሆኗል፡፡ ከነዚህ ውስጥ በ16 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈውና በ2005 ዓ.ም. ግንባታው ተጠናቆ በመስከረም 2006 ዓ.ም. ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ሳውዝ ስታር ኢንተርናሽናል ሆቴል ይጠቀሳል፡፡ ሆቴሉ የተለያየ መጠን ያላቸው ክፍሎች ሲኖሩት፣ ክፍሎቹም በአገሪቱ ጥንታዊ፣ ታሪካዊና የቱሪስት መስህብ በሆኑ መዳረሻዎች ጣና፣ አክሱምና ኤርታሌ የሚሉት ስያሜዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ስቲም፣ ሳውና ባዝ፣ ጃኩዚ፣ የውኃ ዋና ገንዳ፣ ለሆቴሉ አገልግሎት ብቻ የሚውል ሱፐር ማርኬትና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የሆቴል ግብዓቶችን አሟልቶ የያዘ መሆኑም ይነገርለታል፡፡ ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት የሚነገርለት ሆቴል በአሁኑ ወቅት 216 ሠራተኞችን ያስተዳድራል፡፡ ሆቴሉ ለተጨማሪ ማስፋፊያ ከከተማው አስተዳደር መሬት ተረክቦ ቀጣይ ማስፋፊያዎችን እያከናወነ ነው፡፡ በሆቴሉ እንቅስቃሴና በተለይ ደግሞ በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ ከተከናወነው የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ ዙሪያ አቶ ያሬድ ፈይሳን ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

  ሪፖርተር፡- ከእህል ንግድ አስመጪና ላኪ ከዚያም በሐዋሳ ከተማ በሆቴል ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ሆቴሉ ሥራ ከጀመረ ሁለት ዓመት አልፎታል፡፡ በአጠቃላይ ሒደቱን እንዴት ይገልጹታል?

  አቶ ያሬድ፡- ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት የሆቴል ኢንዱስትሪ ቀላል ሳይሆን እጅግ ብዙ ውጣ ውረዶችን የሚጠይቅ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ነው፡፡ በዚህ ኢንዱስትሪ አንዱና ብቸኛው በርካታ ሰዎች ከአገር ውስጥም ይሁን ከአገር ውጭ መጥተው ተዝናንተው ሲወጡ መመልከቱ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ወደ እዚህ የሆቴል ኢንቨስትመንት ከመምጣቴ አስቀድሞ ብዙዎች እንደሚያውቁት ተወልጄ ባደግኩበት አዲስ አበባ የእህል ንግድ ከመጀመሬ በፊት ቢዝነስን አንድ ብዬ የጀመርኩት ከታች ከወዛደርነት ተነስቼ ነው፡፡ በዚህ የተጀመረው የንግድ እንቅስቃሴ ከረዥም ጊዜ እልህ አስጨራሽ ጥረት በኋላ ወደ አስመጪና ላኪነት ደርሼ ለዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከሳውዝ ስታር በተጨማሪ በአዲስ አበባ በተለያየ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በመሰማራት የተለያዩ ድርጅቶችም አሉኝ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆቴሉ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ምን ምን ናቸው?

  አቶ ያሬድ፡- ሳውዝ ስታር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊያሟላቸው የሚገቡ ነገሮችን አሟልቶ የያዘ ነው፡፡ ስቲም፣ ሳውና ባዝ፣ ጃኩዚ፣ የውኃ ዋና በርከት ያሉ ባሮች፣ ኬክ ቤቶችና ከራሱ የገበያ ማዕከል (ሱፐር ማርኬት) ጀምሮ የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾችና ሌሎችንም አገልግሎቶች ይሰጣል፡፡ ሰዎች ባላቸው አቅም ልክ ተገቢውን አገልግሎት አግኝተው የሚመለሱበት ሆቴል ነው፡፡ ከትልልቅ መንግሥታዊ ተቋማት አንስቶ እስከ ዓለም አቀፍ የዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ድረስ ይገለገሉበታል፡፡ 

  ሪፖርተር፡- በቅርቡ ለሆቴሎች ደረጃ ተሰጥቷል፡፡ በሐዋሳ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ሪዞርቶችን ጨምሮ በርካታ ሆቴሎች ቢኖሩም ሳውዝ ስታርን ጨምሮ አራት ሆቴሎች ብቻ የአራት ኮከብ ደረጃ ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡ የደረጃ አሰጣጡን ሒደት አስመልክቶ የእርስዎና የሆቴልዎ አቋም ምንድነው?

  አቶ ያሬድ፡- የደረጃ አሰጣጡ በአዲስ አበባም ሆነ በሐዋሳ የተሰጠው የሆቴል ደረጃ እውነቱን ለመናገር ከሆነ ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉት፡፡ ይህንኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በሚገኙበት ተናግሬያለሁ፡፡ እንደ ሐዋሳ ሳውዝ ስታር ባለቤትነቴ የተሰጠውን ደረጃ እቀበላለሁ፡፡ ነገር ግን አራት ኮከብ የተሰጣቸው ሆቴሎች ሁሉም ይመጥናሉ ወይ? የሚለው ግን ያሳስበኛል፡፡ ሳውዝ ስታርን ለየት የሚያደርገው ከምለው ውስጥ ሕንፃው የመሬት መንቀጥቀጥና የመሳሰሉትን ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋዎችን እንዲቋቋም ተደርጎ የተገነባ ነው፡፡  በሆቴላችን ውስጥ የሚሰጡ አገልግሎቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በግሌ በዘርፉ የሚገኙ ባለመያተኞችን ስለማምን ከግንዛቤው ጀምሮ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ነው የተደረገው፡፡ ሌላ የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የተወሰኑ ሕንፃዎች ግንባታ ናሙና (ሳምፕል) በመመልከት ለሳውዝ ስታር አዋርድ ሰጥተዋል፡፡ ለዚህ የበቃው ደግሞ አንድ ሕንፃ ከግንባታ ይዘቱ ጀምሮ በራሳቸው መስፈርት መሠረት ከለኩ በኋላ ነው፡፡

  ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ካለው ተሞክሮ ብዙ ጊዜ ከሆቴል ሕንፃ ግንባታ ጀምሮ በተለይ ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋዎችን ታሳቢ አድርጎ ግንባታው ሲገነባ አይስተዋልም፡፡ ከዚህ አኳያ ሳውዝ ስታር እነዚህን ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን አሟልቶ እንዲጠናቀቅ ስታቅዱ መነሻችሁ ምን ነበር?

  አቶ ያሬድ፡- እነዚህን የመሰሉ ግንባታዎች አቅምን እንደሚፈታተኑ ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እኔም ተፈትኘበታለሁ፡፡ ያም ሆኖ ግን የዘርፉ ሙያተኞች ለዚህ ጉዳይ ቅርበቱም ዕውቀቱም ስላላቸው እነሱ የሚደርሱበትን ሙያዊ ድምዳሜ መቀበል ግድ ስለሚል መሆንም ስላበት የሆነ ክንውን ነው፡፡ ከዲዛይን እስከ ግንባታው በሙያተኛው ውሳኔ የተከናወነ ግንባታ ነው፡፡ ሳውዝ ስታር ሁለተኛውን የማስፋፊያ ግንባታም እያከናወነ ነው፡፡ ይህም ቢሆን አሁን ካለው በተሻለ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች የሚከናወኑበት ከስብሰባ አዳራሾች ጀምሮ ዓለም አቀፍ የመዋኛ ገንዳ (ስዊሚንግ፣ ፑል)፣ እንዲሁም የክፍሎቹ መጠንና ግልጋሎትም ቢሆን እንደየ ደረጃቸው የተከፋፈሉ ሲሆን፣ የቤተሰብ ኤክስኩቲቭ፣ በተጨማሪም ሦስት የምግብ ቤቶች፣ ሦስት ባርና ሁለት ካፌዎችን አካቶ የያዘ ነው፡፡  

  ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

  አቶ ያሬድ፡- ኢንዱስትሪው በአገሪቱ መስፋፋት ደረጃ የጀመረው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቢሆንም ይኼ ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ በርካታ የሚጎሉ ነገሮች አሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙዎቻችን ወደ ሆቴል ኢንዱስትሪ ስንገባ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ተለያዩ አገሮች ስንሄድ ከምንመለከተው ተነስተን የምንገባበት ነው፡፡ ምናልባትም ይኼ አካሄድ ወደፊት ኢንዱስትሪው እየተስፋፋ በሄደ መጠን ሙያተኞችን በበቂ ደረጃ ከማግኘት ጀምሮ ችግር መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ አሁንም በአንዳንድ ትልልቅ ደረጃ ካላቸው ሆቴሎች ጀምሮ የሙያተኞች ጉዳይ ሲያስቸግር እየተስተዋለ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ የሚጎሉ ነገሮች አሉ፡፡

  ሪፖርተር፡- ሆቴሉን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ማን ነው?

  አቶ ያሬድ፡- እኔና ባለቤቴ፡፡

  ሪፖርተር፡- ከእርስዎ ጀርባ የመንግሥት ባለሥልጣናት በባለቤትነት እንዳሉበት የሚናገሩ አሉ?

  አቶ ያሬድ፡- እዚህ አገር ብዙ ጊዜ የማንነት ጥያቄ በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡ መነሻውና መሠረቱ አይታወቅም፡፡ ይህንን እኔ ራሴ ሰምቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን ከቁብ ስለማልቆጥረው ቦታ አልሰጠውም፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት የሳውዝ ስታር ባለቤቶች እኔና ባለቤቴ ብቻ ነን፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ሆቴሉ ሲመሠረት የራሱ መመሥረቻ ደንቦች አሉት፡፡ መመልከት ይቻላል፡፡ ከአዲስ አበባ እህል በረንዳ ጀምሮ የእኔን ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁ አሉ፡፡ እነሱን ሳይቀር ጠይቆ እውነታውን መረዳት ይቻላል፡፡ መንግሥትም ቢሆን ሳውዝ ዝታር የያሬድ ቶሎሳና የባለቤቱ መሆኑን ያውቃል፡፡ ከየት ተነስቼ እዚህ እንደደረስኩ መረጃዎች አሉ፡፡ መመልከትና መረዳት ይቻላል፡፡

  ሪፖርተር፡- የወሬው መነሻ ምንድነው ብለው ያስባሉ?

  አቶ ያሬድ፡- የወሬ መነሻ ወሬ ካልሆነ በእኔ በኩል እንዲህና እንዲያ የምለው የለኝም፡፡ ቀደም ሲል ለመናገር እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት በሳውዝ ስታር ሥር 216 ያህል ሠራተኞች አሉት፡፡ ከዚህ በላይ ሠራተኞች እንዲኖሩኝ ነው የእኔ ፍላጎት፡፡ ምክንያቱም በዚህ ምድር ለሰው ልጅ ለብቻው የተሰጠው ምንም ነገር የለም፡፡ እኔም የዚህ አንድ አካል በመሆኔና በረከቱም ከፈጣሪ ስለሆነ ለሕዝቡ እያበረከትኩ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ድርጅቶቼ ጭምር በአጠቃላይ ከ400 በላይ ሠራተኞች አሉኝ፡፡ እነዚህ ሰዎች በእኔ ሥር እግዚአብሔር ፈቅዶ እስካስተዳደርኳቸው ድረስ ትልቁ ደስታዬ ይሄ ነው፡፡ ለወደፊቱም ከዚህ የተለየ ስሜት ይኖረኛል ብዬ አላስብም፡፡ ስለሆነም ነው ለወሬ ጊዜና ቦታ የማልሰጠው፣ ሲቆም ይቆማል፡፡ የሚገርመው አንዳንድ ሰዎች በአካል እኔ እየመጡ ነገሩ ምንድነው? የሚሉኝ ገጥመውኛል፡፡ በእኔ ሰዎች ጥሩ ነገር ተሠርቶ እስከተመለከቱ ድረስ ያንን ከማበረታታት ይልቅ ለወሬና ለአሉባልታ ጊዜ ለምን እንደሚሰጡ አይገባኝም፡፡

  ሪፖርተር፡- ተፅዕኖ ፈጥሮቦታል?

  አቶ ያሬድ፡- በፍፁም፡፡ እንደዚያማ ቢሆን ኖሮ እዚህ ባልደረስኩ፡፡ በአገሪቱ ከሥራ ይልቅ የወሬ ልምድ እየተስፋፋ መምጣቱ ያስገርመኛል፡፡ የተማሩና የተመራመሩ ሳይቀር በእንደዚህ የመሰለ ወሬ የተጠመዱ ሞልተዋል፡፡ በግሌ ያሳፍረኛል፡፡ የሚገርመው በአገራችን ስላልተለመደ ነው እንጂ በብዙ አገሮች በጣም በትንሽ ገንዘብ ተነስተው ትልቅ ደረጃ የሚደርሱ ሰዎች አሉ፡፡ ቅንነት፣ መተሳሰብና ሰዎች የሚሠሯቸው ማናቸውም ነገሮች የእኔ ናቸው ብሎ የሚያስብ ትውልድ ያስፈልገናል፡፡ በግሌ በዚህ ረገድ ከአገሪቱ ከመንገድ ጀምሮ የሚከናወኑ ማናቸውም ነገሮች የእኔ አድርጌ ነው የምወስዳቸው፡፡ ሁሌ ‹‹ደሃና ረሃብተኞች›› ተብለን መቆየትን ለምን ብለን ማሸነፍ የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን በማውራት ብቻ ምንም ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡

   

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

  የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  የአገር ውስጥ የፍራፍሬ ገበያን ፍላጎት ይሸፍናል የተባለለት የብላቴው እርሻ ልማት

  መንግሥት የግብርና ምርታማነትና የፍራፍሬ ምርትን ለማሳደግ በ‹‹አረንጓዴ አሻራ›› በሚል...

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ‹‹የንባብ አብዮት ለትውልድ ብለን ተነስተናል›› አቶ ሰለሞን ደርቤ፣  የሕያው ፍቅር ለኢትዮጵያ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ

  ሕፃናት በለጋ ዕድሜያቸው አዕምሯቸው እንዲዳብር ማንበብ ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡ ዜጎች ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ሥልት፣ ዘዴና ችሎታ እንዲኖራቸው ማንበብ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ ይነገራል፡፡ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በኢኮኖሚያዊ...

  የቤት ፍላጎትንና አቅርቦትን ለማጣጣም የተነሳው ተቋም

  በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤት እጥረት የተነሳ በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ሲፈተኑ ይታያል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቅሙ ኖሯቸው መኖሪያ ቤት ለመሥራት...

  የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት የመቀየር ጉዞ

  ብርሃን ለሕፃናት የማኅበረሰብ ተሃድሶ መርህን መሠረት በማድረግ፣ በዋናነትም አካል ጉዳተኛና ሌሎች ለችግር የተጋለጡ ሕፃናትን ለማገዝ ከ25 ዓመታት በፊት በጥቂት በጎ ፈቃደኞች የተመሠረተ ድርጅት ነው፡፡...