Tuesday, March 5, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የባዶ ሆድ ወግ

እነሆ መንገድ። ከጦር ኃይሎች – ዘነበወርቅ – አየር ጤና ባኮበኮበ ታክሲ ተሳፍረናል። ረፋድና ቀትር ሰዓት ታይቶ በሚለይበት የእሳት ዘመን፣ የእጆቿን መዳፎች በእንሶስላ ያጠቆረች የቤት እመቤት የጋቢናውን በር በርግዳ ከፈተችው። በሩን እንደ መከዳ በክርኑ ተደግፎ በሐሳብ ሰምጦ የተቀመጠው ጎልማሳ ቀልቡ ተገፈፈ። ‹‹በሞትኩት እኔ ልደንግጥልህ? አስደነገጥኩህ?›› እመቤቲቱ በመንሰፍሰፍ አየችው። ‹‹ኧረ ግድ የለም። ወንድ ልጅ ድጋፉን ሲነጥቁት ከደነገጠማ ይህቺ አገር ምኑን የወንድ አገር ሆነችው?›› አላት። ‹‹የጀግና አገር ለማለት ነው የወንድ ያልከው? ከነገሥታት እስከ ተራዎቹ በአርበኝነት ስማችንን ያስጠራን ሴቶችም እኮ አገራችን እዚሁ ነው፤›› በማለት እመቤቲቱ ርህራሄዋ ወደ ማጥቃት ተሸጋገረ። ‹‹ልክ ነሽ! ልክ ነሽ! እንደሱ ማለቴ ሳይሆን አየሽ . . . እ እ . . . እንዴት ልበልሽ ያው ዘመኑ እንደምታውቂው ነው። የዓለም ፖለቲካና ታሪክስ ከኢኮኖሚና ከግዛት ወደ ማስደንገጥና ማሸበር የተሸጋገረበት ዘመን ነው። አባባሌ . . .›› እያለ ሊቀጥል ሲል ተሳፋሪዎቹን አራግፎ ሾፌሩን ሰላም ሊል አንድ ወያላ አሰገገ።

‹‹ወይ ጉድ ተመችቶህ የለ እንዴ? አንተ ምን አለብህ፤›› አለው ሰላምታውን ትቶ። ለነገሩ ሰማያዊውን ሰላምታ ለዓለማዊ ድሎትና ጉስቁልና ያልቀየረው አሳፋሪም ተሳፋሪም የለም። ‹‹ምን ይመቸኛል? እዚህ ‘ቪአይፒ’ የሚቀመጡ ሰዎች እኮ ፍልስፍናቸው ሥራ አላሠራን አለ?›› እያለ ሾፌሩ ወደ ጎልማሳው አመለከተው። ‹‹እሱን ፍራ ወንድሜ። ዘንድሮ ከቢሮክራሲ ቀጥሎ ገዥና ተገዥን አላስማማ ያለው እኮ ዘንድሮ አጓጉል አዛምደው ሊያስረዱን ያልቻሉት አብዮትና ዴሞክራሲ ናቸው። ታዲያ ምን ቸገረህ? የባጥ የቆጡን ሲዘባርቅ አንተ ከሥር ግባለትና ዘመኑ የቻፓ እንጂ የፊሎዞፊ እንዳልሆነ አስተምረው። ሾፌር አስተማሪ መሆን አይችልም ያለው ማን ነው?›› እያለ ተሰናበትነው። ይኼኔ ከጎኔ የተቀመጠች ቀዘባ፣ ‹‹እንዲህ ወሬና ትችት ላይ አንደኛ ሆነን ተግባሩ ያቃተን ለምድነው?›› ትለኛለች። ሲባል ሰምቶ እንደ ማውራት መኖር ይቀል መስሏት!

‹‹ሳበው›› ብሎ ወያላው በሩን ዘጋ። ‹‹ይኼው አሥር ዓመት ብስበው ብስበው የበጠስኩት ሁሉ ከጥገና፣ ከቤት ኪራይና ከአንተ ደመወዝ መቼ አለፈ?›› ሾፌራችን ወያላውን ገልመጥ አደረገው። ‹‹በል እኔን አትጨምረኝ። ተደራጅ ስትባል ያመነታኸው አንተው ነህ፤›› ወያላው ሳያስበው ነገር ቆሰቆሰ። ጎልማሳው ‹‹የታክሲውን ወለል ኮብልስቶን ልታነጥፉበት ነው ተደራጁ የሚሏችሁ?›› ሲል አንዳንዱ በግርምት አንዳንዱ በስላቅ ፈገግ አለ። ‹‹እኔ ምን አውቃለሁ? የዚህ ዓለም ሕግ ሀብታሞቹን ትቶ ድሆች ላይ ለምን እንደሚበረታ አላውቅም፤›› ብሎ ትከሻውን ሰበቀ። ባለእንሶስላዋ እመቤት፣ ‹‹ያለው እንኳን ከሰው መቼ ከራሱ ይስማማል ብለህ ነው? ፍቅር አጥቼ ከምከብር እኔስ ድህነቴን እመርጣለሁ፤›› ስትል ማንም ሳይጠይቃት ኑሮዋን ተረከች።

‹‹የለም! የለም! አሁን እኮ የምንጫወተው ስለመደራጀት ነው። ስሚ እንጂ እውን እያደራጀን ያለው ፍቅር ነው ፖለቲካ?›› ጎልማሳው በመልሶ ማጥቃት ስልት አፋጠጣት። መሀል መቀመጫ ላይ የተቀመጠች ወይዘሮ ወገቧ ድረስ ወርዶ ባሽሞነሞናት ነጠላዋ ሥር በእጆችዋ የሆነ ነገር እየሠራች፣ ‹‹መደራጀት ፖለቲካዊ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው?›› ብላ ዙሪያ ገባዋን ስትቃኝ፣ ‹‹ከባቢሎን ግንብ ጀምሮ፤›› ብሎ አጠገቧ የተሰየመ አተኳሪ ወጣት መለሰላት። ‹‹ኧረ ጎበዝ አሁን እኮ ያለው 21ኛው ‘ሴንቸሪ’ ላይ ነው፤›› አላቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተቀደደ ባርኔጣ የደፋ ተቅበዝባዥ ወጣት። ‹‹ያው ነው! የእኛንም የባቢሎናውያንንም ቋንቋ እያደበላለቀ ያለው ‘መደራጀት’ ነው፤›› ሲል፣ ‹‹የልማት እንጂ የጥፋት ግንብ ገንቡ ያለን አለ እንዴ?›› ብላ ቀዘቢት አየችኝ። በባቢሎናውያንን መዝገበ ቃላት ነገር የሚተረጉም ባልታረመበት በዚህ ጎዳና፣ ስንቱ በጎ አሳቢ ነገን አሳቢ ራዕይ ባክኖ ቀርቶ ይሆን?

ከፌርማታ ፌርማታ እየዘለልን ከጨዋታ ጨዋታ ሲከተል ግማሽ መንገድ ተጉዘናል። በዚህ መሀል መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ ወጣት ጓደኛማቾች አንዱ፣ ‹‹እስኪ አሁን ለሰውዬው ደውል፤›› ይላል። ‹‹አሁንማ አልደውልም ምሳ ሰዓት እየደረሰ ነው፤›› ይላል ወዳጁ ኮስተር ብሎ። ‹‹እና? ምሳ ሰዓት ቢደርስ ብራችንን መቀበል አንችልም?›› ይላል መልሶ ያኛው። አንዳች ነገር የከበዳቸው አልያም የጨነቃቸው ናቸው። ‹‹እሱ አይደለም ‘ፖይንቱ።’ አየህ ብንደውል ገንዘቡን አሁኑኑ አይሰጠንም። እንዲያውም ነጥብ መጣል ነው፤›› ሊያግባባ ይሞክራል ያኛው። ‹‹እኛ ከሀብታም ጋር የሊግ ውድድር አልጀመርን። ደልለናል ኮሚሽናችንን ይስጠን በቃ። ምንድነው አንተ እንደዚህ…?›› እያለ ነገር ሊያዞርበት ሲል ምሳ ሰዓት ይለፍ ባዩ፣ ‹‹አልገባህም አሁን ብንደውል በእርግጠኝነት የሚለን ምሳ ልብላ፣ እናንተም ምሳ ብሉና ከሰዓት በኋላ ኑ ነው፤›› አለው።

‹‹እና ይኼ ምንድነው ነጥብ የሚያስጥለው?›› ወዳጁ ግራ ተጋብቶ ሲጠይቅ ተሳፋሪዎችም አብረውት ግራ ተጋብተው የሚለውን ለመስማት ወደ መላሹ ዞሩ። ምክንያቱን በሰው ፊት ለመናገር ሲፈራ ሲቸር ከቆየ በኋላ፣ ‹‹በምናችን ነው እኛ ምሳ የምንበላው? ገንዘብ እኮ የለንም። ምን ነክቶሃል አንተ ሰው? እሱ እስኪበላ እኛ ሳንበላ መጠበቃችን ላይቀር ለምን ሞራላችንን መጫወቻ እናድርገው? አይገባህም እንዴ?›› ብሎ ዕቅጩን ነገረው። ‹‹አሃ ነጥብ መጣል ያልከው ይኼን ኑሯላ? እኔ ደግሞ ቁማር ገብታችሁ መስሎኝ ልጠቁማችሁ ነበር፤›› ብለው ከጎናቸው የተቀመጡ አዛውንት ጠቀሱት። ‹‹ሆድ ከማስጮህ የባለፀጋ ለበጣ ሌላ ምን የሞራል ነጥብ የሚያስጥል ነገር አለ?›› እያሉ ጓደኛማቾቹ ተስማምተው ሲያበቁ የጥቅሻ ብድራቸውን መለሱ። ፖለቲካ የሌለበት ቢመስልም የባዶ ሆድ ወግ በነጥብ ሲሰላ ለሚያይ ፓርላማ እስኪገባ ሆዱን ይቆርጠዋል!

ጉዟችን ቀጥሏል። ዘነበወርቅ ላይ ከመድረክ እንደሚሰናበት ዝነኛ ተዋናይ እንደ ፀሐይ ግርዶሽ መዳፎቿን በእንሶስላ ያሽሞነሞነችው እመቤት እጆቿን አውለብልባ ተሰናበተችን። በምትኳ ኋላ እንደታዘብነው ሙግትና ኑሮ ያደቀቃቸው ጠና ጠና ያሉ እህትማማቾች ተተኩ። ወያላው እያጠጋጋ ቦታ ሰጣቸው። ‹‹አንችዬ አሁን ይኼ ኑሮ ኑሮ ነው?›› ትላታለች ጠየም የምትለው። ‹‹ተይኝ! አገር የምናስለቅቅ ይመስል አሥር ዓመት ሙሉ ተመላለስን፤›› ትቃትታለች በጉምጉምታ። አዛውንቱ ቅርብ ናቸውና ጠየቁ። ‹‹ምን ለማስለቀቅ ነው አሥር ዓመት ልጄ?›› ሲሉ፣ ‹‹አንድ የአያቶቻችን ይዞታ የነበረ ቦታ ነበረን እዚህ ልደታ አካባቢ…›› መለሱ በትብብር። ‹‹ዕጣህን አመስግን ወንድሜ። አንዱ ይኼው እንደምታየው ለአንድ ይዞታ አሥር ዓመት ይሟገታል። ገሚሱ በአሥር ዓመት ይኼው አዲስ አበባችንን የደረቀ ቅጠሏን አራግፎ በአዲስ እየተካ አገር ያሳድጋል። ሌላው ደግሞ ቦታ ተመርቶ አጥር አጥሮ ሳይገነባ ሕዝብና መንግሥትን ግራ ያጋባል፤›› የምትለኝ ያው ያቺው ዘማማ ነች።

ይኼኔ ‹‹ወራጅ›› ብላ ጮኸች ከእህትማማቾቹ አንዷ። ‹‹ቆይ ቦታ ይያዝ›› ብሎ ወያላው ተረጋግቶ መለሰ። ‹‹ወራጅ አልኩህ ወራጅ!›› ጮኸች በድጋሚ። ‹‹እንዴ አደባባይ ላይ እንዴት ላውርድሽ?›› ወያላው ግራ ሲጋባ፣ ‹‹ምነው ጃንሆይን በአደባባይ አውርዳን መስሎኝ? ምን ሆንን ዛሬ? አውርደኝ ብዬሃለሁ አውርደኝ፤›› እያለች ስትግል ሾፌሩ ትዕግሥቱ አልቆ መሳደብ ጀመረ። ተው ሲባል ብሶበት ጭራሽ ታክሲዋን መሀል አደባባይ አቁሞ፣ ‹‹ዱላ ካማረሽ ውረጂ›› ይል ጀመር። ‹‹ኧረ በፈጠራችሁ ሰላም ስጡን፤›› ሲል ጎልማሳው ሾፌሩና ጠበኞቹን እያፈራረቀ እያየ፣ ‹‹ፍትሕ በሚዘገይበት ዓለም ምን ሰላም አለ? ቻለው፤›› ተባለ። በስንት ሁከትና ንትርክ እህትማማቾቹ ጥቂት ተጉዘው ሲወርዱ ‹‹በስንቱ እንዝናና›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመው ወጣት አሸሞረ። የአንዱ ምሬት ለአንዱ መዝናኛ፣ የአንዱ ሙግት ሌላው መርቻ ሲሆን እያየን እንዳላየን አለፍነው። ካለፍን እንታለፋለና!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹መኖር አላጓጓን አለ እኮ! ወይ ዓለም፤›› ብሎ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ወጣቱ ብሶት ጀመረ። ‹‹ተው እንጂ ለመኖር መስሎኝ ዴሞክራሲ፣ ግድብ፣ ልማት፣ መዋጮ፣ ቅብጥርስ እያልን ፀጉር የምንነጨው?›› ወይዘሮዋ ሞገተችው። ‹‹እሱ ሳይሆን በቃ እኔ የዚህ የአየር ንብረት መዛባት ናላዬን እያዞረው ነው፤›› አላት ረገብ ብሎ። ‹‹እሱንስ ትናንት በቴሌቪዥን ሲያሳዩት ነበር። ዘለዓለም ሰበብ ነው ቴለቪዥኑም ሰው የሚያውቀው። የአደጉት አገሮች ፋብሪካዎች የሚለቁት ጭስ  . . .›› ስትል አቋርጧት፣ ‹‹ዓለም ላይ ያሉ ፋብሪካዎች በጠቅላላ ቢዘጉ አየሩ አይሻሻልም፤›› ብሎ አረፈው። ‹‹ለምን?›› ወይዘሮዋ ደነገጠች። ‹‹እንዴት ለምን? መሬት እኮ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት የሚባለውን ሁሉ ያጠራቀመችው በስድስት ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ ነው። እንዴት ነው በአንድ ቀን ፋብሪካ ዘጋችሁ ብላ አየሯን የምታድሰው?›› ብሎ ማጣቀሻ በማታውቅበት ነገር መጣባት።

‹‹እና ተስፋ የለንም እያልክ ነው?›› አሉት አዛውንቱ በድንገት። ‹‹ተስፋው አንድ ብቻ ነው። ይኼው አሁን ያለው የዓለም ሕዝብ ቁጥር በግማሽ መቀነስ አለበት  . . .›› ብሎ ሳይጨረስ ታክሲያችን በጩኸት ታመሰች። ወጣቱ ደንግጦ፣ ‹‹አስጨርሱኝ እንጂ›› ቢል ‹‹እስክታጠፋን ነው የምናስጨርስህ? አሸባሪ ከሩቅ አይመጣም አሉ የማን አገር ጠቅላይ ሚኒስትር። እንዲህ ነችና…›› እያለ ተሳፋሪዎች ወረዱበት። ‹‹እስካሁን እያዋጣሁ ሠርቼ ሠርቼ የህዳሴውን ግድብ መጨረሻ ሳላይ ይቀነስ ይለኛል?›› ሲል አንዱ፣ ‹‹ኮንዶሚኒየም ሳይደርሰኝማ አልወርድም። ታክሲ መሰለችው እንዴ ሕይወት ሞልቷል የሚለን ይኼ?›› እያለ ሌላው ተንጫጫ። ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ባይቋጭልን ኖሮ ቀናሽና ተቀናሽ አዳሽና ታዳሽ ጉዱ ፈልቶ ነበር። ‘አዳሽና ታዳሽ ሲፋጠጡ ከድጡ ወደ ማጡ’ አሉ አዛውንቱ። ይኼ ሁሉ ታክሲ ውስጥ ባይሆን የት ይገኝ ነበር? የባዶ ሆድ ወግ እንዴት ደስ ይላል፡፡ ቂም የለበትማ፡፡ መልካም ጉዞ!       

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት