Friday, March 1, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከፀረ ሙስና ተቋም ውስጥ የፍትሕ ሥራን መቀነስ የፀረ ሙስና ትግልን አለማወቅ ነው

ከፀረ ሙስና ተቋም ውስጥ የፍትሕ ሥራን መቀነስ የፀረ ሙስና ትግልን አለማወቅ ነው

ቀን:

በእውነቱ ምንአየሁ

ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ውልደት ምክንያት በሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም ከተነደፉት ከአምስቱ ንዑሳን ፕሮግራሞች ውስጥ የሥነ ምግባር ማሻሻያ ፕሮግራምን በመጠቀም ነበር፡፡ ይህንኑ በአቅም ግንባታ ፖሊሲና ስትራቴጂ ሰነድ ላይም የኮሚሽኑን መመሥረት አስፈላጊነት በግልጽ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም  የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለሰ ዜናዊ  ጭምር በመሩዋቸው መድረኮች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶበት፣ የውጭ ባለሙያዎች ተቀጥረው የሰጡትን ድርጅታዊ አወቃቀርን በመከተል ነበር የተመሠረተው፡፡ ኮሚሽኑ ሦስት ዓላማዎችን ይዞ በአዋጅ እንዲመሠረት ተደርጓል፡፡ የመጀመርያው የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ትምህርቶችን ለኅብረተሰቡ በማስተማር ሙስናን የሚጠየፍ ዜጋ መፍጠር፣ ሁለተኛው በመንግሥት ተቋማት ለሙስናና ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን በመለየት  መከላከል፣ ሦስተኛው አሁን ለመቀነስ እየተሠራ ያለው የፍትሕ ሥራ የሆነው የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን በመቀበል፣ በመመርመር፣ በመክሰስና በማስቀጣት የተመዘበረ ሀብት ማስመለስ ዓላማዎቹ ናቸው፡፡ እንግዲህ ሦስቱም ዓላማዎች የማይነጠጣሉ አንዱ ሌላውን እየተከተለ የሚከናወን፣ ተመጋጋቢነት ያላቸው መሆኑን በወቅቱ የምሥረታ ጥናት ሲያካሂዱ የነበሩት ባለሙያዎች በሰነዶቻቸው ላይ በግልጽ  አስቀምጠዋል፡፡ መጀመርያ ማስተመር፣ ቀጥሎ መከላከል ከሦስቱም ውጪ የሆነ ሰው ሙስና የሚሠራ ከሆነ በሕግ ማስቀጣትና የመዘበረውን የሕዝብ ሀብት ማስመለስ ነው መርሁ፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በአዋጅ ከተመሠረተ 15ኛውን ዓመት ግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. ያከብራል፡፡ የኮሚሽኑ አመሠራረት በወቅቱ በአገሪቱ የሙስና ወንጀል እየተበራከተ መምጣቱና አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት እየዘነጉ ከአገር ይልቅ ወደ ራስ ወዳድነት እያዘነበሉ በመምጣታቸው፣ ቢያንስ ሃይ የሚል ተቋም አስፈላጊነቱ በደንብ ስለታየ ነበር፡፡ ተቋሙ ሲመሠረት  የፍትሕ ሚኒስቴር፣ ልዩ ዓቃቤ ሕግና ፖሊስም ነበር፡፡ ሙስና ልዩ ሙያና አካሄድ ስለሚጠይቅ እንጂ እነዚህ ተቋማት አይሠሩም ተብሎ አልነበረም ለብቻው በሕግ እንዲመሠረት የተደረገው፡፡ በሌላ በኩል ከደርግ ዕዝ ኢኮኖሚ ሥርዓት ወጥተን ስለነበር ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ)፣ ወዘተ ጋር ግንኙነት በመጀመራችን፣ እነሱም የጠየቅነውን ብድርና ዕርዳታ ለመስጠት በቂ ዋስትና ስለፈለጉም ነበር፡፡ በመሆኑም  የኮሚሽኑ ሥራ ልዩ ሙያንና ጥንቃቄን የሚጠይቅ በመሆኑ በሙያው የሠለጠነ የሰው ኃይል በሌለበት አገር እንሞክረው በሚል እሳቤ በድፍረት ነበር የተመሠረተው፡፡  ተቋሙ ሥራውን በዳዴ ይጀምር እንጂ በአሁኑ ወቅት በፀረ ሙስና ትግል ሙያ ከፍተኛ ልምድና ክህሎት ያዳበረና ከፍተኛ ውጤቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ ተቋም መሆኑን፣ በተለያየ የሚያወጣቸው ሪፖርቶችና የተወካዮች ምክር ቤት ከ2008 ዓ.ም.  በፊት የሚያደርጋቸው የክትትልና ድጋፍ ሥራ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡ የተወካዮች ምክር በ2008 በጀት ዓመት ለተቋሙ ጥሩ ዕይታ ያለው አይመስለኝም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሙስና ወንጀል ረቂቅ፣ ውስብስብና ባህሪን በየጊዜው የሚለዋወጥ በመሆኑ፣ በሰዎች አዕምሮ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ ስለሆነም ኮሚሽኑም የሙስና ወንጀል ረቂቅነቱን እየተከተለ ራሱን በማዘጋጀት ሙስና በሚፈጸምበት አካባቢዎች ላይ ዝግጅት  እያደረገ ኃላፈዎችን፣ ሠራተኞችን (በጊዜው ባያውቀውም ሙስኞችን፣ ጠቋሚዎችንና ምስክሮችን ያካተተ) የሥልጠና ፕሮግራሞችን በማዘጋጃት ያስተምራል፡፡ በመቀጠልም በየተቋማቱ ውስጥ ለሙስናና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ የሆኑ አሠራሮችን በመለየት የአሠራር ሥርዓት ጥናት ያካሂዳል፡፡ የጥናት ውጤቱ እንዲተገበር ክትትልና ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ያረጋግጣል፡፡ ሁለቱንም አሠራሮች ሳይቀበሉና ሳይመሩ የሙስና ወንጀል የሚሠሩትን ደግሞ በመመርመር፣ በመክሰስና በማስቀጣት የተመዘበረ ሀብት የማስመለስ ሥራ ይሠራል፡፡

ኮሚሽኑ ይህን ሥራ የሚሠራው የተለያዩ ባለሙያዎችን በመቅጠርና በማሠልጠን ሲሆን፣ በተለይም አብዛኛዎቹ ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት የተሻለ ልምድና ዕውቀት እንዳላቸውና እንዳካበቱ ይገመታል፡፡ ኮሚሽኑ በተመሳሳይ በሁሉም የክልል መስተዳደሮች የፀረ ሙስና ተቋም መሥርቶ ትግል እየተካሄደ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ያሉት በተለይም ከሙስና የፀዱ የሚባሉ አገሮች ሦስቱን ዓላማ ይዞ የሚቀንቀሳቀስ፣ የፀረ ሙስና ተቋም በማዋቀር እንደሆነ ወደ አገሮቹ መሄድ ሳያስፈልግ ድረ ገጾችን በማየት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያም የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋምን ስታቋቁም የተለያዩ አገሮችን ተምክሮና ልምድ ወስዳ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡

ሌላው ኮሚሽኑ እስካሁን እንቅስቃሴ፣ ልምድና ተሞክሮ ያለበት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ከዓለምና ከአኅጉራችን ተሞክሮና ልምድ በማነፃፀር በግኝት ላይ ተመሥርቶ ወደ ድምዳሜ ላይ መድረስ ሲገባ፣ ያለምንም ጥናትና መረጃ የኮሚሽኑን አቅም ማሳነስ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በቅድሚያ ለምን ዝርዝር ጥናት እንዲካሄድ አይደረግም? ለምን ተሞክሮዎችና ልምዶች አይታዩም? ምንስ ጠንካራና ደካማ ጎን ታይቶ ነው ለመበተን ውሳኔ እየተሰጠ ያለው? ይህ የፀረ ሙስና ተቋም የአገር ሀብት ነው፡፡ ሕዝቡ እሮሮውን የሚያሰማበት ተቋም ነው፡፡ ዜጋው በሙሰኞች ላይ ቁጭቱንና ብሶቱን የሚወጣበት ነው፡፡ በፀረ ሙስና ትግል እንቅስቃሴ  ውጤታማነት ላይ ጥናት ተካሂዶ ነው  ከተባለ እስኪ በግልጽ እንስማው፣ ሕዝቡም እንዲያውቀው ይደረግ፡፡ በእርግጥ ተቋሙ የሚመራው በሰዎች ነው እንጂ በመላዕክት አይደለም፡፡ እንደ ማንኛውም ተቋም የውስጥ ችግሮች ይኖሩታል፡፡ አሉትም፡፡ የውስጥ ችግሮችን ደግሞ አሁን መንግሥታችን የመልካም አስተዳደር ችግርን ለመፍታት ባስቀመጠው መርህ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ሀብት ያፈራሉ የተባሉ ባለሙያዎች ካሉ የትም አልሄዱም አሉ፡፡ እኔ ራሴ የማውቃቸው ስላሉ እንደ ማንም ዜጋ ከሕግ በላይ አይደለም፣ ሊጠየቁ ይገባል፡፡

እስቲ የአገራችንን የፍትሕ ሥርዓት በትንሹ እንቃኝ፡፡ አገራችን ከአፄ ምኒልክ አገዛዝ ጀምሮ  ሥርዓት ያለው የፍትሕ ሥርዓት እንዳለ ነው እኔ የማውቀው፡፡ ያልተማሩ ወላጆቻችን በፍትሕ ይዳኙ እንደነበር እናውቃለን፡፡ እኔ የሚገርመኝ በአንድ ወቅት የፍትሕ ሚኒስትር ባቀረቡት የፍትሕ አካላት የኪራይ ሰብሳቢነትና የሙስና ችግሮች እነዚያ አሸባሪ ከምንላቸው ባልተናነሰ አይደለም እንዴ ሕዝቡንና መንግሥትን እየበደሉ ያሉት፡፡ ደግሞ እኮ የፍትሕ ሥርዓት በእኛ አገር የዜጎች መብት ማስከበርና የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ሳይሆን የሀብት ማከባቻ እኮ ነው፡፡ ከፀረ ሙስና ተቋም የግል ጥብቅና ፈቃድ ወስደው የወጡት እኮ ሁሉም በእግር አይሄዱም፡፡ እኔ 52 ዓመቴ ነው፡፡ በመንግሥት ተቋማት የብዙ ዓመታት አገልግሎትና ልምድ አለኝ፡፡ እስካሁን ድረስ የታክሲ ፍራንክ ይቸግረኛል፡፡ በዚህ ዕድሜ ሐይገርና ባስ ተጋፍቼ ነው የምሄደው፡፡ ለዚያውም የወያላዎችን ግልምጫና ስድብ ችዬ፡፡  የፀረ ሙስና ተቋም ዓቃቤ ሕግ፣ ዳኛና የተከሳሽ ጠበቃ በአንድ ወቅት የአንድ ትምህርት ቤት፣ የአንድ ክፍል ጓዳኞች እንደሚሆኑ አትርሱት፡፡ ከእነዚህ እንዴት ነው ዜጎች ፍትሕ በትክክል ያገኛሉ የሚባለው? መንግሥት የጥቅም ግጭት የሚፈጥሩ አሠራሮችን ለይቶ ማስተካከል ሲገባው ወደ ማጥ ውስጥ እንዲገባ መፍቀዱ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ሌላው ፖሊስ ነው፡፡ እኔ ባለሁበት አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ፣ ወንጀል መርማሪ፣ ከከሳሽና ከተከሳሽ ምልጃ እንደሚቀበሉ በደንብ አውቃለሁ፡፡ ጥቆማ አቅርብ አትበሉኝ እንጂ፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በ2005 ዓ.ም. ያወጣውን የስታስቲክስ መረጃ በአጋጣሚ አግኝቼ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ከከሰሳቸው አካላት ከመሬት ቀጥሎ አገር ያስቸገሩት የፍትሕ አካላት ሰዎች ናቸው፡፡ በቀላል ሙስና ወንጀል ክስ ላይ የፖሊስ ድርሻ 60 በመቶ ይይዛል፡፡ እንግዲህ ይህ ችግር በደንብ ባልጠራበትና የኅብረተሰብ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ባልተሠራበት፣ እንዴት ተደርጎ ነው ቢያንስ ማስፈራሪያ የሆነውን ተቋም ለማፍረስ የታሰበው?

የሙስና ወንጀል የጥቂት ሰዎች (የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የባለሀብቶች፣ የደላሎች፣ ወዘተ) ሥራ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለምን ይሰርቃሉ? ቢባል መልሱ ሀብታም ለመሆን፣ የተሻለ ገቢ ፍለጋና በምድር ላይ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ነው፡፡ ይህ ነው በቃ ፍላጎታቸው፡፡ ስለዚህ ጥቂቶች ሀብታም ሆነው የተሻለ ኑሮ ሲኖሩ ብዙኃኑ ደግሞ እየተቸገሩ ይኖራሉ፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ሙስናን ለመሥራት የተመቻቸ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ለመከላከል አቅም ያለው ጠንካራ የፀረ ሙስና ተቋም ያስፈልገናል፡፡ ልጆቻችን ይህን ለማስቀረት እኮ ነው 17 ዓመታት ሕይወታቸውን ሰጥተው የታገሉት፡፡ አጥንቶቻቸው እኮ ይወቅሰናል፡፡ ይታሰብበት፡፡

ዛሬ ያደጉትና ያላደጉት አገሮች የፀረ ሙስና ተቋማት አሏቸው፡፡ የተቋማቱ ጥንካሬና ድክመት እንደ አገሮቹ መንግሥታት ጥንካሬና ቁርጠኝነት ይወሰናል፡፡ አፍሪካ ግን ለዚህ የታደለች አይደለችም፡፡ ወደ አመራር የሚመጡ የአፍሪካ መሪዎች ቁርጠኛ ስለማይሆኑ የሚመሠርቱት የፀረ ሙስና ተቋምም ጠንካራ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ግን የአፍሪካ አገሮች ካላቸው የፀረ ሙስና ተቋማት የተሻለ ተቋም እንዳላት የዓለም ባንክን ጨምሮ፣ የተለያዩ አበዳሪና ለጋሽ ድርጅቶችና አገሮች መስክረዋል፡፡ ይህ ተቋም ነው እንግዲህ በረቂቅ ዘዴ ሲፈርስ ምን ይዘን ነው በእነዚህ አካላት ፊት የምንቀርበው የሚባለው፡፡ ይህን ተቋም  የበለጠ  ማጠናከር ሲገባን አፍርሰን ምን ልንሆን ነው? መንግሥታችን ለሕዝብ የቆመ ከሆነ ከልብ ቢያስብበት ጥሩ ነው፡፡

የፀረ ሙስና ተቋሙን ለማፍረስ የታሰበው መንግሥት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅድ ሰነድ ላይ ኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስናን መከላከልና መዋጋት የሞት ሽረት ነው የሚል ‹ሮድ ማፕ› በመንደፉ ሥጋቱ የገባቸው ሰዎች ተቋሙን ለመበታተን ያሴሩት ሴራ ነው የመሰለኝ፡፡ የፀረ ሙስና ተቋም የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ ኮሚሽኑ ለምድነው ወደ ምክር ያዘነበለ ሥራ የሚሠራው? ብሎ ነበር ግብረ መልስ የሰጠው፡፡ እኔም ይህ አቋም ነበረኝ፡፡ ምክር መስጠት አንዱ ዓላማው ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ብዙ ሙሰኞችን ሕግ ፊት ማቅረቡን ከተቋሙ ሪፖርት ላይ አድምጫለሁ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በአገራችን በባለሀብት አጋፋሪነት በመንግሥት ኃላፊና በመንግሥት ሠራተኛ ከሚፈጸመው የሙስና ወንጀል፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን መከላከልና መዋጋት የቻለው ቢበዛ ከ25 እስከ 30 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ሙሰኞችን የሚያስረው እኮ በደረሰለት ጥቆማ እንጂ፣ የራሱን ኢንተለጀንስ ተጠቅሞ አይደለም፡፡

የደረሰውን ብቻ መሥራት ደግሞ የመንግሥት አቅጣጫ ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢባል ኢንተለጀንስ የሚጠቀም ከሆነ ብዙ ጉድ ሊወጣ ስለሚችል፣ ዞሮ ዞሮ ጦሱ ለማን አንደሚሆን መንግሥትም ሥጋት ስላለው እንደሆነ ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ የተወካዮች ምክር ቤት ከሁለት ወራት በፊት ሲያራምድ የነበረውን አቋም የማይረሳ ከሆነ አሁን ሰዎች ለማውጣት ያቀረቡትን ሕግ አይፀድቅም የሚል ድምዳሜ አለኝ፣ በጣም እርግጠኛ ነኝ፡፡ የፓርላማ አባላት ይህንን ካደረጉም በዜጎች ይመሰገናሉ፣ አገሪቱን ከጥፋት በማዳናቸው ለዘለዓለሙ ይዘከራሉ፡፡ የፀረ ሙስና ተቋም መነካት የለበትም፡፡ ካልሆነ ግን ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆኖ እንደ ሌሎች የዴሞክራቲክ ተቋማት ለይስሙላ ይኖራል፡፡ አገርን ጥቂቶች ይቀራመታሉ፣ ቆርጥመው ይበሏታል፡፡ የተወካዮች ምክር ቤት ሕጉን ካፀደቀ ግን ታሪክ የማይረሳውን ጥፋት ያጠፋል፡፡  ልታድግ በዳዴ ያለች አገር ያሰበችበት ቦታ ሳትደርስ ዕድገቷ ያበቃለታል ማለት ነው፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አባላት የእኛ ተወካዮች ናቸውና እኛን ረስተው ያቀረብነውን አቤቱታ ወደ ጎን ጥለው ሕጉ የሚፀድቅ ከሆነ ግን ሙስኞች እልል ይበሉ፣ የዝነኛውን ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠን ‹ያሰብኩት ተሳካ፣ ያለምንኩት ሆነልኝ› ይበሉ፡፡ ዘፈኑንም ለዜጎች ይጋብዙልን ሚዲያዎችን ተጠቅመው፡፡ እኛም ዜጎች ቀን እስከሚወጣልን ድረስ ሱባዔ እንገባለን፡፡ ይብቃኝ፡፡ በመጨረሻም የኮሚሽኑን ሥራ ለመቀነስ ከተፈለገ የባለሙያ ጥናት ያስፈልጋል፡፡ ጥናቱ ይካሄድ፣ ተሞክሮና ልምዶች ይታዩ፣ አዋጭነቱ በደንብ ይገምገም፣ ሕዝብ/ዜጋው በግልጽ ይወያይበት፣ ለይስሙላ በቲቪ ኑና ተወያዩ ማለት ተገቢ አይመስለኝም፣ በቂም አይደለም፡፡ ‹የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች› እንዳይሆን በደንብ ይታሰብበት፡፡ የወከልናችሁም አቤቱታችንን ስሙልን፡፡ የምክር ቤት ቆይታ ዘመናችሁ ሲጠናቀቅ አብረን እንደምንቆዝም ከወዲሁ አስቡበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...