Friday, December 8, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ወደ ግል የተዛወሩ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች እየተዳከሙ መሆኑ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት ከኃላፊነት ተነሱ

የአዋሳ፣ የአርባ ምንጭ፣ የድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎችና ቢኤም ኢትዮጵያ የልብስ ስፌትና ጨርቃ ጨርቅ አክሲዮን ማኅበር ከመንግሥት ወደ ግል ከተዘዋወሩበት ጊዜ አንስቶ በታሰበው ደረጃ ውጤት እያመጡ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) የ2008 የስድስት ወራት የሥራ ሪፖርቱን ባለፈው ዓርብ ባቀረበበት ወቅት ነው፡፡

በኢሠማኮ ፕሬዚዳንት በአቶ ካሣሁን ፎሎ በቀረበው በዚሁ ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፣ እነዚህን የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የገዙት ባለሀብቶች ተቋማቱ ብቁ፣ ተወዳዳሪና ውጤታማ ሆኖ እንዲቀጥሉ በተሻለ ሁኔታ ለመምራትና ለማሻሻል ነበር፡፡ ሆኖም ከመንግሥት ጋር በገቡት ውል መሠረት የተቋማቱን አሠራር ከማሻሻልና የሠራተኞችን ዘላቂ የሥራ ዋስትናና ጥቅማ ጥቅሞች ከማክበር ይልቅ፣ በመለዋወጫ መሣሪያዎች እጦትና በጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት ምክንያት የፋብሪካዎቹ የሥራ እንቅስቃሴ ከቀን ወደ ቀን እየተዳከመ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ፋብሪካዎች የሚገኙ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበራት የተቋማቱ ቀስ በቀስ መዳከም ያሳሰባቸው እንደሆነ ከየፋብሪካዎቹ የሚደርሷቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የሠራተኛ ማኅበራቱም ለጨርቃ ጨርቅ ቆዳና ልብስ ስፌት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ሥጋታቸውን በጽሑፍ ጭምር ያቀረቡ መሆኑን በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑም የችግሩን አሳሳቢነት በተጨባጭ ማስረጃ አስደግፎ ለኢሠማኮ ማቅረቡን የገለጹት አቶ ካሣሁን፣ በዚሁ መሠረት በተከሰተው ችግር ዙሪያ ውይይት ለማድረግና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ኢሠማኮ ለኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በደብዳቤ ጠይቆ፣ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ አመራሮች በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡ በተደረገውም ውይይት የሠራተኞች የሥራ ዋስትና በተመለከተ መንግሥት የሚያየው ሆኖ የተከሰቱትን ችግሮች ግን ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር እንዲቀርብ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት፣ የውይይት መድረኩ እንዲመቻች ተጠይቆ ምላሽ እየተጠበቀ ነውም ተብሏል፡፡ ሆኖም አሁንም የፋብሪካዎቹ አካሄድ በአሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡  

ኢሠማኮ የኢንዱስትሪ ግንኙነት ሥራዎችና የማኅበር አደረጃጀትን በተመለከተ በቀረበው በዚሁ ሪፖርቱ፣ በሌሎች ተቋማት ውስጥ ተከሰቱ ያላቸውን ችግሮችን ጠቅሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ የአዶላ ወርቅ ልማት ድርጅትን የሚመለከተው አንዱ ነው፡፡ ድርጅቱ ለልማት ከመንግሥት የተሰጠው ሕጋዊ የወርቅ ማምረቻ ቦታ በአካባቢው ሌሎች አምራቾች በመያዙ ምክንያት፣ የድርጅቱ ቀጣይ ሕልውናና የሠራተኞች የሥራ ዋስትና አደጋ ላይ መሆኑን ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡

ለአዶላ ወርቅ ወቅታዊ መፍትሔ እንዲፈለግለት ከአገር አቀፍ ኃይል ማመንጫ ኬሚካልና ማዕድን ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን በኩል የቀረበው ጥያቄ፣ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመክሮበታል፡፡ በመጀመሪያ ጉዳዩን ይዞት የሄደው ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ነው፡፡ ሆኖም ሚኒስቴሩ ጉዳዩ የማይመለከተው መሆኑን በመግለጹ እንደገና ጉዳዩ ይመለከተዋል ወደተባለው ማዕድን ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር በኩል መፍትሔ እንዲሰጥ በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ ጥያቄው ግን እስካሁን መፍትሔ አላገኘም፡፡ በኢሠማኮ የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ የቀድሞ የሕዝብ ሱቆች ሠራተኞች መብትን ለማስጠበቅ ያከናወነውን ሥራ ለጠቅላላ ጉባዔው አቅርቧል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ የሕዝብ ሱቅና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ተቋማት ወደ ሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከተላለፉ በኋላ በአንዳንድ ተቋማት የሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር ሕጋዊ መብት እየተጣሰ መሆኑን ገልጿል፡፡ ለዚህ የመብት ጥሰት መፍትሔ እንዲሰጣቸው የቱሪዝም ሆቴሎችና ጠቅላላ አገልግሎት ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ጥያቄ በማቅረቡ፣ ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል ተብሏል፡፡

በዚሁ መሠረት የችግሩን አሳሳቢነት ተጠቅሶ የሠራተኞች የመደራጀትና የመደራደር ሕጋዊ መብት እንዲከበር መፍትሔ እንዲሰጣቸው፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ማሳወቅ አንዱ ዕርምጃው እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ቢሮውም የተቋማቱ ሠራተኞች በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ መሠረት የተከበረላቸው የመደራጀትና የመደራደር ሕጋዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ መመርያ እንዲተላለፍ በማድረግ ችግሩን ለማቃለል ተሞክሯል ተብሏል፡፡ 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዓርቡ የኢሠማኮ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ዘሪሁን ዓለሙ፣ ከኃላፊነታቸው ተነስተው አዲስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሰይሟል፡፡

ከኢሠማኮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ አቶ ዘሪሁን ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት የትራንስፖርትና መገናኛ ሠራተኛ ማኅበራት ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በመሆን በሚያገለግሉበት ወቅት ከፋይናንስ አሠራር ውጭ ተፈጸመ በተባለ ወጪ ምክንያት ነው፡፡ ለጠቅላላ ጉባዔው በቀረበው ሪፖርት ላይ የፌዴሬሽኑ ኦዲት ኮሚቴ ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ባቀረበው የሥራ ክንውን ሪፖርት ቀደም ሲል የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የነበሩና በኋላም የኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ዘሪሁን ዓለሙ፣ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት ፈጽመዋቸዋል የተባሉ ጥፋቶች መቅረባቸውን ይገልጻል፡፡ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤትም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ተወያይተውበት ግለሰቡ ኢሠማኮ ጋር እየሠራ በመሆኑ፣ የኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ጉዳዩን አጣርቶ አቶ ዘሪሁን ከምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው እንዲነሱ መወሰኑን በዕለቱ ገልጿል፡፡

በዚሁ መሠረት የኢሠማኮ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባካሄደው ግምገማ አቶ ዘሪሁን የፌዴሬሽኑ አመራር በነበሩበት ወቅት የፈጸሟቸው ጥፋቶች በኢሠማኮ ሕገ ማኅበርና የዲሲፕሊን መመርያ መሠረት ደረጃ የማያስጠብቅና ከባድ ሆኖ በመገኘቱ፣ ከኢሠማኮ ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው እንዲሰናበቱ ማድረጉንም ለጠቅላላ ጉባዔ ተገልጿል፡፡

ይህንኑ ውሳኔ ተከትሎ በተሰናባቹ ምክትል ፕሬዚዳንትና በተጓደሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምትክ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኖ በዚሁ መሠረት አቶ አያሌው አህመድ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ደግሞ የኢንዱስትሪ ግንኙነትና ማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ኃላፊ ሆነው እንዲሠሩ ተመርጠዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች