ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን (ታኮን) በአጠቃላይ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት ያስችለኛል ያለውን አሠራር ለመዘርጋት ፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ ከተባለ ኩባንያ ጋር በመፈራረም ሥራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡
የሁለቱን ኩባንያዎች ስምምነት በተመለከተ የተሠራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን አጠቃላይ አሠራር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ኮንትራክተሮች የሚከተሉትን ተቋማዊ አደረጃጀት እንዲኖረው የሚያስችለው ነው፡፡ በፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ ተሠርቶ የሚተገበረው አሠራር የድርጅቱን የኢንጂነሪንግ፣ የኮንስትራክሽን ሥራዎች፣ የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ ሥርዓት፣ የንብረት አስተዳደር፣ የግዥ አቅርቦት፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎችን እንዲሁም ሌሎች የሥራ ሒደቶችን በዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት ለውጥ ማስተዳደር የሚያስችለው እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
ሳፕ (SAP) በዓለም አቀፍ ደረጃ ግዙፉ ተቋማዊ የመዋዕለ ንዋይ ዕቅድ አገልግሎት ሰጪ ሲሆን፣ ለልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎች የምክር አገልግሎት የሚያቀርብ ድርጅት ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ዋና መሥሪያ ቤት ኮንትራቱ በተፈረመበት ወቅት የታፍ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ሰይፉ አምባዬ እንደገለጹት፣ ይህ ስምምነት የኮንስትራክሽን ድርጅቱን አጠቃላይ አሠራር በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ነው፡፡ ድርጅታቸው ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ ተከታታይ መሻሻሎችንና ዓመታዊ የአፈጻጸሞችን፣ የገበያ ድርሻውንና ማኅበረሰባዊ ኃላፊነቶችንና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነቱ እያደገ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰይፉ፣ እየጠነከረ የመጣውን ውድድር ለመቋቋም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አሠራርን መዘርጋት የግድ አስፈላጊ በመሆኑ ስምምነቱን ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ወቅታዊውን የገበያ የውድድር ለመቋቋም እንዲሁም የአገልግሎት ጥራትና የማስረከቢያ ጊዜንም በትክክል ለመተግበር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ጊዜው የሚፈልገው ዕርምጃ ነውም ተብሏል፡፡ ‹‹ኩባንያችን እደርስበታለሁ ብሎ ላስቀመጥነው ግብ መሳካትና እንዲሁም በድርጅቱ ውስጥም ሆነ በውጭም የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ዘንድ የሚፈለግብን መዳረሻዎች ላይ ለመገኘት እንድንችል፣ አስተማማኝ መሣሪያ ሆኖን ብቃታችንንም በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ እንዳለው በመተማመናችን ትግበራው ላይ ለመሠማራት ወስነናል፤›› ሲሉ አቶ ሰይፉ ገልጸዋል፡፡
ትግበራው ለተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን በኢንዱስትሪው ተጠቃሽ እንዲሆን የሚያስችለውና የፕሮጀክት አፈጻጸሞቹ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደሚረዳው የፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ግርማቸው አድማሱ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የፋይናንሺያል ሥርዓቱ፣ በሰው ኃይል ሀብት ልማትና በሌሎች ወሳኝና ቁልፍ የሆኑ የንግድ ሥርዓቱ አኳያ በደንበኞቹ የሚተገበርና አገልግሎቱ በዓለማችን አሉ የተባሉ ተቋራጮች የሚሠሩበት ደረጃ ማቅረብ የሚያስችለው መሆኑንም አቶ ግርማቸው ገልጸዋል፡፡
ፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ በምሥራቅ አፍሪካ ከሚገኙ የሥርዓት (ሲስተም) ትግበራና ዝርጋታ አቅራቢ ድርጅቶች ግዙፉና አንደኛው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የአሠራር ሥርዓት ማሻሻያዎችን ተቋማዊ ሽግግሮችን (ለውጦችን) በማድረግ የተራቀቁ ቴክኖሎጂዎችን በማስተግበር የሚታወቅ ድርጅት ነው ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ፌርፋክስ በኢትዮጵያ ግዙፉ የሳፕ (SAP) የተቋማዊ የመዋዕለ ንዋይ ዕቅድ አቅራቢ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከሚገኙ ሌሎች የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት የሚሠራ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክትም በተመለከተ ከተመሳሳይ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር በመሥራት ጉልህ ልምድ ካዳበረውና መሠረቱን በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ካደረገው አይኤስዋይኤክስ (ISYX) ቴክኖሎጂ በመባል ከሚታወቀው የቴክኖሎጂ አቅራቢ ድርጅት ጋር በሽርክና የሚሠራ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ ፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቱን ለመዘርጎት የስድስት ወራት ጊዜ እንደተሰጠው አቶ ግርማቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋት ፌርፋክስ ቴክኖሎጂስ የተመረጠው ተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን አገልግሎቱን ለማግኘት አውጥቶት በነበረው ጨረታ አሸናፊ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ጨረታ ስምንት ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ ተብሏል፡፡