የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ታኅሳስ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. ያካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ውሳኔና ምርጫ በፍርድ ቤት ተሽሮ ድጋሜ ጠቅላላ ጉባዔ እስኪጣራ ንግድ ምክር ቤቱ በባላደራ ቦርድ እንዲተዳደር ተደርጎ ነበር፡፡
ይህንኑ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲያስፈጽም የተሰየመው የባላደራ ቦርድ በፍርድ ቤት የተሻረውን የንግድ ምክር ቤቱ ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔና ምርጫ በድጋሚ እንዲከናወን አድርጓል፡፡ በወቅቱ ባላደራ ቦርዱን እንዲመሩ የተሰየሙት የቀድሞው የንግድ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ አሊ ሲራጅ (አሁን በሕይወት የሉም) እና በባላደራ ቦርዱ ውስጥ የተካተቱት ሌሎች አባላት ዋነኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በድጋሚ በመጥራት አዲስ ምርጫ እንዲከናወን በማድረግ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አንዲፈጸም አድርገዋል፡፡
በባላደራ ቦርዱ አስፈጻሚነት መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው በዚሁ ጠቅላላ ጉባዔና አዲስ ምርጫ በፍርድ ቤት ውሳኔ ሚያዝያ 10 ቀን 2006 ዓ.ም. የተሻሩትን አብዛኛዎቹን ተመራጮች መልሶ ወደ አመራር ያመጣ አንደነበርም ይታወሳል፡፡ በዚህ ምርጫ ሒደት ብዙ ጥያቄዎች የተነሱ ቢሆንም፣ ባላደራ ቦርዱ የዕለቱን ምርጫ አፀድቆ ጠቅላላ ጉባዔውም የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ ተጠናቋል፡፡ ክንውኑ በወቅቱ የነበረውን ውዝግብ ያረገበ ቢሆንም፣ በዚያው ዕለት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ውሳኔ የተላለፈበት አንድ ጉዳይ ግን መፈጸም ባለመቻሉ አሁንም በአባላት ዘንድ ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡
አንዳንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባላት እየተነሳ ነው የተባለው ጥያቄም በባለዳራ ቦርዱ ተጠርቶ በነበረው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተመረጠው የዳይሬክተሮች ቦርድ የሥራ ዘመን አንድ ዓመት ብቻ እንደሚሆን የተወሰነው ውሳኔ ተግባራዊ መሆን ካለመቻሉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ለአንድ ዓመት እንዲያገለግል የተመረጠውና አቶ ኤልያስ ገነቲ የሚመራው የንግድ ምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ የተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ተጠናቋል፡፡
መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ኃላፊነቱን ተረክቦ ለአንድ ዓመት እንዲያገለግል የተመረጠው አዲሱ አመራር፣ የአንድ ዓመት አገልግሎቱ ካበቃ በኋላ የ10ኛ እና 11ኛውን ጠቅላላ ጉባዔውን በአንድ ላይ እንዲካሄድ የጠቅላላ ጉባዔው በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፎም ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የንግድ ምክር ቤቱ ዳይሬክተሮች ቦርድ መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ የፀደቀውን የጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ማክበር አልቻለም፡፡ ጉዳዩን የሚከታተሉት የንግድ ምክር ቤቱ አንዳንድ አባላት እንደሚገልጹት፣ በወቅቱ በጠቅላላ ጉባዔ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ለአንድ ዓመት እንዲያገለግል የተመረጡ አመራሮች የአገልግሎት ዘመን መጋቢት 10 ቀን 2008 ዓ.ም. ቢጠናቀቅም፣ እስካሁን ጠቅላላ ጉባዔውን ሊጠራ አለመቻሉ አግባብ እንዳልሆነ ያመላክታሉ፡፡
መጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ከመጠናቀቁ በፊት አሥረኛውንና አሥራ አንደኛውን የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራትና ማካሄድ እንዲሁም የሁለቱን በጀት ዓመታት ዓመታዊ ጉባዔውን በአንድ ላይ ከማካሄድ ጎን ለጎን ንግድ ምክር ቤቱን የሚመሩ አዳዲስ አመራሮን ለመምረጥ ምርጫ ማካሄድ ይጠበቅበት እንደነበርም ተገልጿል፡፡ ነገር ግን አሁን በአመራር ላይ ያለው ቦርድ የተሰጠውን ኃላፊነት ወደ ኋላ በማድረግ የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ በሚፃረር መልኩ መጠራት ያለበትን ጉባዔና ምርጫ ሳያካሂድ ቀርቷል፡፡ ይህ የጠቅላላ ጉባዔተኛውን ውሳኔ ያለማክበርና ተግባራቸው ሕገወጥ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ ጊዜውን ጠብቆ መካሄድ የነበረበት የንግድ ምክር ቤቱ 10ኛ እና 11ኛ ጠቅላላ ጉባዔ ለምን መካድ እንዳልቻለ እንኳን ለአባላቱ አለመግለጻቸው እንዳሳዘናቸውም ያመለክታሉ፡፡
መጋቢት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. የተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የተላለፈው ውሳኔ በፍርድ ቤት የተሾሙት የባላደራ ቦርድ አባላት ፊት እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ የባላደራ ቦርዱም ቢሆን የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች ለምን ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳልጠሩ መጠየቅ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡
ጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫው ወቅቱን ጠብቆ አለመከናወኑም በንግድ ምክር ቤቱ የመተዳደሪያ ደንብ መሠረት አንድ የቦርድ አመራር በኃላፊነት ላይ መቆየት ያለበትን ጊዜ ያፋለሰም እንደሆነ ከተሰጡት አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን በፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በቦርዱ አባልነት ለመምራት የሚችለው ለሁለት ዓመት ነው፡፡ አሁን ግን በኃላፊነት ላይ ያሉት አመራሮች የኃላፊነት ዘመን በመተዳደሪያ ደንቡን በሚፃረር ሁኔታ ከተቀመጠላቸው የኃላፊነት ጊዜ በላይ እንዲቆዩ እያደረገ ነው፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የንግድ ምክር ቤቱ አመራሮች እንደገለጹት ደግሞ፣ በጠቅላላ ጉባዔው በእርግጥም በዚህ ወር መደረግ እንደነበረበት ያምናሉ፡፡ ነገር ግን ጠቅላላ ጉባዔው ያልተጠራበትን የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ያስረዳሉ፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ኤልያስ ገነቴ እንደገለጹት፣ አሁን በአመራር ላይ ያለው ቦርድ የአንድ ዓመት የሥራ ዘመኑ ቢያልቅም፣ አሳማኝ ናቸው ባሉዋቸው ምክንያት የጠቅላላ ጉባዔው እንዲራዘም ተደርጓል፡፡
በዚህ ወር መደረግ የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔ ያልተጠራበት ዋነኛ ምክንያት የአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተ ያወጣው መመርያ መሆኑን አቶ ኤልያስ ተናግረዋል፡፡ መመርያው ሁሉም የንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫቸውን በተለያየ ጊዜ ማድረግ እንደማይችሉና ሁሉም በተመሳሳይ ወቅት እንዲያካሂዱ የሚደነግግ ነው፡፡
በዚህ ድንጋጌ መሠረት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫን ከኢትዮጵያ በጀት ዓመት መዝጊያ ጋር ተሳስሮ ሰኔ 30 ከተጠናቀቀ በኋላ ባሉት ሦስት ወራት ማካሄድ እንዳለባቸው የሚደነግግ በመሆኑ፣ በዚህ መመርያ መሠረት የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በመጋቢት 2008 ዓ.ም. ማካሄድ የነበረበትን ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ ወደ መስከረም 2009 ዓ.ም. እንደተሸጋገረ የአቶ ኤልያስ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡
ይህ የአዲስ አበባ ንግድና ምክር ቤት ውሳኔ የጠቅላላ ጉባዔውን ውሳኔ አይፃረርም ወይ? ለሚለው ጥያቄ፣ አቶ ኤልያስ ይህ የተወሰነው ከአቅም በላይ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በዚህ በአጭር ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት ተገቢ ሆኖ ያለመገኘቱን ያመለከቱት አቶ ኤልያስ፣ መጋቢት 2008 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ እንደገና መስከረም 2009 ዓ.ም. ሌላ ጠቅላላ ጉባዔ መጥራት ከወጪ አንፃርም የሚያስቸግር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ስለዚህ ጠቅላላ ጉባዔውንና ምርጫን መስከረም ላይ ማካሄዱ የተሻለ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤልያስ፣ ይህም ቢሆን ግን ጠቅላላ ጉባዔው በመጋቢት ወር ያልተካሄደበትን ምክንያትና የሚካሄድበትን ጊዜ የሚገልጽ መረጃ ለአባላት እንዲሰራጭ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱን ሰሞናዊ ውሳኔ የማይቀበሉ ያነጋገርናቸው አባላት ግን፣ አሁንም ንግድ ምክር ቤቱ ደንብና የጠቅላላ ጉባዔን ውሳኔ የጣሰ ተግባር ተፈጽሟል ብለው ያምናሉ፡፡
ሊካሄድ የሚገባው ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ አለመካሄዱ ደግሞ ለአንድ የምርጫ ዘመን እንዲያገለግሉ የተመረጡት አመራሮች ለተጨማሪ አንድ ዓመት በቦታው ላይ እንዲቆዩ ዕድል ለመስጠት የተፈለገ መሆኑን ያሳያል የሚል መከራከሪያም እያቀረቡ ነው፡፡ አሁን በተፈጠረው ክፍተት ጠቅላላ ጉባዔው ወደ መስከረም 2009 ዓ.ም. ከተሸጋገረ ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በፊት ያገለገሉበትን ጊዜ ሳይጨምር ከስድስት ወራት በላይ ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡
ጉዳዩን የበለጠ አነጋጋሪ የሚያደርገው ደግሞ ለንግድ ምክር ቤቱን ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ መታገድ ምክንያት የሆነው የሕግ ጥሰት መሆኑ እየታወቀ፣ አሁንም በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የሚነሳ ጉዳይ ቸል ብሎ የጠቅላላ ጉባዔውን የሥልጣን ዘመን ማራዘሙ ነው ተብሏል፡፡
በጠቅላላ ጉባዔውና ምርጫውን በተጠቀሰው ጊዜ ላለመከናወን የተሰጠውን ምክንያት የማይቀበሉ መሆናቸውን የገለጹ አንድ የንግድ ምክር ቤቱ አባል ደግሞ፣ በዚህ ወር መካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔ ላለመካሄዱ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መመርያን በምክንያትነት ማቅረቡ አሳማኝ ያለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡
እንደ አስተያየት ሰጪው ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት መመርያን ማክበሩ መልካም ቢሆንም፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ ንግድ ምክር ቤቱን የሚወክል አባል መላክ የሚችልበት ዕድል ስላለ የተሰጠውን ምክንያት መቀበል ይከብዳል ብለዋል፡፡