Saturday, December 9, 2023

ከታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎን ኢትዮጵያውያን የሚገነቡት ፖለቲካዊ ጉልበት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዛሬ አምስት ዓመት ፕሮጀክት ‹‹X›› በሚል ያልተለየ መጠሪያው የታወቀው፣ በሚያዚያ ወር 2003 ዓ.ም. የመሠረተ ድንጋዩ ሲጣል ‹‹የሚሊኒዬም ግድብ›› የተባለውና በመጨረሻም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚል መጠሪያን ያገኘው የዚህ ትውልድ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አሻራ ግንባታ ዘንድሮ አምስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

የታላቋ ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ በትውልድ ቅብብሎሽ መሸጋገር ያልቻለበት ሚስጥር ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ የሆነ ትልቅ የታሪክ ምርምርን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ የቀድሞውን ታላቅነት ለመመለስ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውያን በዓባይ ወንዝ ላይ የጀመሩትን ግድብ ‹‹የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ›› ብለው ሰይመውታል፡፡  

የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ አንድነት የሥልጣኔና የጉልበት ምንጭ እንደሆነው ሁሉ፣ የታላቋ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ኢትዮጵያውያንን በአንድነት እንዲያስተሳስር እንዲሁም ለዘመናት ካሳለፈችው በጦርነትና በእርስ በርስ ግጭት የታጀበ የድህነት ሕይወት መንቃቷን እንዲያውጅ መሆኑን፣ ስያሜው በተሰጠበት ወቅት የተሳተፉ ባለሥልጣናት የሚገልጹት ነው፡፡

በቅርቡ ከምሁራን ጋር ውይይት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡

የግድቡ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አካባቢ ደስታቸውንና ድጋፋቸውን ከመግለጽ ባለፈም በተግባር አሳይተዋል፡፡

በፖለቲካ ጭቆናዎች ተንገሽግሸው ከአገር የወጡ ኢትዮጵያውያን ሳይቀሩ፣ የፖለቲካ ልዩነታቸውን ትተው በወቅቱ ለፕሮጀክቱ ያላቸውን ድጋፍ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘበትን ቀን ግንቦት 20፣ እንዲሁም በምርጫ ወቅቶች ይህንን ፕሮጀክት ለፖለቲካ ዓላማ በዋለባቸው ወቅቶችም የአገር ውስጥ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ‹‹ፕሮጀክቱ የሕዝብ እንጂ የፓርቲ አይደለም›› በሚል ክርክራቸው፣ ገዥው ፓርቲ ከተግባሩ እንዲቆጠብ በማሳሰብ ድጋፋቸውን ለፕሮጀክቱ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ለፕሮጀክቱ ያላቸውን ድጋፍ በስሜት ብቻ ሳይሆን ባላቸው የገንዘብ አቅም ሁሉ አሳይተዋል፡፡ ሠራተኛው እስካሁን ድረስ ስምንት ቢሊዮን ብር ከአነስተኛ ወርኃዊ ደመወዙ ያዋጣ ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማት በበኩላቸው በተለምዶ የታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ቦንድ በሚል የሚታወቀውን የመንግሥት ሰነድ በመግዛት ላይ ናቸው፡፡

በእስካሁኑ ሒደትም በዚህ የገንዘብ መሰብሰቢያ መንገድ መንግሥት ከግል የመንግሥት ተቋማት ብቻ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ችሏል፡፡ ይህ ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለህዳሴው ግድብ የሚውል ነው ባይባልም፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያንን በዚህ መልኩ እያስተሳሰረ የአንድነታቸው ጉልበት ምን ያህል አቅም እንደሆነ እየመሰከረ ነው፡፡ ይህ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አወንታዊ ተፅዕኖ በአገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡

በግብፅ ላይ ያደራጀው ፖለቲካዊ ጉልበት

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ በተጣለበት ወቅት በግብፅ በኩል የተሰማው የጦርነት ማስፈራሪያ፣ በኢትዮጵያውያን ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ለፓርላማ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በግብፅ በኩል ስለሚሰነዘረው የጦርነት ማስፈራሪያ ተጠይቀው፣ ‹‹ዋናው አለመፍራት ነው›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን በዲፕሎማሲያዊ ዘመቻና በጠረጴዛ ዙሪያ ግብፅን የመርታት ግብ በመጣል እንደሚንቀሳቀሱ መግለጻቸው፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይህንን ፕሮጀክት በመወከል በያለበት አገር የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሠራ ኃላፊነት እንደተሰጠውም ገልጸው ነበር፡፡

በዚህ መሠረት የተንቀሳቀሰው ሕዝብና መንግሥትም፣ በወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት የነበሩትን መሐመድ ሙርሲ ‹‹አንድ ጠብታ የዓባይ ውኃ እንድትቀንስ አንፈቅድም›› ከሚለው የቴሌቪዥን ንግግራቸው ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ አስገድዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙርሲ ከላይ የተገለጸውን የተናገሩት፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት ውስጥ ታሪካዊ ክስተት ተደርጐ በሚቆጠረው የዓባይን ተፈጥሯዊ መስመር ለግንባታው ሲባል በተቀየሰበት ወቅት ነው፡፡

በዚህ ግድብ የግንባታ ሒደት ውስጥ ሁለተኛው ታሪካዊ ክስተት የሚባለው ግብፅና ሱዳንን በጠረጴዛ ዙሪያ አስቀምጦ እ.ኤ.አ. በማርች 2015 ላይ የመርህ መግለጫ ስምምነትን ያስፈረመው፣ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ድል ነው፡፡

በዚህ የስምምነት መገለጫ ላይ ግብፅና ሱዳኖች ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪካቸው ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ የመጠቀም መብቷን የተቀበሉበት፣ አጠቃቀሙም ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መርህ የሚለውን የኢትዮጵያ አቋም የተቀበለ ነው፡፡

ሪፖርተር በዚህ ስምምነት ዙሪያ ከወራት በፊት ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ‹‹ለዘመናት የቆየውን የበላይነት የለወጠ የፖለቲካ ጨዋታውን በኢትዮጵያ በኩል ያደረገ ነው፤›› በማለት ገልጸውታል፡፡ እንደ እሳቸው አባባል ‹‹ጌም ቼንጅ›› ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የግድቡን ማኅበራዊና አካባቢያዊ ተፅዕኖዎችን፣ እንዲሁም የኃይድሮ ሲሙሌሽን ሞዴልን ለማጥናት ሁለት የፈረንሣይ ኩባንያዎች ተመርጠው ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሦስተኛው ታሪካዊ ክስተት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሒደት ውስጥ ተፈጽሟል፡፡

ይኸውም የዓባይ ወንዝን ተፈጥሯዊ ካልሆነው መስመሩ ወደ ቀድሞው መስመሩ፣ ነገር ግን የግንባታው ክፍል ባረፈበትና አራቱ የውኃ መውረጃ ከልቨርቶች በተገጠሙበት የግንባታው ክፍል እንዲፈስ መደረጉ ነው፡፡

ይህንን ክስተት ታሪካዊ የሚያደርገው ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ ለደቂቃዎች ያህል ቢሆንም እንኳ የዓባይን ፍሰት መግታት የሚያስችላት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት ከተፈጠረ በኋላ በግብፃዊያን በኩል ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥና የመልካም ግንኙነት ፋይዳን ወደመቀበል፣ እንዲሁም ሌሎች የውኃ አማራጮችን እንዲያማትሩ ተገደዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በፌብርዋሪ 2015 ውስጥ በግብፅ ቴሌቪዥን ንግግር ያደረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ፣ ኢትዮጵያ በምትገነባው ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ ውኃ መያዝ ስትጀምር ሊፈጠር የሚችለውን የውኃ እጥረት ለማካካስ አማራጭ የውኃ ምንጮችን ለመጠጥነት ለማዋል የማጣሪያ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡

አህራም የተባለው የአገሪቱ ታዋቂ ጋዜጣ እ.ኤ.አ. ማርች 11 ቀን 2016 ዕትሙ ስለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ በርካታ የግብፅ ምሁራንን አስተያየት የያዘ ዘገባ አቅርቧል፡፡

በዚሁ ዘገባ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት አባልና በዓለም አቀፍ ሕጐች ላይ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አይማን ሰላሳ፣ ‹‹በማንኛውም ሁኔታ ግብፅ ከእንግዲህ የግድቡን ግንባታ ማስቆም የምትችልበት ሁኔታ የለም፤›› ብለዋል፡፡

ይኼው ዘገባ ግብፅ ከእንዲህ በታላቁ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ መከተል የሚገባት በሚል ንዑስ ርዕስ የተለያዩ ምሁራን አስተያየት አካቷል፡፡ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የግንባታና ዲዛይን ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር የሆኑት ሸሪን አል ባራዲ፣ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ የውኃ ሙሌት በግብፅ የእርሻ ወቅት እንዳታከናውን የሚያስችል ስምምነት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት ያቀደችው በሰባት ዓመት ውስጥ መሆኑን የሚጠቅሱት አል ባራዲ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ጊዜ እንድታራዝም ማሳመን እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ይህንኑ አስተያየትም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሸሪፍ እስማኤል የግድቡ ሙሌት ወደ 12 ዓመት ከፍ እንዲል፣ የአገሪቱ መንግሥት እየተደራደረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዳሴ ግድቡ ድርድር ውጪ የግብፅ መንግሥት ሌሎች የውኃ አማራጮችን እያማተረ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር በመሆን የቪክቶርያ ሐይቅን ከሜዲትራኒያን ባህር ጋር በማገናኘት የበለጠ ውኃ ወደ ናይል ተፋሰስ መግባት የሚችልበትን አኅጉራዊ ፕሮጀክት እየተጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጀርመን ዩኒቨርሲቲ የኃይድሮሎጂና የውኃ ማኔጅመንት ተመራማሪ የሆኑት ሃኒ ሰዊላም በበኩላቸው፣ የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ተጋሪ አገሮች በመተባበር የተቀናጀ ፕሮጀክት በጋራ ተግባራዊ ማድረግ መጀመር እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

በአንዱ አገር የኃይል ማመንጫ፣ በሌላው አገር የእርሻ ሥራ፣ በሌላው ደግሞ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ፕሮጀክቶችን በጋራ ተግባራዊ በማድረግ ውጤቱንም መጋራት መጀመር እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

በአጠቃላይ በግብፅ በኩል እየተያዘ የመጣው አዲስ አቋም፣ ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አማካይነት የገነባችውንና እየገነባች ያለውን ፖለቲካዊ ጉልበት የሚያሳይ ነው እየተባለ ነው፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -