Monday, July 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በተመሠረተባቸው ክስና በተፈቀደላቸው ዋስትና ላይ ብይን ለመስጠት ተቀጠሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– መታመማቸውንና የሚወስዱት መድኃኒት መርዝ እንደሆነባቸው ተናገሩ

የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ በባንክ የሚያዙበት በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ሳይኖራቸው ለስድስት ግለሰቦች በድምሩ ከ4.8 ሚሊዮን ብር በላይ ደረቅ ቼክ በመስጠት ወንጀል በተመሠረተባቸው ክስና በሥር ፍርድ ቤት ተፈቅዶላቸው በታገደው የዋስትና ጉዳይ ላይ ብይን ለመስጠት ለረቡዕና ለሐሙስ ተቀጠሩ፡፡

አቶ ኤርሚያስ በዘመን ባንክ በቂ ስንቅ (ገንዘብ) ሳይኖራቸው የግል ተበዳዮች ለተባሉት አቶ ፍጹም አስፋው 2,450,000 ብር፣ ለሳምራዊት ጴጥሮስ 822,900 ብር፣ ለጽጌረዳ አበበ 500,000 ብር፣ ለንጉሤ መንግሥቱ 500,000 ብር፣ ለሳዲቅ አብዱልዋህብ 255,534 ብር፣ እንዲሁም ለዶ/ር ኤርሚያስ ሀብቴ 343,400 ብር ደረቅ ቼክ መስጠታቸውን ገልጾ፣ ክስ የመሠረተው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡

መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ መጋቢት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግና ተከሳሽ ስለክሱ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሰጠው አስተያየት ተጠርጣሪው የተከሰሱበት ደረቅ ቼክ የማውጣት (መስጠት) ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም የተጠቀሰባቸው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 693(1)ን ማለትም ‹‹… በቂ ገንዘብ አለመኖሩን እያወቀ ቼክ ያወጣ (የሰጠ) ከሆነ፣ በቀላል እስራት ወይም እንደ ነገሩ ክብደት ከአሥር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፤›› የሚል በመሆኑ፣ አቶ ኤርሚያስ ላይ የቀረበው ክስ ተነቦላቸው የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡና በማረሚያ ቤት ሆነው ምስክሮቹን እንደ ክሱ እንዲያሰማ እንዲፈቀድለት ጠይቋል፡፡

የአቶ ኤርሚያስ ጠበቃ አቶ ሞላ ዘገዬ በበኩላቸው ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዱ፣ ‹‹ክሱን አይተነዋል፡፡ እንቃወማለን፡፡ የመጀመሪያ መቃወሚያ ለማቅረብ ጊዜ ያስፈልገናል፡፡ ዓቃቤ ሕግ እንደገለጹት ክሱ ዋስትና የሚያስከለክል አይደለም፡፡ እንደነዚህ ዓይነት የክስ ጉዳዮች ዋስትና አያስከለክሉም፡፡ የተጠቀሰውም የሕግ አንቀጽ አይከለክልም፡፡ ዋስትና የግለሰብ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ ልዩ የዜጎች መብት በመሆኑና ሊከለከል ስለማይገባ፣ አቶ ኤርሚያስ በዋስ ተለቀው ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ፤›› ሲሉ አመልክተዋል፡፡

አቶ ሞላ ዋስትናን በሚመለከት ጨምረው ሲያስረዱ ዋስትናን በሚመለከት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 63 ላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውጪ፣ ማንኛውም ዜጋ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ መስጠቱንም ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ አቶ ኤርሚያስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከእስር ቢለቀቁ ወደ ውጭ ከወጡ ሊመለሱ እንደማይችሉ የገለጸው ግምት መሆኑን ያስረዱት አቶ ሞላ፣ ሕገ መንግሥት የፈቀደው የማይጣስና የማይገረሰስ መብትን የተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ተጨባጭ ባልሆነ ነገር እየተሳበበ ሊከለከል እንደማይገባም አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ አቶ ኤርሚያስ ስለራሳቸው እንዲገልጹ ጠይቋቸው ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት መሆናቸውን፣ በእናትና በአባታቸው ቤት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ውስጥ እንደሚኖሩ፣ ሁለተኛ ዲግሪ እንዳላቸውና የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር የቦርድ አባል ሆነው እየሠሩ እያለ መታሰራቸውን አስረድተዋል፡፡

ነጭ ባርኔጣ፣ ረዘም ብሎ ነጣ ያለ ጃኬትና ጀለቢያ (ሽርጥ) ለብሰውና ጥቁር ነጠላ ጫማ ተጫምተው ችሎት የቀረቡት አቶ ኤርሚያስ፣ አንገታቸውና እግራቸው አካባቢ በቀይ ሰውነታቸው ላይ ሽፍታና ጥቁር ነጠብጣብ የሚታይ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ምን እንደሆኑ ጠይቋቸው፣ ዓይነቱን ባይናገሩም ሦስት ዓይነት ሕመሞች መታመማቸውንና የሚወስዱት መድኃኒት መርዝ እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ሕክምና እንዲያገኙና ከጠበቃዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ የክስ መቃወሚያ ለመቀበልና በዋስትና ጥያቄው ላይ ብይን ለመስጠት ለሐሙስ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ኤርሚያስን የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መርማሪ ቡድን ጠርጥሬያቸዋለሁ ባለው ከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ምርመራውን ሳያጠናቅቅ (ለ70 ቀናት ታስረው ከርመዋል)፣ የሥር ፍርድ ቤት በ500 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በመፍቀዱ ላይ ተቃውሞ አቅርቧል፡፡ ይግባኙ የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ሦስተኛ ወንጀል ችሎት የመርማሪ ቡድኑን አቤቱታ ካሰማ በኋላ፣ አቶ ኤርሚያስ በሌላ ክስ ለዋስትና ጉዳይ መቀጠራቸውን አስታውሶ በተቀጠሩበት የዋስትና ጉዳይ ቢፈቀድላቸው መርማሪ ቡድኑ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ጥያቄ ቢያቀርብም፣ መርማሪ ቡድኑ ‹‹ዋስትናውን እንቃወማለን፣ ምርመራ አልጨረስንም፣ ፍርድ ቤቱ የሥር ፍርድ ቤትን የምርመራ ሒደት ይመልከትልን፤›› በማለት 37 ገጽ ግልባጭ ማያያዙን አስረድቷል፡፡

የተጠርጣሪ ጠበቃ አቶ ሞላ የሥር ፍርድ ቤትን ክርክር እንደሚያውቁ በመግለጽ ግልባጭ እንደማያስፈልጋቸው በመናገራቸው፣ ፍርድ ቤቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለዓርብ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ እስከዚያው ድረስ የሥር ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና ፈቃድ ታግዶ እንዲቆይም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች