Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮምና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቴሌኮም ኢንጂነሪንግ ለማሠልጠን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮ ቴሌኮም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር፣ በሁለተኛ ዲግሪ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ ለማሠልጠን የሚያስችል ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ሁለቱ ተቋማት ይህን የትምህርት ሥርዓት በጋራ ለመሥራት ስምምነቱን የተፈራረሙት ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲሆን፣ በዕለቱም የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል፣ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትርና የኢትዮ ቴሌኮም የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መኩሪያ ኃይሌ፣ እንዲሁም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ተገኝተዋል፡፡

ለሦስት ዓመታት የሚቆየውን ስምምነት የተፈራረሙት ደግሞ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ ናቸው፡፡

በሁለቱ ተቋማት የጋራ ትብብር የሚካሄደው የቴሌኮሙዩኒኬሽን የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም በመጀመሪያው ዙር ከ50 እስከ 100 ለሚሆኑ የኢትዮ ቴሌኮም የኢንጂነሪንግ ሠራተኞች ዕድሉ እንደሚሰጥ፣ በቀጣይም ሒደቱ እየታየ ፕሮግራሙ ሌሎችን የሚያካትት እንደሚሆን በፊርማው ሥነ ሥርዓት ወቅት ይፋ ተደርጓል፡፡

በዚህም መሠረት በመጀመሪያው ምዕራፍ የሚሠለጥኑት 50 የኢትዮ ቴሌኮም ኢንጂነሪንግ ሠልጣኝ ሠራተኞች ወደ ሥልጠና እንደሚገቡ ተገልጿል፡፡

‹‹ይህ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ የትምህርት ፕሮግራም የውል ስምምነት በዘርፉ ደረጃውን የጠበቀ የሰው ኃይል ለማፍራትና በአገራችን ከፍተኛ እመርታ እያሳየ ያለውን የቴሌኮም ዘርፍ ዘላቂ ዕድገት የሚያረጋገጥ ይሆናል ተብሎ ይታመናል፤›› በማለት አቶ አንዱዓለም በወቅቱ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለይም በቴሌኮም ዘርፍ በአገሪቱ የሚታየውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ክፍተትም የሚቀርፍ እንደሚሆንም አክለው አስረድተዋል፡፡

በሁለቱ ተቋማት ትብብር አማካይነት የሚሰጠው የትምህርት ፕሮግራም በሁለት የሙያ መስኮች (Specialization) የሚሰጥ ሲሆን፣ እነሱም የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ የትምህርት ዘርፎች ናቸው፡፡

በቴሌኮሙዩኒኬሽን ኔትወርክ ኢንጂነሪንግ የትምህርት ዘርፍ የሚሰጡት ትምህርቶች ተማሪዎች ባለገመድና ገመድ አልባ ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ የንድፈ ሐሳብ፣ የትንተና፣ የዲዛይንና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ሲስተሞችን ሞዴሊንግ ሥራ የሚያካትቱ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት ተማሪዎች በትምህርታቸው ማጠናቀቂያ ወቅት ዲዛይን የማድረግ፣ አመራር የመስጠትና ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴሌኮም ኔትወርኮችን ለማስተዳደር፣ እንዲሁም በቴሌኮም ኢንዱስትሪ የሚኖሩ ለውጦችን ቀድመው እንዲመለከቱና ዝግጁ እንዲሆኑ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በተመሳሳይ በቴሌኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ሲስተምስ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ የትንተና፣ የዲዛይን፣ የጥገናና የቴሌኮም ኢንፎርሜሽን ሲስተምን ማስተዳደርና ደኅንነቱን መጠበቅ የሚያካትት ነው፡፡ የትምህርት ኮርሶቹ በቴሌኮም ኢንፎርሜሽን ሲስተም ቀረፁ፣ ግንባታና አስተዳደር የተካተተ መጪውን የቴሌኮም ዕድገት ሒደት መተንበይ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችሉ እንደሆነም፣ እንዲሁ በፊርማው ሥነ ሥርዓት ወቅት ተገልጿል፡፡

‹‹በአጠቃላይ በሁለቱ ተቋማት አማካይነት የተከናወነው ስምምነት በአሁኑ ወቅት በዘርፉ የሚታየውን የተማረ የሰው ኃይል ጥራት በዘላቂነት ለመፍታት ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን፣ በተለይም የተማረ የሰው ኃይል ከውጭ በማስመጣትና በአገራችን ልጆች በመታገዝ ዕድገታችንን እንድናሳይና ለታቀደው አገራዊ ውጥን የራሱን አስተዋጽኦ የሚጫወት ይሆናል፤›› በማለት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም ከስምምነቱ የሚጠበቀውን ትሩፋት ገልጸዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች