የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በማዕከልና በክፍላተ ከተሞች ዕርምጃ የወሰደባቸውን 672 የመሬት ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ለመተካት ቅጥር ጀመረ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት አምስት ሳምንታት በወሰደው ዕርምጃ፣ አብዛኛዎቹ ክፍላተ ከተሞች በርካታ የሰው ኃይል ስላጡና በምትካቸው አመራርም ሆነ ባለሙያ ባለመተካቱ ኅብረተሰቡ እየተጉላላ መሆኑ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተተኪ ሠራተኞች ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድረው ያለፉትን ከመጋቢት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መቅጠር ጀምሯል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመልካም አስተዳደርና የሲቪል ሰርቪስ ክላስተር አስተባባሪና የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይስሃቅ ግርማይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕርምጃ በተወሰደባቸው ምትክ ከሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ቅጥር ተጀምሯል፡፡ የሰው ኃይል ቅጥሩ በሚቀጥሉት ሰባት ቀናት ተጠናቆ ወደ ሥልጠና እንደሚገባና ክፍተቱ እንደሚሞላ አቶ ይስሃቅ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎች በተለይ በይዞታ፣ በሰነድ አልባ፣ በመሬት ሊዝና በተለያዩ የመሬት ጉዳዮች አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን እየገለጹ ነው፡፡ በርካታ ነዋሪዎች የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት ክፍለ ከተሞችን ቢጎበኙም፣ በተነሱት ምትክ ሌሎች አመራሮችና ባለሙያዎች ባለመተካታቸው እየተጉላሉ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡
‹‹አንዳንድ ቢሮዎች አገልግሎት የሚሰጡ ሠራተኞች ቢኖራቸውም ረጃጅም ሠልፎች እየታዩባቸው ነው፡፡ ሌሎቹ ቢሮዎች ደግሞ አገልግሎት የሚሰጥ የሰው ኃይል ስላልተመደበላቸው በበርካታ ነዋሪዎች ላይ መጉላላትን ፈጥሯል፤›› በማለት በቦሌ ክፍለ ከተማ በመሬት ይዞታ ዘርፍ ለመስተናገድ የሄዱት አቶ አበበ ሁንዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
መልካም አስተዳደር ለማስፈንና ሙስናን ለመዋጋት ተብሎ በተወሰደው ዕርምጃ፣ በማዕከልም ሆነ በክፍላተ ከተሞች ላለፉት አምስት ሳምንታት ክፍት በሆነ መዋቅሮች እስካሁን የሰው ኃይል አልተተካም፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን በነባር አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ ዕርምጃ ሲወሰድ በተመሳሳይ ወቅት ስለተተኪዎች ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ጉዳይ አብሮ ባለመታሰቡ በርካታ ነዋሪዎች በየዕለቱ እየተጉላሉ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከነዋሪዎች ጋር እያካሄደ በሚገኘው ውይይት፣ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በመሬት ዘርፍ የተወሰዱት ዕርምጃዎች በመልካም ጎኑ የሚታዩ ቢሆንም፣ አሁንም ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡ አካላት አሉ፡፡ ከዚህም ባለፈ ስለተተኪዎች አብዝቶ መጨነቅ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ በአጠቃላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መልካም አስተዳደር ለማስፈን የጀመራቸው ሥራዎች መልካም ጅማሬ መሆናቸውን፣ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ግን በሥልጣን ዘመናቸው መልካም ሥራ ሠርተው ማለፍ እንዳለባቸው በነዋሪዎች ተጠይቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመሬት ዘርፍ በተጨማሪ 595 የፖሊስ አባላት ላይ ዕርምጃ ወስዷል፡፡ ከእነዚህ የፖሊስ አባላት ውስጥ 80 የሚሆኑት ከአባልነት የተሰናበቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ከገንዘብ ቅጣት እስከ ማዕረግ ማንሳት የሚደርስ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ታውቋል፡፡ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ ቀጣይነት እንዳለው አቶ ይስሃቅ አረጋግጠዋል፡፡