Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊውጭ አገር ሊሄዱ ሲሉ በስህተት ተይዘው ታስረው የነበሩት ሹም ተለቀቁ

ውጭ አገር ሊሄዱ ሲሉ በስህተት ተይዘው ታስረው የነበሩት ሹም ተለቀቁ

ቀን:

– ስህተቱ የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ነው ተብሏል

የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግንባታ ዘርፍ ማስተባበሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ በስህተት ታስረው አንድ ቀን ካደሩ በኋላ ተፈቱ፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ተክሉ ፍቅሩ መጋቢት 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ለ18 አጥቢያ ወደ ግሪክ ለመሄድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ ፓስፖርታቸውን ለኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምርያ ሰጥተው ወደ ውስጥ ለማለፍ ሲጠባበቁ፣ መታገዳቸው ተነግሯቸው ለብቻቸው እንዲሆኑ መደረጋቸው ታውቋል፡፡

- Advertisement -

የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የግንባታ ዘርፍ ማስተባበሪያ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ግራ እንደተጋቡ፣ የቀረውን የሌሊት ክፍለ ጊዜ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አድረው በነጋታው እሑድ መጋቢት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. በምን ጥፋት እንደታገዱ ሲጠይቁ፣ ከአገር እንዳይወጡ ያሳገዳቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መሆኑ እንደተነገራቸው ታውቋል፡፡

ቀኑ እሑድ በመሆኑ በምን ምክንያት እንደታገዱ መጠየቅ ያልቻሉት አቶ ተክሉ አዳራቸውን በመምርያው ለማድረግ ተገደዋል፡፡ መጋቢት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአገር እንዳይዋጡ ዕግድ ያስጣለባቸው ፀረ ኮሚሽን ሲጠየቅ፣ በ2006 ዓ.ም. ከአቶ ተክሉ መሥሪያ ቤት በሙስና የተጠረጠሩ ኃላፊዎች ሲከሰሱ የሳቸውም ስም ወደ ተቋሙ ተልኮ እንደነበር፣ የተከሰሱት ከአገር እንዳይወጡ ዕግድ ሲጣል ስማቸው አብሮ መላኩን መግለጹን አቶ ተክሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አቶ ተክሉ በወቅቱ ስማቸው የተላከ ቢሆንም፣ የማይፈለጉ መሆኑን አረጋጋጦ ማሰረዝ (ማስነሳት) ሲገባው ዝም ብሎ ከሁለት ዓመታት በላይ ማቆየቱ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

አቶ ተክሉ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የተያዙት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ከግሪክ አቻው ጋር በውኃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ላለው ትምህርታዊ የልምድ ልውውጥ ለመሄድ ሲሉ ነው፡፡

የልምድ ልውውጡን ለመካፈል ወደ ግሪክ የሚሄዱት አቶ ተክሉን ጨምሮ አምስት አባላት ያሉትና በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ የሚመራ ቡድን የነበረ ቢሆንም፣ ኮሚሽኑ ፈጠረው በተባለ ስህተት ምክንያት አቶ ተክሉ ሳይሄዱ ቀርተዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከግሪክ ውኃና ፍሳሽ መሥሪያ ቤት ጋር ትምህርታዊ ሥልጠናና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ዕድሉን በማግኘቱ፣ ለልዑኩ የአውሮፕላን ትኬትና ሌሎች ወጪዎችን ወጪ ማድረጉ ታውቋል፡፡ ከፍተኛ እምነት የተጣለባቸውና የልምድ ልውውጡን በመካፈል ለባለሥልጣኑ የአሠራር መሻሻልና ለውጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ የታመነባቸው አቶ ተክሉ፣ በፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የግዴለሽነት አሠራር ሊጨናገፍ መቻሉ አሳዛኝ መሆኑን፣ የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የሥራ ባልደረቦች ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አዲስ በተረቀቀውና ለፓርላማ በቀረበው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ፣ የመመርመርና የመክሰስ ሥልጣኑ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንደሚሰጥበት በቅርቡ የተገለጸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በአቶ ተክሉ ፍቅሩ ላይ ፈጽሞታል ስለተባለው ስህተት ማብራሪያ እንዲሰጥ ሪፖርተር ለማግኘትና ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ አንድ ተጠርጣሪ በተጠረጠረበት ወንጀል ፍርድ ቤት ቀርቦ በሚደረግ ክርክር፣ የዋስትና መብቱ ተከብሮ በውጭ ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ሲፈቀድለት፣ እንደየጉዳዩ ክብደት ከአገር እንዳይወጣ ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እንዲጻፍ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚሰጥ ቢሆንም፣ አቶ ተክሉ በወንጀል ተጠርጥረው ሳይከሰሱ፣ ምርመራ ሳይጣራባቸውና ሳይታሰሩ ከአገር እንዳይወጡ መታገዳቸው ከማስገረምም ባለፈ፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥር መሆኑን አስተያየት የሰጡ የሕግ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...