የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በሥራ ላይ ላሉና ለተሰናበቱ ስምንት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የአምባሳደርነትን ሹመት ሰጡ፡፡
የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው በቅርቡ ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነታቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት አቶ ያለው አባተ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ዮናስ ዮሴፍ፣ እንዲሁም አቶ እሸቱ ደሴና አቶ አዛናው ታደሰ ናቸው፡፡
የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ስምንቱም ተሿሚዎች ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደሮች በመሆን ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች እንደሚወክሉ አስታውቋል፡፡ በተለያዩ ኃላፊነቶች በመንግሥት ሥራ ላይ የቆዩት ተሿሚዎቹ፣ በየትኛው አገር ኢትዮጵያን እንደሚወክሉ ግን ማብራሪያ አልተሰጠም፡፡