Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከታሪክ የማይማር ታሪክን ለመድገም ይገደዳል!

  ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት ላይ በመመሥረት በቅንነት፣ በድፍረትና በወሳኝነት ከ100 ቀናት በላይ የዘለቀው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አመራር፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ከፍተኛ አመኔታና ከበሬታ አግኝቷል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችም ኢትዮጵያውያን ይህንኑ ስሜታቸውን እየገለጹ ነው፡፡ ወትሮም በቀርፋፋነቱ የሚታወቀውን የመንግሥት ቢሮክራሲ ኋላ ቀር አሠራር ከሥር መሠረቱ በመናድ፣ የብርሃን ፍጥነት በሚያስብል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሰዱ ወሳኝ ዕርምጃዎች የብዙዎችን ቀልብ ገዝተዋል፡፡ እነዚህ ወሳኝ የሆኑ ዕርምጃዎች ከአገር ውስጥ አልፈው ዓለም አቀፉን ማኅብረሰብ አስደምመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለሦስት ዓመታት ያህል ገብታበት ከነበረው የቀውስ አረንቋ ውስጥ ወጥታ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑ፣ ከኤርትራ ጋር ለሃያ ዓመታት የዘለቀው የመረረ ጠላትነት ወደ መቀራረብና መተባበር እየተለወጠ መሆኑ፣ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ አመርቂ እንቅስቃሴዎች መስተዋላቸውና የመሳሰሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር መልካም ጅምሮች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ፡፡ እነዚህ ለአገር የሚጠቅሙ መልካም ነገሮች ከእጅ እንዳያመልጡ ግን ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ የኢትዮጵያ የዘመናት ታሪክም የጥንቃቄን አስፈላጊነት አበክሮ ያስገነዝባል፡፡

  ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት አደጋ ውስጥ ተፍጨርጭራ እንድትወጣ ከፍተኛ ጥረቶች በሚደረጉበት በዚህ ወቅት፣ በተለያዩ አካባቢዎች እያጋጠሙ ያሉ አለመረጋጋቶች ያሳስባሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ለውጡን በጋራ ተቀብለው አገራቸውን ወደ ከፍታው ማማ ለማድረስ ቃል እየገቡና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፋቸውን እየሰጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡ እንዲከናወን ከሚፈለግበት መንገድ ውጪ በስሜታዊነት ጥፋቶች ይፈጸማሉ፡፡ እዚህም እዚያም እያጋጠሙ ያሉ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች፣ ለውጡን ከማጨናገፍ የዘለለ ፋይዳ እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡ ችግሮች ቢያጋጥሙ እንኳን በሰከነ መንገድ እየተነጋገሩ መፍታት ሲገባ ለሰው ሕይወት ሕልፈት፣ ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት መጋለጥ የተጀመረውን ለውጥ ከማኮላሸት ውጪ ፋይዳ የለውም፡፡ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ያጋጠሙዋትን መልካም አጋጣሚዎች ያጣችው ከስህተት መማር ባለመቻሉ ነው፡፡ የ1966 ዓ.ም. ሕዝባዊ አብዮት ተጠልፎ ወታደሩ እጅ የገባው በወቅቱ ስክነት በመጥፋቱ ነው፡፡ ያ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ደም የፈሰሰው ስሜት ምክንያትን በማሸነፉ ነው፡፡ ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ ያጋጠሙ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ከስህተት ለመማር ፈቃደኝነት በመጥፋቱ ነው፡፡ ከበቀል ወደ በቀል የተደረገው አጉል ሽግግር ያተረፈው ጥፋት ነው፡፡ እጅ ውስጥ የገባን ዕድል ማባከን ከታሪክ አለመማርን ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝብና አገር ተጎድተዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም ነገር በላይ የሚወዳት እናት አገሩን ህልውና በምንም መደራደር አይፈልግም፡፡ አገሩ ካለችበት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፅኑ ችግር ተላቃ ዴሞክራሲያዊትና የበለፀገች እንድትሆን የፀና ፍላጎት አለው፡፡ ይህ መሠረታዊና ሊታለፍ የማይገባው ፍላጎት በጥቃቅን ምክንያት በሚነሱ ሁከቶችና ግጭቶች መጨናገፍ የለበትም፡፡ ማንኛውም ጥያቄ ያለው አካል በመጀመርያ የሕዝብን ፍላጎት ያክብር፡፡ በመቀጠል ለሐሳብ ነፃነት የሚጮሁ ወገኖች የአንድ ግለሰብ መብት ሲጣስ እያዩ እንዳላዩ አይሁኑ፡፡ የተጀመረው መሠረታዊ ለውጥ ለስኬት መብቃት የሚችለው፣ የሁሉም ዜጎች መብት ሳይሸራረፍ ሲከበር መሆኑን ግንዛቤ ይያዝ፡፡ ለውጡ ሰላም ማስፈን ካስቻለ ሰላምን የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን ማስወገድ ይገባል፡፡ ትናንት የተፈጸሙ ጥፋቶች በሕግ እንዲዳኙ ማድረግ ሲገባ፣ የጎዳና ላይ ፍትሕ ፍለጋ መሯሯጥ አገርን ችግር ውስጥ ይከታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የይቅርታና የፍቅር እጅ ዘርግተው ለውጡን እናስቀጥል ሲሉ ድጋፉን የሰጠ ሕዝብ፣ በጎን የአመፃ መንገድ እየተመረጠ ሁከት ሲቀሰቀስ ይቆጣል፡፡ አገርን ቀውስ ውስጥ የሚከት ችግር በየቦታው ሲቀፈቀፍ ከታሪክ እንማር ይላል፡፡ ከታሪክ አለመማር ወደ ውድቀት ያንደረድራል፡፡

  መሰንበቻውን በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የተስተዋሉ ድርጊቶች ማስተዋል የጎደላቸው ለመሆኑ ከአካባቢዎቹ የወጡት መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ በጨፌ ኦሮሚያ (በኦሮሚያ ምክር ቤት) ባደረጉት ንግግር፣ በምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ድርጊት በማውገዝ ሰላም እንዲሰፍን በአጽንኦት ጠይቀዋል፡፡ ይህ ጊዜ እንዲመጣ የተከፈለውን መስዋዕትነት በማስታወስ፣ የሕዝቡን ሰላም ማወክ እንደማይገባ አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት ችግሩን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከብዶት እንዳልሆነና የሕዝብን ሰላም፣ የአገሪቱን ፀጥታ ማስፈንና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ኃላፊነቱ መሆኑን፣ ነገር ግን ኃይል በመጠቀም ወደ አላስፈላጊ ሁኔታ እንዳይገባ ችግሮች ሰላማዊ መፍትሔ ቢያገኙ ተመራጭ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም ለክልሉ ሰላም መደፍረስ ማንኛውም የውጭ ኃይል ምክንያት መሆን እንደማይችል ገልጸው፣ ክልሉን ለማመስ የሚደረገው ጥረት ግን ራስን በራስ እንደ ማጥፋት ይቆጠራል ብለዋል፡፡ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የሚሳካው ሰላምን በማደፍረስ ሳይሆን በሰከነ መንገድ ሰላም ማስፈን እንደሚገባ፣ በተዘጋጀው ሜዳ በእኩልነት መጫወት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመው፣ የሰላም መደፍረስን በተመለከተ ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ የሁለቱም ፕሬዚዳንቶች ማሳሰቢያ ለውጡ ስኬታማ መሆን የሚችለው ሰላምን በማስፈን እንጂ፣ ሁከት ቀስቅሶ እርስ በርስ በመባላት እንዳልሆነ ይጠቁማል፡፡ አጥፊዎች ሲያጋጥሙ እንኳ ወደ ሕግ ማቅረብ እንጂ፣ የኃይል ዕርምጃ መውሰድ አግባብ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚናገረውም ወርቃማ ዕድሎች ያመለጡት ስክነት እየጠፋ ስሜታዊነት የበላይነት በመያዙ ነው፡፡

  በየትኞቹም በችግር ውስጥ ባለፉ አገሮች የተስፋ ጭላንጭሎች ሲገኙ የተደበላለቁ ስሜቶች ይፈጠራሉ፡፡ በአንድ በኩል ጨቋኞች መንበራቸውን ላለመልቀቅ ሲፍጨረጨሩ፣ በሌላ ወገን ተጨቋኞች ለመበቀል ይነሳሉ፡፡ የሕግ የበላይነት በሌለበት ደግሞ ዳኝነቱ የሚያምፁት እጅ ላይ ይወድቅና ከበፊቱ ያልተናነሰ የሕግ ጥሰት ይፈጸማል፡፡ በብዙ አገሮች እንዲህ ያለው ሁነት በማጋጠሙ ለደም መፋሰስና ለአገር ውድመት የሚያጋልጡ ክስተቶች አገር አተራምሰዋል፡፡ በኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ አሁን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩት የለውጥ ጉዞ ስህተትን ላለመድገም በጣም የተጠነቀቀ፣ የአገሪቱን ያለፉ ዘመናት የታሪክ ውጣ ውረዶች በማገናዘብ ሰላማዊ መንገድ የመረጠ፣ ፍቅርና ይቅርታን በማስቀደም ኢትዮጵያውያንን በአንድነት ለማስተሳሰር ‹‹መደመር›› የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ የዓላማው መሪ ቃል ያደረገና ከአገር አልፎ ምሥራቅ አፍሪካን የሚያካልል ራዕይ የሰነቀ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ ይህ ወርቃማ ሐሳብ ደግሞ የሚሊዮኖችን ድጋፍና ይሁንታ ከማግኘቱም በላይ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወድማማች ሕዝቦችን ከዓመታት መለያየት በኋላ ማገናኘት እየጀመረ ነው፡፡ እኛ ልዩነቶቻችንን ይዘን ለጋራ አገራችን አንድ ላይ መቆም ካልቻልን ግን ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ እኛ እርስ በርስ ሳንስማማ ከማንም ጋር በሰላም መኖር እንደማንችል ሊታወቅ ይገባል፡፡ ታሪክን የኋልዮሽ ማየትም ብዙ ያስተምራል፡፡

  በአጠቃላይ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጎዳና በስኬት መጓዝ እንዲችል የመላ ልጆቿ ርብርብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ርብርብ ከስሜታዊነት ርቆ በምክንያታዊነት መመራት አለበት፡፡ ወጣቱ ትውልድ ከስሜታዊነት ይልቅ በምክንያታዊነት እንዲመራ ዕገዛ ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያልተጣሩ መረጃዎች ሲሠራጩ ለምን? መቼ? የት? እንዴትና የመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ማንሳት ከተቻለ ስህተት የመፈጸም ዕድል ይቀንሳል፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶችንና ዓላማዎችን ያነገቡ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያም ሆነ በተለያዩ ዘዴዎች የተዛቡ መረጃዎችን በማሠራጨት ስሜትን ሊጎዱ ስለሚችሉ፣ ወጣቶችም ስሜታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ግብታዊ ዕርምጃዎችን ስለሚወስዱ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በስህተት በሚወሰዱ ዕርምጃዎች በሚደርሱ አደጋዎች ምክንያት ፀፀት የሚከተለው፣ ከወዲሁ ለእያንዳንዱ ድርጊት ጥንቃቄ ሲጎድል ነው፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ በስህተት ወይም በቸልተኝነት ምክንያት በተፈጸሙ ድርጊቶች ብዙ ተጎድታለች፡፡ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን አጥታለች፡፡ ታሪክን የኋሊት በቅጡ መመልከት ባለመቻሉም በርካቶች ለሞት፣ ለስቃይ፣ ለስደትና ለእንግልት ተዳርገዋል፡፡ በዚህ ዘመን ሊበቃ ይገባል፡፡ ከታሪክ የማይማር ታሪክን ለመድገም ይገደዳልና!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰሜኑ ጦርነት የተበላሹ ብድሮች ከባንኮች የፋይናንስ ሪፖርት ላይ አይነሱም ተባለ

  ልማት ባንክ አሥር ቢሊዮን ብር ታማሚ ብድር እንዲነሳለት ጠይቋል የኢትዮጵያ...

  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ዩክሬንን እንዲጎበኙ ጥያቄ ቀረበ

  በመካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ ከአቶ ደመቀ መኮንን...

  ለውጭ ባንኮች የፀደቀው ፖሊሲ ብዥታ እንደፈጠረበት የመድን ሰጪዎች ማኅበር ገለጸ

  የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ በቅርቡ ያፀደቀው የፖሊሲ...

  ባለሦስትና አራት እግር ተሽከርካሪዎች የሚመሩበት የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው

  በአዲስ አበባ ከተማ የአሠራር መመርያ ሳይዘጋጅላቸው በኅብረት ሥራ በመደራጀት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...