በአገሪቱ በሥራ ላይ ከሚገኙ የግል ባንኮች አንዱ የሆነው አዋሽ ባንክ፣ በ2010 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.96 ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ታወቀ፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ያስመዘገበው የትርፍ መጠን ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡ ባንኩ በአንድ ዓመት ልዩነት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የትርፍ ዕድገት ያስመዘገበበት ውጤት፣ አሁንም ከግል ባንኮች በትርፍ መጠን ዕድገት የመጀመርያውን ደረጃ ይዞ እንዲቀጥል አስችሎታል፡፡
ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ በኋላ የመጀመርያው የግል ባንክ በመሆን ሥራ የጀመረው አዋሽ ባንክ፣ ባለፈው ዓመት ከታክስና ሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.44 ቢሊዮን ብር ማትረፉ ይታወሳል፡፡ በ2010 የሒሳብ ዓመትም ይህንን የትርፍ መጠን ዕድገት በማስቀጠል የትርፍ መጠኑን በ35 በመቶ አሳድጓል፡፡
የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ደግሞ በ13 ቢሊዮን ብር በመጨመር በ2010 የሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ፣ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 45.7 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት 32.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ይህ የተቀማጭ የገንዘብ መጠን በ39.5 በመቶ ማደጉ ተመልክቷል፡፡ ይህ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በዕድገቱም ሆነ በደረሰበት ደረጃ ከግል ባንኮች በከፍተኛነቱ የተመዘገበ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ የሰጠው የብድር መጠንም ወደ 31.2 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ በ2009 ሒሳብ ዓመት 22.6 ቢሊዮን ብር ብድር መስጠቱ ሲታወስ፣ የአሁኑ ግን በ8.6 ቢሊዮን ብር ወይም በ38 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ባንኩ እመርታ ያሳየበት ሌላው ዕድገቱ ደግሞ የሀብት መጠኑን በ36 በመቶ ማሳደጉ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በ2010 ሒሳብ ዓመት የባንኩ ጠቅላላ ሀብት 57.8 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡
አዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል መጠኑ ሦስት ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ቅርንጫፎቹንም ወደ 366 አድርሷል፡፡ በአንድ ዓመት የከፈታቸው ቅርንጫፎች 50 መሆናቸው ተገልጿል፡፡