Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበቤቶች ኮርፖሬሽን መጋዘኖች የታጎረው የኤርትራዊያን ንብረት ባለቤቶቹን እየጠበቀ ነው

በቤቶች ኮርፖሬሽን መጋዘኖች የታጎረው የኤርትራዊያን ንብረት ባለቤቶቹን እየጠበቀ ነው

ቀን:

ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ወደ አውቶብስ ተራ (መርካቶ) መንገድ በስተቀኝ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በቀድሞ ወረዳ 01 ቀበሌ 01 ጨው በረንዳ አካባቢ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ይዞታ የሆኑ መንታ መጋዘኖች ከኢትዮጵያ በጦርነቱ ጊዜ የተባረሩ ኤርትራውያን ንብረቶችን እስካሁን ድረስ ይዘው ቆይተዋል፡፡

ሲመንስ ጨው በረንዳ በሚሰኝ ልዩ ስም የሚታወቁት መጋዘኖች ላለፉት ሃያ ዓመታት ያህል ለኮርፖሬሽኑ ምንም ዓይነት ገቢ አላስገቡም፡፡ አካባቢው ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግበት በመሆኑ በወር እስከ 500 ሺሕ ብር ድረስ ሊከራዩ የሚችሉ መጋዘኖች የተሞሉት በኤርትራዊያን ንብረቶች ነው፡፡

እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው መጋዘኖች ቢያንስ በ19 መጋዘኖች የኤርትራዊያን ልዩ ልዩ የቤት፣ የቢሮ፣ የንግድ፣ የፋብሪካ ምርቶችና ተሽከርካሪዎች ተሞልተው ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ መጋዘኖች ውስጥ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር የነበሩት ኃይሌ መንቆርዮስና የኤምባሲው ንብረቶች፣ እንዲሁም የ54 ኤርትራዊያን ንብረቶች ታጭቀዋል፡፡

ከሃያ ዓመታት በፊት ከወዳጅነት በላይ ግንኙነት በነበራቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በድንበር ምክንያት ከፍተኛ ጦርነት መካሄዱ ይታወሳል፡፡ በጦርነቱ ማግሥት ሁለቱም አገሮች አንዱ የአንዱን አገር ዜጋ አባረዋል፡፡ በዚህ ወቅት በተለይ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን (የቀድሞው የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት) ቤቶችን ተከራይተው ይኖሩ፣ ይነግዱና ያመርቱ የነበሩ ኤርትራዊያን አገር ለቀው መውጣት ሲጀምሩ ኮርፖሬሽኑ የኤርትራዊያኑን ዕቃ እየሰበሰበ በመጋዘኖቹ አስቀምጧል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከአገር የወጡ ኤርትራዊያንን ንብረት ላለፉት ሃያ ዓመታት ጠብቆ በሥርዓት አስቀምጧል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች የኤርትራዊያን ንብረት የሆኑ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖች፣ አልባሳት፣ አልጋዎች፣ መጠጦች፣ የተለያዩ የቢሮ ዕቃዎችና ቁሳቁሶች ይገኛሉ፡፡ የአምባሳደር ኃይሌ ዕቃዎችም ከእነዚህ ዕቃዎች ጋር በመጋዘኖቹ ውስጥ አሉ፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኑ ሕጋዊ ሆኖ ለቀረበ ባለቤት ዕቃዎችን የሚያስረክብ መሆኑን፣ በቅርቡም ትክክለኛ የንብረት ባለቤት ለሆኑ ግለሰብ የተለያዩ ዕቃዎች፣ ወርቆችና ጥሬ ገንዘብ ጭምር አስረክቧል፤›› ሲሉ የኮርፖሬሽኑ የመጋዘኖች ኃላፊ አቶ አንበሳው ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኤርትራዊያንን ንብረት ብቻ በመጠበቅ አልተወሰነም፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በኤርትራ ይፋዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል ሁለቱም የዘጓቸውን ኤምባሲዎች መክፈትን ያጠቃልላል፡፡

ኤርትራ በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ አካባቢ በግምት 6‚000 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ኤምባሲ ነበራት፡፡

በሁለቱ አገሮች አለመግባባት በተከሰተው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት ሁለቱም አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን መዝጋታቸው አይዘነጋም፡፡

ኤርትራ ትጠቀምበት የነበረውና በይፋ የተከፈተው የኤምባሲ ሕንፃ ታዋቂው ግሪካዊው ነጋዴ ኤልያስ ፓፓሊኖስ በ1950ዎቹ የገነቡት ነው፡፡ ይህ ሕንፃ በደርግ ዘመን በአዋጅ ቁጥር 26/1967 ዓ.ም. ተወርሷል፡፡ ከዚያ በኋላ የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማኀበር (አኢወማ) ይገለገልበት የነበረ ሲሆን፣ ከወታደራዊው መንግሥት ውድቀት በኋላ ደግሞ የኤርትራ ኤምባሲ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡

የኤርትራ ኤምባሲ ከተዘጋ በኋላ ላለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡

በመጨረሻ ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን እንደገና እያደሱ በመሆናቸው፣ የወጣቶች ፌዴሬሽን በማስለቀቅ በድጋሚ ለኤርትራ ለመስጠት ሰፊ እንቅስቃሴ ሲደረግ ሰንብቷል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ካለፈው ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ ዳዋ የለበሰውን  ምድረ ግቢ በማፅዳት ሥራ ላይ የከረመ ሲሆን፣ ሥራውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ሲከታተሉ ነበር፡፡

ከሕንፃ ፅዳት፣ ከቀለም ቅብና ከግቢ ማስዋብ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የሰላም አየር መንፈስ በመጀመሩ፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ኤርትራዊያን ዕቃዎቻቸውን ከኮርፖሬሽኑ ማግኘት ይችላሉ ሲል ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...