በኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጦርነት ምክንያት ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የአየር ክልል ዓርብ ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በከፊል ተከፈተ፡፡
ከግንቦት 5 ቀን 1990 ዓ.ም. ጀምሮ የሁለቱ አገሮች አዋሳኝ የአየር ክልል ለማንኛውም የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከሐምሌ 1 ቀን እስከ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በኤርትራ ባደረጉት ጉብኝት፣ ሁለቱ አገሮች ከፈረሙዋቸው በርካታ ስምምነቶች መካከል የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ትብብር ስምምነት በዋነኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሃያ ዓመታት ያቋረጠውን የአስመራ በረራ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በቦይንግ 787 ድሪምላይነር ዘመናዊ አውሮፕላን ለመጀመር ዝግጀቱን እንዳጠናቀቀ አስታውቋል፡፡
አየር መንገዱ ወደ አስመራ በረራውን ለመጀመር ላለፉት ሃያ ዓመታት የተዘጋው የኢትዮጵያ ኤርትራ የአየር ክልል እንዲከፈትለት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ለኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንም ለዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ደብዳቤ በመጻፍ የተዘጋው የአየር ክልል እንዲከፈት ጠይቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ወሰንየለህ ሁነኛው (ኮሌኔል) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር ውይይት ከተካሄደ በኋላ ከስምምነት ላይ በመደረሱ አዲስ አበባን ከአስመራ የሚያገናኘው የቀጥታ የአየር መስመር ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዲከፈት ተደርጓል፡፡ ይህ የአየር መስመር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም አየር መንገዶች ክፍት እንደሆነ የሚያስታውቅ መልዕክት ለአገሮች ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣናት እንደተላለፈ ወሰንየለህ (ኮሎኔል) ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ‹‹UG650›› በሚል የኮድ መለያ የሚታወቀው የበረራ መስመር ከኬንያ ተነስቶ በአዲስ አበባ መቐለና አስመራ የሚደርስ ነው፡፡ እንደ አዲስ የተከፈተው ቀጥታ የበረራ መስመር UM 308 የሚል የኮድ መለያ ወጥቶለታል፡፡
ለጊዜው የተከፈተው አንድ የበረራ መስመር ሲሆን፣ በቀጣይ ከኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጋር በመመካከር ተጨማሪ አራት የበረራ መስመሮች እንደሚከፈቱ ዳይሬክተር ጄኔራሉ አስረድተዋል፡፡ ከሃያ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንና የኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎች ሐምሌ 5 ቀን 2010 ዓ.ም. በስልክ በመነጋገር፣ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ግንኙነት መሥርተዋል፡፡
ከኤርትራ ትራንስፖርትና ኮሙዩኒኬሽን ሚኒስቴርና ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ይሁንታን ያገኘው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ የበረራ መስመሩን መከፈት ለኤርትራ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ካሳዬ አሳውቋል፡፡ ‹‹ይህ ለሁለቱ አገሮች ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መከፈት ትልቅ ዜና ነው፤›› ብለዋል ወሰንየለህ (ኮሎኔል)፡፡
የአየር ክልሉ ዝግ ሆኖ በመቆየቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን አሳፍሮ ወደ አስመራ የተጓዘው ቦይንግ 737-800 ኔክስት ጄኔሬሽን አውሮፕላን በጂቡቲ በኩል መሄዱ ይታወሳል፡፡ ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡትን የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ያሳፈረው አውሮፕላን የበረረው አዲስ በተከፈተው ቀጥታ የበረራ መስመር እንደሆነ ታውቋል፡፡