Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት አምራቾች በውጭ ምንዛሪ እጥረት መማረራቸውን ገለጹ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ከባለድርሻ አካላት ጋር ሐምሌ 6 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባካሄደው የውይይት መድረክ፣ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዳማረራቸው አስታወቁ፡፡

      ኢንስቲትዩቱ የ2010 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ባቀረበበት መድረክ፣ በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ምርት የተሰማሩ ባለሀብቶች የውጭ ምንዛሪና የጥሬ ዕቃ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የመሬት ዕጦት ዘርፉን እየተፈታተኑ ያሉ ዋነኛ ችግሮች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡ በተለይ ለግብዓት መግዣ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማጣታቸው ምክንያት፣ ፋብሪካዎች በመዘጋትና ሠራተኞች በመበተን ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

      በየዕለቱ የሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በምርታማነታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩን የገለጹት ባለሀብቶቹ፣ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ የግንባታ ፈቃድ ማግኘትና የመሬት አቅርቦት ችግር ከፍተኛ ጋሬጣ እንደሆኑባቸው ጠቁመዋል፡፡

      ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የጭነት ትንራስፖርት ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተፎካካሪ ለመሆን እንደማያስችላቸው ገልጸዋል፡፡ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ የዘርፉን ችግሮች ኢንስቲትዩቱ በሚገባ እንደሚገነዘብ፣ ችግሮቹን ከባለሀብቶችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር በጋራ ለመፍታት ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ አሁን በአገሪቱ ባለው የለውጥ መንፈስ በመታገዝ ችግሮቹን ለመፍታት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የባለሀብቶቹን ቅሬታ ሪፖርት እንደሚመለከቱ ታውቋል፡፡

      በ2010 በጀት ዓመት ከንዑስ ዘርፉ ከወጪ ንግድ 62 ሚሊዮን  ዶላር  ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 28.2 ሚሊዮን ዶላር የተገኘ ሲሆን፣ አፈጻጸሙ የዕቅዱን 45.4 በመቶ ሆኗል፡፡ አፈጻጸሙ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው ከ17.2 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነፃፀር የ63.1 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡

      ለወጪ ንግድ አፈጻጸሙ አነስተኛ መሆን በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ምርታቸውን ማጓጓዝ ተስኗቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በማዕድን ማውጫ ቦታዎች ላይ በተከሰቱ ግጭቶች ፋብሪካዎች ሥራ ለማቋረጥ ተገደው እንደነበር ተገልጿል፡፡

      የውጭ ምንዛሪና የጥሬ ዕቃ እጥረትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑ አቶ ሳሙኤል አምነዋል፡፡ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ልማት ኢንስቲትዩት በራሱ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚንቀሳቀስ ተቋም ሳይሆን ንዑስ ዘርፉን ለመደገፍ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸው፣ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ በማማከር፣ የቴክኒክ ሥልጠና በመስጠትና ማነቆዎችን በመፍታት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድተዋል፡፡

      ‹‹ችግሮች ቢኖሩም አበረታች ውጤቶች ተገኝተዋል፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከታቀደው በታች ቢሆንም ከ2009 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር ከ17.2 ሚሊዮን ዶላር ወደ 28.2 ሚሊዮን ዶላር ማሳደግ መቻሉን፣ የዘርፉን የኢንዱስትሪ ምርቶች አጠቃላይ ዋጋ ወደ 39.7 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ታቅዶ 31.4 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን እንደ አበረታች ስኬት ጠቁመዋል፡፡

      ናሽናል ሲሚንቶ 17 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘቱ አቶ ሳሙኤል አመሥግነውታል፡፡ ዘሚሊ ቀለም ፋብሪካ በተፈጠረለት አገራዊ የገበያ ትስስር 175,855,290 ብር ሽያጭ ለማከናወን መቻሉ ተገልጿል፡፡

የገበያ ችግርና በቴክኖሎጂ የሠለጠነ ባለሙያ እጥረት በዘርፉ የተስተዋሉ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘርፉ ባሉ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች አማካይነት ለ7,756 ሰዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ ለ8,769 ያህሉ የሥራ ዕድል መፍጠሩን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች