በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ረዳት ሚኒስትር ሆነዋል
በአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩት አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶን፣ የሶማሊያ አምባሳደር ተደረጉ፡፡
አምባሳደር ያማሞቶ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ አምባሳደር ሆነው ለተወሰኑ ዓመታት ማገልገላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ላለፉት አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ደግሞ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር፡፡
አምባሳደር ያማሞቶ በረዳት ሚኒስትርነት ኃላፊነታቸው ወቅት እያሉ በቅርቡ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያና በጂቡቲ ጉብኝት አድርገው ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ይታወሳል፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአምባሳደር ያማሞቶ ምትክ አምባሳደር ቲቦር ናዥን በምትካቸው የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ዕጩ በማድረግ ካቀረቧቸው በኋላ፣ ከሳምንት በፊት የአገሪቱ ሴኔት ሹመታቸውን አፅድቋል፡፡
ረዳት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ቲቦር ናዥ በኢትዮጵያና በኤርትራ ጦርነት ወቅት በአዲስ አበባ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ማገልገላቸው አይዘነጋም፡፡
ከረዳት ሚኒስትርነታቸው የተነሱትን አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ደግሞ በሶማሊያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው እንዲያገለግሉ ሰሞኑን መሾማቸውን የአሜሪካ መንግሥት በይፋ አስታውቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ያገለገሉ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቶችን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ተጠሪ ማድረጋቸው፣ ቀደም ብሎ በዚህ ኃላፊነት ላይ የነበሩትን አምባሳደር ያማሞቶ በሶማሊያ መመደባቸው፣ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳይ የውጭ ግንኙነት ትኩረት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያተኮረ መሆኑን እንደሚያሳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡