Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ቢሮ የ40/60 ቤቶች ኢንተርፕራይዝን ክፉኛ ተቸ

የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ቢሮ የ40/60 ቤቶች ኢንተርፕራይዝን ክፉኛ ተቸ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ቢሮ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት የከተማው የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በሥራ አፈጻጸሙ ደካማ፣ በንብረትና ሀብት አስተዳደርም ዝርክርክነት የተንሰራፋበት መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኢንተርፕራይዙ በበኩሉ ሌብነት መኖሩን አምኖ፣ ሪፎርም ካልተካሄደ ባለው መዋቅር የተያዘው ግዙፍ የቤቶች ግንባታ ዕቅድ ማሳካት አይቻልም ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር ጽጌወይን ካሳ ረቡዕ ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ለከተማው ምክር ቤት ባቀረቡት የክዋኔ ኦዲት፣ የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ በእንከኖች የተሞላ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በቀረበው ሪፖርት ኢንተርፕራይዙ በተቋቋመበት ዓላማ መሠረት በሦስት ዓመት ውስጥ 20 ሺሕ ቤቶችን ለመገንባት የተያዘው ዕቅድ አለመሳካቱን ተመልክቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም የንብረትና የገንዘብ አያያዝ፣ እንዲሁም አጠቃቀም ላይ በርካታ ችግሮች መኖራቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል አንዱ በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው የሥራ ተቋራጮች ምልመላ፣ የቴክኒክ ግምገማ ውጤታቸው ከ70 በመቶ በታች የሆኑ ተቋራጮች በቤቶች ግንባታ መሳተፍ እንደሌለባቸው ያዛል፡፡ ነገር ግን የቴክኒክ  ግምገማ ውጤታቸው ከ70 በመቶ በታች የሆኑ ሥራ ተቋራጮች እንዲያልፉ ተደርጎ ሥራ እንደተሰጣቸው ተጠቅሷል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው በእህል ንግድና በሕንፃ አቅራቢ ሳይቶች የሚካሄዱ የ40/60 ቤቶች ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ ያልተቻለው፣ የኤሌክትሪክና የሳኒተሪ ዕቃዎች እጥረት በማጋጠሙ መሆኑን ኢንተርፕራይዙ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ዋና ኦዲተር ቢሮ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት በጎፋ ማዕከላዊ መጋዘን ውስጥ 352.99 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የኤሌክትሪክና የሳኒተሪ ዕቃዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዋና ኦዲተር ጽጌወይን ከውጭ አገር የገቡ 271.3 ሜትሪክ ቶን ባለ ስድስት ቁጥር ብረቶችና 3‚850.69 ሜትሪክ ቶን ባለ ስምንት ቁጥር ብረቶች፣ ለዝናብና ለፀሐይ ተጋልጠው ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የእነዚህ ብረቶች ዋጋ በድምሩ ከ1.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ በግንባታ ግብዓት ማጠናቀቂያ ሰነድ ላይ ለተመሳሳይ መጠን ግንባታ ጥቅም ላይ የሚውል የግብዓት መጠን ተመሳሳይ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ነገር ግን በሰንጋ ተራ ሳይት ዳታ ሥራ ተቋራጭና ኢኩዌተር ሥራ ተቋራጭ፣ እንዲሁም በክራውን ሳይት ኤፍኢ ሥራ ተቋራጭና ፍሊንትስቶን ሥራ ተቋራጭ የተለያዩ የግብዓት ዓይነቶችን በብልጫ ወስደው መገኘታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ለማሳያ ከቀረቡ እነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባዘጋጀው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ላይ ኢንተርፕራይዙ ከ2005 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ 20 ሺሕ ቤቶች እንደሚገነባ የተገለጸ ቢሆንም፣ ግንባታቸው ተጠናቆ ለኅብረተስቡ የተላለፉት 1‚292 ቤቶች ብቻ መሆናቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

ከ161 ሺሕ በላይ ቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ካደረጉበት ከ2004 ዓ.ም. ወዲህ፣ የቤት ፈላጊዎች ጉጉቱ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም፣ የሥራ አፈጻጸሙ ደካማ መሆን ብዙዎችን ተስፋ እያስቆረጠ መሆኑን፣ ከዚህም አልፎ ሕግና ሥርዓት የማይከበርበት፣ ሌብነት የተንሠራፋበት እየሆነ መምጣቱ ፕሮጀክቱን እየተከታተሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

 ከአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ምክትል ቢሮ ኃላፊነት ተነስተው ከአምስት ወራት በፊት የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት አቶ መኮንን አምባዬ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሌብነት እንዳለ ያምናሉ፡፡

አቶ መኮንን እንደተናገሩት፣ በተካሄደው የክዋኔ ኦዲትና እንዲሁም መሥሪያ ቤታቸው ካካሄደው ኦዲት በመነሳት አጥፊዎች ላይ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ እየተወሰደም ነው፡፡

አቶ መኮንን እንደሚሉት ኢንተርፕራይዙ 20 ሺሕ ቤቶችን ከገነባ በኋላ እንዲፈርስ ሆኖ የተደራጀ ነው፡፡ ነገር ግን የቤት ፈላጊዎች ምዝገባ ከተካሄደ በኋላ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑ በመታወቁ፣ በአሁኑ ወቅት 38,500 ቤቶችን እየገነባ ነው፡፡ ‹‹ግዙፉን ዕቅድ ለማሳካት ግን አሁን ያለው አደረጃጀት ስለማይችል ሪፎርም ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡  

‹‹የነበረው አደረጃጀት ይህንን ሥራ ሊያከናውን በሚችልበት ደረጃ ባለመሆኑ፣ አዲስ ሪፎርም እያካሄድን ነው፤› ብለው፣ በዋና ኦዲተር የቀረቡ ጉዳዮች ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አንዳንድ የኦዲት ውጤቶች ግን ትክክል እንዳልሆኑ አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...