Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጉደኛው መሪያችን 

ጉደኛው መሪያችን 

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ምን እንላቸዋለን? ከአሁን በፊት መሪዎቻችንን ለመግለጽ የተጠቀምንባቸውን ቃላት ሁሉ የሚያልፉ ሆኑብኝ። ጉደኛ የሚለውን ቃል የመረጥኩት ያልተለመደና ያልታየ ነገርን ስለሚገልጽ ነው። በሌሎች ስንቀና የእኛም ተራ ደርሶ ይሆንን? ደቡብ አፍሪካ ኔልሰን ማንዴላ ነበራት፡፡ ህንድ ማኅተመ ጋንዲ ነበራት፣ አሜሪካ ጆርጅ ዋሽንግተን ነበራት፡፡ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ደርሰውላት ይሆን?

ፋታ እንስጣቸው እያልን ስናወራ፣ እርሳቸው በድርጊታቸው አንዱን ሳናጣጥም ሌላ እየጨመሩ በመልካምነት ፋታ አሳጡን።

ቀድመው ያሞገሱትን ማማት ይቸግራል ብለን፣ ተስፋን በሥጋት ሰንቀን፣ ዳር ቆመን በጥርጣሬ የምናይ ሁሉ ጉድ ፈላብን። ዛሬ ዛሬ ተስፋ ሥጋትን እያሸነፈ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ድጋፍ እየጎረፈ ነው። ትናንት እንዳንጨራረስ እየፈራን ከዚህ አጣብቂኝ ማን ያወጣናል ስንል ነበር። የማይታለፍ የለም ያ ታለፈና አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በፍቅርና በይቅርታ ሁሉንም እየማረኩና እያስደመሙ፣ በደስታም እያሰከሩ በሚገርም አዲስ አካሄድ ኢትዮጵያን እያሻገሩ ይገኛሉ። ግን ቆም ብሎ ለሚያስተውል ይህ ትዕይንት ከሥጋና ደም ሥራ በላይ ነው። የኢትዮጵያ አምላክ በምሕረት እርሱ ራሱ ምድራችንን በፈውሱ እየጎበኘ እንደሆነ ለአስተዋይ ሰው ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ ደግሞ በሥራ ላይ ሲሆን፣ ጠላት ለማሰናከል ሙከራ ያደርጋል እንጂ ፈጣሪን ያደናቅፈዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

 

ያልተጠበቀው የኢትዮጵያዊነት ውበት ነገ እጅግ ደምቆ ሲበራ ልናይ ከሆነ፣ የማይጨበጥ ሕልም የሆነብን ዴሞክራሲ ነገ እንደ ዕለት እንጀራችን የምንመገበው ዕውነታ ሊሆን ከሆነ፣ ዛሬ የሚገፋፉትና የሚጠላለፉት ፖለቲከኞች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ሆነው በወንድማማችነት መንፈስ የአስተሳሰብ ፍጭትና ፍትጊያ ሲያደርጉ ዓይተን ለመሆኑ እንዲህ ያሉ ድንቅዬዎች ከየት መጡ እስክንል ድረስ የሚያስገርሙን ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹ሜዳውም ይኼው ፈረሱም ይኼው› በሀቅ መሪህን ምረጥ ተብሎ ጉድ የሚባልበት ጊዜ ሊመጣ ከሆነ፣ እኛስ የየራሳችንን የኑሮ ብልኃታችንን እንደለመድነው ከዚህ በኋላ ማስኬድ እንዴት ይቻለናል?

ዛሬ አይደርስ መስሎን ራሳችንን ለኢትዮጵያ የተዘጋጀን እንደሆነ ለመጠየቅ ሐሳቡም የለንም። ዛሬ ዓይናችንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ላይ አተኩረን፣ ራሳችንን ከኃላፊነት አሰናብተናል። ቁም ነገሩ ኢትዮጵያ ልትነሳና ልትደምቅ፣ ይህንንም መቀልበስ በማይቻል ጎዳና ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በብልኃት የተሞላ የጥድፊያ ጉዞ ላይ ያሉ ይመስላል። ታዲያ ለዚህ የመታደስ ዘመን ራሳችንን በመስዋዕትነት ለመስጠት እያሰብን ነን ወይ? ኢትዮጵያ የሚሞትላት ሳይሆን በመስዋዕትነት በመኖር ለችግሯ ሊደርስላት የሚችል ዜጋ የምትፈልግበት ጊዜ እየመጣ ነው። ለመልካም ኑሮ አገራችንንና ምድራችንን ትተን የተሰደድን ሁሉ፣ ለምድራችን ፈውስ ለመሆን ምቾትን ንቀን፣ ከሕዝባችን ጋር መከራ በመቀበል የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት ማድረግ የምትጀምርበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ በፅድቅና በእውነት ለሕዝብ አገልጋይ በመሆን ራስን ከምቾት አፋተው ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት የሚያደርጉበት ጊዜ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለኢትዮጵያ እየሠሩ ያሉትን እየወደድንና እያወደስን ባለበት በዚህ ወቅት፣ ለእርሳቸው ኢትዮጵያ ራሳችንን በማዘጋጀት እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳን። በመስዋዕትነት በምድረ ኢትዮጵያ በሥራ ተጠምደን፣ የአገራችንን ታሪክ በራሳችን ትውልድ ዘመነ ጊዜ ለውጠን በማየት ከዚህ ዓለም አልፈን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ እንዳሉት ያኔ እኛም በክብር ኢትዮጵያ እንሆናለን።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ‹‹ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ›› ብለው ሲያውጁ፣ ያኔ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ለሰማይ አደራ ሰጥተው፣ ራሳችንን ለተዓምሩ እንድናዘጋጅ ልባችንን ማነሳሳታቸው ነበር። እንደተባለውም ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሊባርክና ያሳለፍነውን የመከራ ዘመን ሊያስረሳን የተስፋ ጭላንጭል ከጊዜ ወደ ጊዜ ቦግ እያለ እየተጨመረ በመብራት ላይ ይገኛል። ለዚህ አስደናቂ የታሪክ ዕድል ራሳችንን ለኢትዮጵያ ለማዘጋጀት መዘርጋት የሚገባን ይመስለኛል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የአምላክን በረከት ከመጥራት አኳያ በንፅፅር የንግግራቸው ማሳረጊያ አድርገው የሚጠቀሙበት ሌላ ሐሳብ አላቸው። ያም፣ ‹‹ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልፅጋ ለዘላለም ትኑር፤››  የሚለው ቁም ነገር ነው። ፈጣሪም ልመናችንን ሰምቶ እየጎበኘን ባለበት ሁኔታ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ታማኝ ሆነው ራሳቸውን ለተባረከች ኢትዮጵያ፣ ራሳቸውን እየሰጡ ባለበት ሁኔታ፣ እኛስ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ? እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይጎበኛታልም።

(ዘለለም እሸቴ (ዶ/ር)፣ ከአዲስ አበባ)

* * *

የካሽ ሬጅስተር ጉዳይ ይታሰብበት

የጽሑፌ ርዕስ የካሽ ሬጅስተር (የገንዘብ መቀበያ መሣሪያ) ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በአጭር ጊዜ በጣም የከበሩ ጥቂት ነጋዴዎች ቢኖሩ የካሽ ሬጅስተር አቅራቢዎች ስለመሆናቸው በንግድ ላይ ያለነው ምስክር ነን፡፡ ለዚህ ሁሉ ከ90 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያዊ መሣሪያውን ለማቅረብ ዕድሉን ያገኙት በጣት የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ናቸው፡፡ እነሱም በትንሽ ብር ያመጡትን መሣሪያ ከ100 ፐርሰንት በላይ በማትረፍ ላለፉት ዓመታት በአጭር ጊዜ ትርፋማ መሆን ችለዋል፡፡ በተጨማሪ እጅግ በጣም የተወሳሰበ የመሣሪያ መመርያዎችን በነጋዴው ኅብረተሰብ ላይ በመደራረብ ነጋዴዎች መሣሪያዎቻቸው ለእነዚህ ውርስ አድርገው መቅረታቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ያለመሣሪያ መሥራቱ ምን ያህል እንግልት እንደሚፈጥርም ሁሉ የሚረዳው ነው፡፡

ለአብነት አንድ ሰው የሒሳብ ሪፖርት ከዘጋ በኋላ የገዛው መሣሪያ ራሱ መያዝ አይችልም፡፡ ይህ ሰው ከሁለት ወይም ከሦስት ዓመት በኋላ ሌላ ድርጅት ቢያቋቁም፣ የመጋዘን ኪራይ በማለት ተጨማሪ ወጪ ከመጠየቁም በላይ የመጋዘን ኪራይ ከከፈለም በኋላ የቲን ለውጥ፣ የባለቤትነት ለውጥ፣ የሰርቪስ፣ ወዘተ እየተባለ ያላግባብ ክፍያ ይጠየቃል፡፡ በተለይ ጀማሪና አነስተኛ ነጋዴዎች በምሬት ለእነዚህ አካላት ብዝበዛ የሚጋለጡበት አሠራር ያለ ሲሆን፣ በጥናት ላይ ተመሥርቶ አገራችንም ከምትከተለው የነፃ ገበያ ሥርዓት መርህ ሁሉም ነጋዴ መሣሪያዋን ቢያቀርብ፣ ግለሰቦች የገዙት መሣሪያ ተጠቃሚ ቢሆኑና ወንጀል የሠራ ነጋዴ በአገሪቱ ሕግ ተጠያቂ የሚሆንበት አሠራር ቢዘረጋ መፍትሔ ነው እላለሁ፡፡ አለበለዚያ በተለይ ሁሉም ነጋዴ ጥቃቅንና አነስተኛ ጨምሮ ወደ ዘመናዊ የገንዘብ መቀበልና መስጠት የመግባት ሥርዓቱ እጅግ የሚደናቀፍ መሆኑንም መጠቆም እወዳለሁ፡፡

(ሕይወት ነኝ፣ ከሳሪስ)

* * *

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...